በመጀመሪያው የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች የምስለ-ችሎት ዉድድር የተሳተፉ ባለሞያዎችንና ተማሪዎችን፣  አሰልጣኞችን፣ የክልል ትምህርት ቢሮ ተወካዮችንና እና የኮሚሽኑ ኃላፊዎችን ያሳተፈው ይህ የውይይት መድረክ፣ በዘንድሮ ዓመት ለሚካሄደው ሁለተኛ ዙር ውድድር ዝርዝር መመሪያ በማዘጋጀትና የጊዜ ሰሌዳ በመቅረጽ በባለድርሻዎች ዘንድ መግባባትን ለመፍጠር የተዘጋጀ ነው። ከጥር 20 እስከ ጥር 21 ቀን 2014 ዓ.ም. የሚካሄደው ስብሰባ በመጀመሪያው ሀገር አቀፍ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች (ት/ቤቶች) ምስለ-ችሎት ውድድር ዙሪያ የታዩ ተሞክሮዎችን ለመገምገም በተደረገው ጥናት ላይ እና በጥናቱ መሰረት ማሻሻያ በተደረገባቸው የውድድሩ መመሪያዎች ላይ ተጨማሪ ግብዓቶችን ይሰበስባል። 

በመድረኩ ላይ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የኢሰመኮ ምክትል ዋና ኮሚሽነር ራኬብ መሰለ በ2013 ዓ.ም. የተካሄደው የመጀመሪያው ዙር ውድድር በሕፃናት መብቶች ዙሪያ ያተኮረ የምናባዊ ጉዳይ ክርክር እንደነበር አስታውሰው፣ “በ2014 ዓ.ም. የሚመረጠው ምናባዊ የሰብአዊ መብቶች ጉዳይ የሀገራችንን ወቅታዊ ሁኔታ ግምት ውስጥ በማስገባት በግጭቶች ምክንያት በተማሪዎችና በማኅበረሰቡ ላይ ሊከሰቱ የሚችሉ ዘርፈ ብዙ የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶችንና ተያያዥ ጉዳዮችን የሚመለከት ይሆናል” ብለዋል። በተጨማሪም ምክትል ዋና ኮሚሽነሯ በኢሰመኮ ስትራቴጂክ እቅድ መሰረት የምስለ ችሎት ውድድር ዓላማ የተማሪዎችንና የማኅበረሰቡን የሰብአዊ መብቶች እውቀት፣አመለካከትና ክህሎት እንዲሁም ስለ ፍትሕ አስተዳደርና እና የዳኝነት ሥርዓት ያላቸውን ግንዛቤ ማዳበር እንደሆነ ገልጸዋል፡፡

የመጀመሪያዉ  የምስለ-ችሎት ውድድር ከስምንት ክልሎች እና ከሁለቱ የከተማ መሰተዳድሮች የተውጣጡ 35 ትምህርት ቤቶችንና 80 ተማሪዎችን ያሳተፈ የነበረ ሲሆን፣ ሁለተኛው የምስለ-ችሎት ውድድር በክልል ደረጃ  በአስር ክልሎችና በሁለት የከተማ መስተዳድሮች በሚገኙ ሁለተኛ ደረጃ ት/ቤቶች ያሳትፋል። በሀገር አቀፍ ደረጃ ደግሞ እነዚህን ክልሎች በሚወክሉ አሸናፊ ተማሪዎች መካከል የሚካሄድ ይሆናል፡፡  

የመጀመሪያው ሀገር አቀፍ ውድድር ውጤቶች፣ በግምገማ ጥናት የተገኙ ውስንነቶች እና የተወሰዱ የማሻሻያ እርምጃዎችን በተመለከተ ለውይይቱ ተሳታፊዎች የኢሰመኮ የሰብአዊ መብቶች ትምህርት ክፍል አስተባባሪ የሆኑት አቶ ተምኪን መኮንን ገለጻ አድርገዋል፡፡

“ልጆች ናቸው፣ አያውቁትም፣ አይችሉትም በሚል ያልተገባ እሳቤ ልንሳተፍባቸው እና ልናውቃቸው ከሚገቡ ነገሮች ልንገደብ አይገባም፤ ልጆች እናውቃለን፣ ጉዳዮችን የመመርመር እና የመረዳት አቅምም አለን፡፡ በኢሰመኮ በተዘጋጀው የምስለ ፍርድ ቤት ውድድር ላይ መሳተፌ የሰብአዊ መብቶች ፅንሰ ሃሳብ እና ህጎች ላይ ሰፊ ግንዛቤ እንዲኖረኝ አድርጎኛል፤ በተለይም በውድድሩ ሂደት፣ በተመሳሳይ ጉዳይ ላይ የአመልካችና የተጠሪ ተወካይን ሚና ወስደን ለክርክር እንድንቀርብ መደረጉ፣ በውድድሩ ላይ እንዲሁም ከውድድሩ በሁዋላ ባለኝ የህይወት መስተጋብር፣ የአስተሳሰብ አድማሴን እና ነገሮችን ከተለያየ አቅጣጫ የመመልከት እና የመረዳት ችሎታዬን እንዳዳብር ረድቶኛል፡፡”

በኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን በተዘጋጀው የጀመሪያው አገር አቀፍ የትምህርት ቤቶች የምስለ ፍርድ ቤት ውድድር ምርጥ ተናጋሪ በመሆነ አሸናፊና የምክክር አውድጥናቱ ተሳታፊ የሆነችው ተማሪ ሳውላወርቅ አለማየሁ

የምስለ-ችሎት ውድድር ተማሪዎች ተገቢው ስልጠና ከተሰጣቸው በኋላ ምናባዊ በሆኑ የሰብአዊ መብቶች ጉዳዮች ላይ ተመስርተው አመልካች እና ተጠሪ በመሆን የቃል እና የጽሑፍ ክርክር የሚያደርጉበትና በሕግና የሰብአዊ መብቶች ባለሞያዎች የሚዳኙበትና ከሞላ ጎደል የመደበኛ ፍርድ ቤት ክርክር ሥርዓትን የሚከተል ማስተማሪያ ወይም ግንዛቤ ማስፋፍያ የውድድር አይነት ነው፡፡ ለሁለት ቀናት የሚካሄደው የውይይት መድረክ ሲገባደድ ባለድርሻ አካላት የሚጠበቅባቸውን ሚናና የስራ ኃላፊነት ተሻሽሎ በወጣው መመሪያ መሰረት በመለየት፣ ሁለተኛውን ውድድር ለማከናውን የወጣውን መርኃ ግብር ለመተግበር የጋራ መግባባት ላይ የሚደርሱበት እንደሚሆን ይጠበቃል፡፡