ሀገር አቀፍ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ዓመታዊ የሰብአዊ መብቶች የምስለ-ችሎት ውድድር


አጭር ገለጻ

በኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) አዘጋጅነት የሚካሄደው ዓመታዊ ሀገር አቀፍ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች የሰብአዊ መብቶች የምስለ-ችሎት ውድድር (National High Schools Human Rights Moot Court Competition በምሕፃረ ቃሉ NHSHRMCC) ታዳጊ ተማሪዎች በሰብአዊ መብቶች ዙሪያ ያላቸውን ዕውቀት፣ አመለካከት እና ክህሎት ለማሳደግ ታስቦ የሚዘጋጅ ነው፡፡ የምስለ ችሎት ውድድሩ በሕግና ሰብአዊ መብቶች ባለሞያዎች የሚዳኝ ከሞላ ጎደል የመደበኛ ፍርድ ቤት ክርክር ሥርዓትን የሚከተል አስተማሪ የውድድር ዐይነት ሲሆን ተወዳዳሪ ተማሪዎች ተገቢው ስልጠና ከተሰጣቸው በኋላ ምናባዊ በሆነ የሰብአዊ መብቶች ጉዳይ (hypothetical case) ላይ ተመሥርተው አመልካች እና ተጠሪን በመወከል የጽሑፍ እና የቃል ክርክር የሚያደርጉበት ነው።

ውድድሩ ሁሉም ክልሎች እና ከተማ መስተዳድሮች የሚሳተፉበት እና በተለይም የክልል እና ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮዎች ትምህርት ቤቶችን እና ተወዳዳሪ ተማሪዎችን በመምረጥ፣ ክልላዊ የውስጥ ውድድሮች ሲካሄዱ ተማሪዎች እና ሌሎች የት/ቤት ማኅበረሰብ አካላት እንዲከታተሉ በማድረግ እና ውድድሮቹን በማስተባበር የሰብአዊ መብቶች ግንዛቤ በትምህርት ቤቶች እንዲስፋፋ ከኢሰመኮ ጋር በከፍተኛ ትብብር የሚሠሩበት ዕድል እየፈጠረ ይገኛል፡፡

ኢሰመኮ በሕግ ከተሰጡት ተግባራት እና ኃላፊነቶች መካከል አንዱ ሰብአዊ መብቶችን ማስተዋወቅ እና ማስተማር ነው፡፡ ይህንኑ ኃላፊነት ይበልጥ ለማሳካት እና ራዕዩን “ሰብአዊ መብቶች ባህል የሆኑባት ኢትዮጵያን ማየት” እውን ለማድረግ የሚረዱ የተለያዩ የሰብአዊ መብቶች ትምህርት እና ስልጠና መርኃ-ግብሮችን ቀርጾ በመተግበር ላይ ይገኛል፡፡ ከእነዚህ የሰብአዊ መብቶች ማስፋፊያ መርኃ-ግብሮች አንዱ በሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ተማሪዎች መካከል ዓመታዊ የሰብአዊ መብቶች የምስለ-ችሎት ውድድሩ አንዱ ነው፡፡

የዚህ ዐይነት ውድድሮች ተማሪዎች የተለያዩ የሰብአዊ መብቶች ርዕሰ ጉዳዮች ላይ እንዲያነቡ፣ እንዲመራመሩ እና ለሰው ልጆች ያላቸውን ፋይዳ እንዲረዱ ለማድረግ ያስችላሉ፡፡ በተጨማሪም ተወዳዳሪዎች የራሳቸውም ሆነ የሌሎች ሰዎች መብቶች ሲጣሱ ለምን ብለው የሚጠይቁበትን ክህሎት እንዲያዳብሩ የሚረዳ ነው፡፡ ከዚህም ባለፈ ከተወዳዳሪ ተማሪዎች በተጨማሪ ውድድሮቹን የሚከታተሉ ሌሎች ተማሪዎች እና የትምህርት ቤት ማኅበረሰብ አባላት ስለ ሰብአዊ መብቶች ይበልጥ እንዲያውቁ እና ለሌሎች ሰዎች መብቶች እንዲቆረቆሩ የማነሳሳት ሚና ይጫወታል፡፡

ሀገር አቀፍ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች የሰብአዊ መብቶች የምስለ-ችሎት ውድድር በሦስት ደረጃዎች የሚከናወን ነው:-

  • ክልላዊ ውድድር፣
  • ሀገር አቀፍ የጽሑፍ መከራከሪያ (Essay) ውድድር እና
  • ሀገር አቀፍ የአሸናፊዎች አሸናፊ የቃል ክርክር ውድድር ናቸው፡፡

