የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) በባሕር ዳር ከተማ ሰኔ 17 ቀን 2015 ዓ.ም. አማራ ክልል የሕግ፣ ፍትሕ እና አስተዳደር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አባላት የስልጠና እና ውይይት መድረክ አዘጋጅቷል። መድረኩ የክልል ምክር ቤት አባላት በሰብአዊ መብቶች ዙሪያ ያላቸውን ግንዛቤ በማሳደግ የክትትልና ቁጥጥር ዐቅማቸውን ለማጎልበት ያለመ ነው።
በዝግጅቱ ላይ ከሌሎች ሀገራት ምክር ቤቶች ተሞክሮ በማጣቀስ የምክር ቤቱ አባላት የሲቪልና ፖለቲካ መብቶች እንዲከበሩ እና እንዲሟሉ ከማድረግ አንጻር ያላቸው ሚና ከፍተኛ በመሆኑ የክትትል እና ቁጥጥር ሥራ በሚሠሩበት ወቅት ይህንን ታሳቢ አድርገው ኀላፊነታቸውን ሊወጡ እንደሚገባ ተመላክቷል። በተጨማሪም መንግሥት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በሚያውጅበት ወቅት ስለተፈቀዱ የመብት ገደቦች እና ስለማይፈቀዱ የገደብ ዓይነቶች ማብራሪያ እና ውይይት ተደርጓል።
በሌላ በኩል አባላቱ የክትትልና የቁጥጥር ሥራቸውን በሚሠሩበት ወቅት በተለይ በተጠርጣሪዎች እና በታራሚዎች አያያዝ ዙሪያ ለሚደረግ ክትትልና እና ቁጥጥር አጋዥ የሚሆን የሰብአዊ መብቶች የማረጋገጫ መዘርዝሮች (checklist) የተመለከተ ማብራሪያ ተሰጥቷል። በክልሉ የሰብአዊ መብቶች ሁኔታ ላይ ግንዛቤ ለማስጨበጥም በ2015 ዓ.ም. በክልሉ ካሉ ማረሚያ ቤቶችና ፖሊስ ጣቢያዎች መካከል በ24 ማረሚያ ቤቶች እና በ60 ፖሊስ ጣቢያዎች የተሠሩ የክትትል ሥራዎች እና ግኝቶች ከምከረ-ሐሳቦች ጋር ቀርበዋል። ከክትትል ሥራዎች በተጨማሪም በበጀት ዓመቱ የተሠሩ የምርመራ ሥራዎች ከግኝቶች እና ምክረ ሐሳቦች ጋር ቀርበዋል። በተለዩት ግኝቶች በክልሉ በስፋት የሚፈጸሙት የመብቶች ጥሰቶች የአካል ደኅንነት መብት ጥሰት፣ የዘፈቀደ እስር፣ የተራዘመ ቅድመ-ክስ እስር እና ፍትሕ የማግኘት መብቶች ጥሰት እንደሆኑ በገለጻው ተመላክቷል። በተያያዘ በክትትልና ምርመራ ሥራ ወቅት ጽሕፈት ቤቱን ካጋጠሙት ተግዳሮቶች መካከል በከፊል የምክረ-ሐሳቦች በባለድርሻ አካላት አለመፈጸም መሆኑ ተጠቅሷል።
የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ የቀረበው የክትትል እና ምርመራ ግኝት በኮሚቴውም የክትትልና ቁጥጥር ሥራዎች በተወሰነ መልኩ የተስተዋሉ ችግሮች እንደሆኑ አንስተዋል። አክለውም በቀጣይ ከማረሚያ ቤት እና ከፖሊስ ጣቢያ ጋር በተገናኘ ከበጀት ጋር የተያያዙ ችግሮች እንዲቀረፉ የበኩላቸውን ሚና እንደሚወጡና ረቂቅ ሕጎች በሚገመገሙበት ወቅት ከሰብአዊ መብቶች ጋር የተጣጣሙ መሆናቸውን እንደሚከታተሉ አስረድተዋል፡፡ በተጨማሪም ክትትልና ቁጥጥር በሚያደርጉበት ወቅት ከሰብአዊ መብቶች አንጻር የሚሠሩትን ሥራዎች ለመገምገም ትኩረት እደሚያደርጉ በመግለጽ፤ ለአባላትም ወደ መጡበት የምርጫ ክልል ሲመለሱ የሰብአዊ መብቶች ጉዳይ ላይ በሚገባ መሥራት እንዳለባቸው ጥሪ አድርገዋል።
በስልጠናው ማጠቃለያ ላይ የኢሰመኮ ባሕር ዳር ጽ/ቤት ኀላፊ አለባቸው ብርሃኑ እንደተናገሩት የቋሚ ኮሚቴው አባላት የኮሚሽኑን የክትትል እና የምርመራ ግኝቶች በሙሉ ተፈጻሚ ይሆኑ ዘንድ አስፈጻሚው አካል ላይ ተገቢውን ግፊት በማድረግ የበኩላቸውን ሚና እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል።