የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ከሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር እና ከኸልፕኤጅ አንተርናሽናል (HelpAge International) ጋር በመተባበር ለአማራ፣ ለሐረሪ፣ ለሲዳማ እና ለትግራይ ክልሎች እንዲሁም ለአዲስ አበባና ለድሬድዋ ከተማ አስተዳደሮች የማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮዎች እና የአረጋውያን እንክብካቤ ማእከላት፤ በአረጋውያን ሰብአዊ መብቶች እና የሴቶች እና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ባወጣው ‘በተቋም ውስጥ የሚገኙ ደሃና ተጋላጭ ለሆኑ አረጋውያን የድጋፍና እንክብካቤ አገልግሎት አሰጣጥ አነስተኛ ስታንዳርድ’ ዙሪያ ጥቅምት 13 እና 14 ቀን 2016 ዓ.ም. የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና ሰጥቷል።

ስልጠናው የተካሄደው ኢሰመኮ ከግንቦት 23 እስከ ሰኔ 2 ቀን 2014 ዓ.ም. በሦስት ክልሎች በአምስት የአረጋውያን የእንክብካቤ ማእከላት ላይ ያካሄደውን ክትትል ተከትሎ የተቋማቱን አገልግሎት ደረጃ በመመዘን መፍትሔ የሚሹ ጉዳዮችን በመለየት ለሴቶች እና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር እንዲሁም ለሌሎች ባለድርሻ አካላት የሰጠው ምክረ ሐሳብ ላይ ተመሥርቶ ነው፡፡ ለሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ከተሰጡ ምክረ ሐሳቦች መካከል በክልል ለሚገኙ የማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮዎች እና የአረጋውያን እንክብካቤ ማእከላት ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ያወጣውን ‘በተቋም ውስጥ የሚገኙ ደሃና ተጋላጭ ለሆኑ አረጋውያን የድጋፍና እንክብካቤ አገልግሎት አሰጣጥ አነስተኛ ስታንዳርድ’ በተመለከተ የግንዛቤ ማስፋፊያ ሥራ እንዲሠራ እንዲሁም በአነስተኛ ስታንዳርዱ ላይ የተወሰኑ ማሻሻያዎችን እንዲያደርግ የሚሉት ይገኙበታል፡፡

የኢሰመኮ የአካል ጉዳተኞች እና የአረጋውያን መብቶች ሥራ ክፍል ዳይሬክተር ሜቲ አቶምሳ ከስልጠናው ተሳታፊዎች ጋር

በስልጠና መድረኩ አነስተኛ ስታንዳርዱን ለማሻሻል የሚያስችሉ ግብአቶች ከተሳታፊዎች የተሰበሰቡ ሲሆን መድረኩ በተለያዩ የአረጋውያን እንክብካቤ ማእከላት መካከል ያለውን ትስስር ለማጠናከር እና የልምድ ልውውጥ ለማካሄድ ምቹ ሁኔታን ፈጥሯል። አነስተኛ ስታንዳርዱ ከአረጋውያን የእንክብካቤ ማእከላት የሚጠበቀውን ዝቅተኛ አገልግሎት የሚጠቁም፣ በኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ችግሮች ውስጥ የሚገኙ የኅብረተሰብ ክፍሎች በተለይ ደሃና ተጋላጭ የሆኑ አረጋውያን ጥራትና ደረጃውን የጠበቀ የተቋም ድጋፍና እንክብካቤ እንዲያገኙ እና ተሳትፏቸው እንዲጎለብት የሚያስችል ሰነድ ነው፡፡

በመድረኩ ላይ በዋናነት ከተነሱ ርዕሰ ጉዳዮች መካከል አነስተኛ ስታንዳርዱ ላይ በሰፈረው መልኩ ማእከላት ቋሚ የፋይናስ ምንጭ እንዲኖራቸው፣ የማእከላቱን ከባቢያዊ ተደራሽነት ለማሻሻል እንዲሁም በማእከል ለሚገኙ አረጋውያን የጤና አጠባበቅ እና ነጻ የሕግ ድጋፍ አገልግሎት እንዲያገኙ ለማስቻል መንግሥት ድርሻውን እንዲወጣ የሚሉትን ጨምሮ አነስተኛ ስታንዳርዱ በአረጋውያን ላይ ለሚደርስ የመብት ጥሰት ተጠያቂነትን ለማምጣት የሚያስችል እንዲሆን በሚል አስተያየቶች ቀርበው ውይይት ተደርጎባቸዋል፡፡

የኢሰመኮ የሴቶች፣ ሕፃናት፣ አረጋውያን እና አካል ጉዳተኞች መብቶች ኮሚሽነር ርግበ ገብረሐዋሪያ

በራስ ተነሳሽነት ማኅበራዊ ኃላፊነታቸውን ለመወጣት ለአረጋውያን ድጋፍና እንክብካቤ ለመስጠት የተቋቋሙ ማእከላት የተቀላጠፈና ደረጃውን የጠበቀ አገልግሎት መስጠት የሚያስችላቸውና የአረጋውያኑን መብት ለማስጠበቅ እንዲሁም ፍላጎቶቻቸውን ለማሟላት የስታንዳርዱ መዘጋጀት አስፈላጊ መሆኑን የገለጹት የእንክብካቤ ማእከላት ተወካዮች፤ ይህንኑ ለማድረግ ያስችላቸው ዘንድም መንግሥት አስፈላጊውን ትኩረት እና ድጋፍ እንዲያደርግላቸው በተለይም ከአረጋውያን የጤና መድኅን ሽፋን አገልግሎት አንጻር ትኩረት ተሰጥቶ እንዲሠራ ጠይቀዋል።

የኢሰመኮ የሴቶች፣ ሕፃናት፣ አረጋውያን እና አካል ጉዳተኞች መብቶች ኮሚሽነር ርግበ ገብረሐዋሪያ በተለያዩ ቦታዎች የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶች መበራከታቸውን ገልጸው አረጋውያን በዕድሜ ዘመናቸው ላበረከቱት እና ለሚያበረክቱት አስተዋጽዖ ልዩ ትኩረት በመስጠት ለአረጋውያን መብት መጠበቅና መከበር ሁላችንም በጋራ ልንሠራ ይገባል ብለዋል፡፡ አያይዘውም የአረጋውያን እንክብካቤ ማእከላት በብዙ ተግዳሮቶች ውስጥ ሆነው ለአረጋውያን ሰብአዊ መብቶች መጠበቅ ለሚያበረክቱት አስተዋጽዖ ዕውቅና በመስጠት ለማእከላቱ ተወካዮች ምስጋናቸውን አቅርበዋል።