በዚህም መሠረት በመጀመሪያ ውድድሩ በክልል ደረጃ ሲደረግ ተወዳዳሪዎች የጽሑፍ መከራከሪያቸውን በማዘጋጀትና በክልል ደረጃ የቃል ክርክር ውድድርን በማድረግ ይጀመራል፡፡ በዚህም ተወዳዳሪዎች በተሰጣቸው ምናባዊ ጉዳይ ላይ በአመልካች እና በተጠሪ (በሁለቱም) ወገን በመሆን የጽሑፍና የቃል ክርክራቸውን ከተለያዩ የሕግ ድንጋጌዎች እና የሰብአዊ መብቶች መርሖች ጋር በማሰናሰል እንዲያቀርቡ ይደረጋል፡፡ የውድድሩን ፍትሐዊነት እና ጥራት ለመጠበቅ ሲባል የተሳታፊ ተማሪዎችን ውድድር በየአካባቢያቸው የሚገኙ ዳኞች፣ ዓቃቢያነ ሕግ እና ሌሎች የሕግ እና ተዛማጅ ባለሙያዎችን በመጋበዝ እንዲዳኙት ይደረጋል፡፡

በመቀጠልም፣ ከሁሉም ተሳታፊ ክልሎች እና ከተማ አስተዳደሮች በቃል ክርክር 1ኛ በመውጣት አሸናፊ የሆኑ ቡድኖች ለመጨረሻው ሀገር አቀፍ የአሸናፊዎች አሸናፊ የቃል ክርክር ውድድር ለማለፍ የሚያስችላቸውን የጽሑፍ መከራከሪያቸውን (Essays) ለኮሚሽኑ እንዲልኩ ይደረጋል።

በመቀጠልም በኮሚሽኑ በሚደረግ የመከራከሪያ ጽሑፍ ምዘና ከፍተኛ ነጥብ ያመጡ ስምንት ቡድኖች ወደመጨረሻው ዙር በማለፍ እና ወደ አዲስ አበባ ከተማ በመምጣት የቃል ክርክር ውድድራቸውን እንዲያደርጉ ይደረጋል፡፡ በዚህም መሠረት የመጨረሻው ሀገር አቀፍ የአሸናፊዎች አሸናፊ የቃል ክርክር ውድድር በሦስት ዙሮች – (በሩብ ፍጻሜ፣ ግማሽ ፍጻሜ እና ፍጻሜ) ይከናወናል፡፡

በሁሉም ደረጃዎች በሚደረጉ ውድድሮች በዳኝነቱ ሂደት ሊከሰት የሚችል ማንኛውንም ዐይነት ወገንተኝነት/አድሎ ለማስቀረት ሲባል የተወዳዳሪዎች የመከራከሪያ ጽሑፎች ልዩ መለያ (ኮድ) ተሰጥቷቸው ለመዛኞች ይተላለፋሉ፡፡ በተጨማሪም በቃል ውድድሩ ወቅት ተወዳዳሪ ቡድኖች በየዙሩ የቡድን ቁጥር እጣ እንዲያወጡ በማድረግ እስከ ውድድሩ ፍጻሜ ድረስ በቡድን ቁጥራቸው ብቻ እንዲታወቁ እና የመጡበት ቦታ ለዳኞች እና ለሌሎች ተሳታፊዎች እንዳይገለጽ ይደረጋል፡፡

በሦስቱም ደረጃዎች አሸናፊ ተማሪዎች በግላቸው እና ተሳታፊ ትምህርት ቤቶች የተለያዩ ዕውቅና እና ሽልማቶች ያገኛሉ።

ሀገር አቀፍ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች የሰብአዊ መብቶች የምስለ-ችሎት ውድድር ከደቡብ አፍሪካ ሀገር አቀፍ የትምህርት ቤቶች የምስለ ችሎት ውድድር (National Schools Moot Court Competition) ልምድ በመነሳት በኢሰመኮ አዘጋጅነት ከ2013 ዓ.ም. ጀምሮ በመካሄድ ላይ የሚገኝ ዓመታዊ መርኃ-ግብር ነው፡፡

ውድድሩ በ2013 ዓ.ም. ለመጀመሪያ ጊዜ ሲደረግ ምናባዊ ጉዳዩ የሕፃናት የመማር እና ሐሳብን በነጻነት የመግለጽ መብቶችን እንዲዳስስ ተደርጎ የተዘጋጀ ነበር፡፡ በዚህ ውድድር፣ ከስምንት ክልሎች እና ሁለት ከተማ አስተዳደሮች የተውጣጡ 35 የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች እና 80 ተማሪዎች ተሳትፈዋል፡፡ ውድድሩም በአዲስ አበባ እቴጌ መነን የሴቶች አዳሪ ትምህርት ቤት አሸናፊነት ተጠናቋል።

በ2014 ዓ.ም. በተከናወነው ሁለተኛው የሰብአዊ መብቶች የምስለ ችሎት ውድድር ላይ በ10 ክልሎች እና 2 ከተማ አስተዳደሮች የሚገኙ 63 የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች እና 130 ተወዳዳሪ ተማሪዎች ተሳታፊዎች የነበሩ ሲሆን፣ ውድድሩ በጎንደር ዩኒቨርሲቲ ማኅበረሰብ ትምህርት ቤት አሸናፊነት ተጠናቋል፡፡ የውድድሩ ምናባዊ ጉዳይ ትኩረትም የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች ጥበቃ እና ሰብአዊ ድጋፍ የማግኘት መብት ላይ ነበር፡፡

በ2015 ዓ.ም. የተከናወነው ሦስተኛው የሰብአዊ መብቶች የምስለ ችሎት ውድድር ምናባዊ ጉዳይ ትኩረቱን ለአካለ መጠን ባልደረሱ እና የወንጀል ድርጊት ተሳትፎ የተጠረጠሩ አዳጊ ወጣቶች ላይ አድርጎ የነበረ ሲሆን፣ በውድድሩ በ10 ክልሎች እና በ2 ከተማ አስተዳደሮች የሚገኙ 72 የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች እና 144 ተወዳዳሪ ተማሪዎች ተሳታፊ ሆነዋል፡፡ የምስለ-ችሎቱ የፍጻሜ ውድደር በሃዋሳ SOS Herman Gmeiner ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት አሸናፊነት ተጠናቋል። የተወዳዳሪ ትምህርት ቤቶች እና ተወዳዳሪ ተማሪዎች ቁጥር በየዓመቱ እያደገ መምጣት የሰብአዊ መብቶች ዕውቀትን በትምህርት ቤቶች አካባቢ ለማስፋፋት በባለድርሻ አካላት ዘንድ ያለው ትብብር እያደገ መምጣቱን እና የውድድሩም ተደራሽነትና ለሰብአዊ መብቶች መስፋፋት ያለው አበርክቶ እየጨመረ መሄዱን ያሳያል፡፡

የሰብአዊ መብቶች ትምህርት በትምህርት ሥርዐት ውስጥ እንዲጠናከር በትብብር ለመሥራት ኢሰመኮ እና የኢ.ፌ.ዴ.ሪ. ትምህርት ሚኒስቴር በ2015 ዓ.ም. የተፈራረሙት የመግባቢያ ሰነድ ከዘረዘራቸው ተግባራት መካከል የሰብአዊ መብቶች ምስለ-ችሎት ውድድርን በጋራ ማካሄድ እንደመሆኑ የውድድሩ ተደራሽነት እየሰፋ እና በተሻለ ጥራት እየተከናወነ እንደሚቀጥል የታመነ ነው፡፡

በቀጣይ በሚደረጉ ውድድሮች ላይም በሰብአዊ መብቶች የምስለ-ችሎት ውድድር ከዚህ በፊት ያልተሳተፉ ትምህርት ቤቶችን እንዲሳተፉ ለማድረግ፣ እንዲሁም የተወዳዳሪ ትምህርት ቤቶች እና ተወዳዳሪ ተማሪዎችን ቁጥር በየዓመቱ ለማሳደግ የሚያደርገውን ጥረት በማጠናከር የውድድሩን ዓላማ ለማሳካት ይሠራል፡፡

ሀገር አቀፍ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች የሰብአዊ መብቶች ምስለ-ችሎት ውድድር በኢሰመኮ አማካኝነት የሚዘጋጅ ቢሆንም፣ የትምህርት ሚኒስቴር በተለይም የክልል እና የከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮዎች ተወዳዳሪ ትምህርት ቤቶችን እና ተማሪዎችን በመምረጥ እና ክልላዊ የውስጥ ውድድሮችን በማስተባበር የሚሳተፉበት ነው፡፡

በተጨማሪም ውድድሩ በሚካሄደባቸው ከተሞች የሚገኙ የመንግሥት ሥራ ኃላፊዎች፣ የትምህርት ቤቶች ርዕሰ-መምህራን፣ የተወዳዳሪ ተማሪዎች አሰልጣኝ መምህራን፣ ቤተሰቦች እና በየአካባቢው የሚገኙ የሕግ እና የሰብአዊ መብቶች ባለሙያዎች የሚያደርጉት ትብብር ለዝግጅቱ በስኬት መጠናቀቅ ከፍተኛ አስተዋጽዖ የሚያደርግ ነው፡፡

በሌላ በኩል ያለፉትን ሦስት ዙር ዓመታዊ ምስለ ችሎት ውድድሮች ለኮሚሽኑ የሰብአዊ መብቶች ሥራዎች የገንዘብ ድጋፍ የሚያደርጉ ዓለም አቀፍና አህጉራዊ ድርጅቶች የምስለ-ችሎት ውድድር ዝግጅቱን በገንዘብ በመደገፍ ከፍተኛ አስተዋጽዖ ሲያበረክቱ ቆይተዋል፡፡ ከነዚህም ለጋሽ ድርጅቶች መካከል የፕሪቶሪያ ዩኒቨርሲቲ የሰብአዊ መብቶች ማእከል፣ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የልማት ፕሮግራም – United Nations Development Program (UNDP)፣ የጀርመን ኤንባሲ፣ የኖርዌይ ኤንባሲ እና የዴንማርክ ሰብአዊ መብቶች ተቋም – Danish Institute for Human Rights (DIHR) ይገኙባቸዋል፡፡