የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ይፋዊ መግለጫ 
ሰኔ 8 ቀን 2014 ዓ.ም.

በየዓመቱ ሰኔ 8 ቀን በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚታሰበውን በአረጋውያን ላይ የሚደርስ ጥቃት የግንዛቤ ማስጨበጫን ቀን ምክንያት በማደረግ በአረጋውያን ላይ የሚደርሰውን ማኅበራዊ መገለል እና አድልዎ ጨምሮ ዘርፈ-ብዙ የሲቪል፣ የፖለቲካ፣ የማኅበራዊ፣ የኢኮኖሚያዊና እና የባሕል መብቶች ጥሰት ዙሪያ ግንዛቤ እንዲኖር ለማድረግ እና ሰብአዊ መብቶቻቸው እንዲጠበቁ፣ እንዲከበሩ እና እንዲሟሉ የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ለሁሉም ባለድርሻ አካላት ጥሪውን ያቀርባል።

በዓለም ባንክ እ.ኤ.አ. የ2019 ሪፖርት መሰረት በኢትዮጵያ 6.8 ሚሊዮን ዕድሜያቸው 60 ዓመትና ከዚያ በላይ የሆኑ አረጋውያን ያሉ ሲሆን፤ 23 በመቶ የሚሆኑት ደግሞ ለልዩ ልዩ ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ አካባቢያዊ እና ባሕላዊ ችግሮች ተጋላጭ ናቸው፡፡ 

አረጋውያን ሰብአዊ ክብራቸው ተጠብቆና በቂ የኑሮ ደረጃ፣ የተሟላ የጤና አገልግሎት የማግኘት፣ እንዲሁም በተለያዩ ማኅበራዊ እንቅስቃሴዎች ላይ የመሳተፍ መብቶች ያላቸው ቢሆንም፤ በተግባር ግን በርካታ ተግዳሮቶች ይገጥሟቸዋል፡፡ መሰረታዊ ፍላጎታቸው ያልተሟላላቸው፣ በተለያዩ የጤና ችግሮች የሚሰቃዩ፣ ገቢ የሌላቸው እና በማኅበራዊ ዋስትና አገልግሎት እጦት በየጎዳናው የወደቁ አረጋውያን አሉ፡፡ 

ሴት አረጋውያን ከእነዚህ ችግሮች በተጨማሪ፤ ከጾታ ጋር በተያያዘ ተደራራቢ ለሆኑ የመብት ጥሰቶች የተጋለጡ በመሆናቸው ወሲባዊ ጥቃቶችን ጨምሮ ጾታን መሰረት ካደረጉ መድሎዎች እና ጥቃቶች ልዩ ጥበቃ ሊደረግላቸው እንደሚገባ የአፍሪካ የሰዎችና የሕዝቦች መብቶች ቻርተር የአፍሪካ ሴቶች መብቶች ፕሮቶኮል ይደነግጋል። ኢትዮጵያም ይህን ስምምነት መጋቢት 21 ቀን 2010 ዓ.ም. ማጽደቋ እና ሴት አረጋውያን ከተለያዩ ጾታን መሰረት ያደረጉ መድሎዎች እና ጥቃቶች የመጠበቅ መብታቸው የተደነገገ ቢሆንም፤ ወሲባዊ ጥቃቶች፣ ኢኮኖሚያዊ ጥቃቶች፣ የቤት ውስጥ ጥቃትና ሌሎችም በደሎች በቤተሰብ እና እንክባካቤ ሊያደርጉላቸው በሚገባቸው የቅርብ ሰዎች ጭምር ይፈጸሙባቸዋል። ከዚህም የተነሳ ለአካላዊ፣ ሥነልቦናዊ፣ ወሲባዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ማኅበራዊ ጉዳቶች ይዳረጋሉ።

በጡረታ የሚሰናበቱ አረጋውያን በቂ የሆነ የጡረታ አበል የማግኘት መብት ያላቸው ቢሆንም፤ የጡረታ ክፍያ የሀገሪቱን ኢኮኖሚያዊ እና ማኅበራዊ ሁኔታ ጋር በተጣጣመ መልኩ በየጊዜው ማሻሻያ የሚደረግበት ባለመሆኑ ምክንያት በጡረታ ገቢ ለሚተዳደሩ አረጋውያን የኑሮ ውድነት ለተደራራቢ ችግሮች ያላቸውን ተጋላጭነት የከፋ ያደርገዋል፡፡

በተለያዩ የኢትዮጵያ ክልሎች በተከሰቱ የጦርነት እና የግጭት ሁኔታዎችም ሆነ ተፈጥሯዊ አደጋዎች ወቅት አረጋውያን ለልዩ ልዩ የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶች ተጋላጭ ሆነዋል፡፡ በተለይም በትግራይ ክልል ተጀምሮ ወደ አጎራባች የአፋር እና የአማራ ክልሎች የተወሰኑ ቦታዎች ተስፋፍቶ በቆየው ጦርነት፤ ሲቪል አረጋውያን ተገቢውን ጥበቃ ሳያገኙ በመቅረታቸው ከፍርድ ውጪ ለሆነ ግድያ፣ ለዘፈቀደ እስራት፣ ለንብረት ዘረፋና ውድመት እንዲሁም ከመኖሪያ አካባቢ የመፈናቀል ጥሰቶች የተፈጸመባቸው ስለመሆኑ ኢሰመኮ በተለያዩ ጊዜያት ይፋ ያደረጋቸው ሪፖርቶች ያመላክታሉ፡፡ እነዚህ የመብት ጥሰቶች ሴት አረጋውያን ላይ ያላቸው ተጽዕኖ ከፍተኛ ከመሆኑም በተጨማሪ፣ ሴት አረጋውያን በእነዚህ የጦርነትና የግጭት አውድ ውስጥ አስገድዶ መደፈርን ጨምሮ ጾታዊ ጥቃቶች እንደተፈጸሙባቸው በሪፖርቶቹ ተመልክቷል፡፡

በአስቸጋሪ የኑሮ ሁኔታ ውስጥ የሚገኙ አረጋውያን ዘላቂ የሆነ የማኅበራዊ ጥበቃ የሚያገኙበትን ሥርዓት መዘርጋትና የአረጋውያን ሰብአዊ መብቶችን ማክበር፣ በትጥቅ ግጭቶች ወቅት አረጋውያን ሲቪሎች ጥበቃ እንዲያገኙ፣ ከወታደራዊ ዒላማዎች አካባቢ እንዲርቁ፣ እንዲሁም በእስር፣ በመጠለያ ጣቢያ የሚገኙ አረጋውያን ልዩ ትኩረት እንዲያገኙ እና የሰብአዊ እርዳታ ተግባራት የአረጋውያንን ጥበቃ እና ልዩ ፍላጎቶቻቸውን ያካተተ መሆኑን ማረጋገጥ የመንግሥት ኃላፊነት ነው፡፡

በኢሰመኮ የሴቶች እና ሕፃናት መብቶች ኮሚሽነር መስከረም ገስጥ እንዳሉት “ሴቶች ከሕፃንነት ዕድሜ ጀምሮ የሚያጋጥማቸው ስር የሰደደ የጾታ ኢ-ፍትሐዊነት፤ በአረጋዊነት ዕድሜም እየተባባሰ የሚሄድ በመሆኑ፣ ሴት አረጋውያን ከጾታ ጋር ተደራራቢ ለሆኑ ዘርፈ ብዙ የመብት ጥሰቶች ይጋለጣሉ።’’ ኮሚሽነር መስከረም አክለውም “አካል ጉዳተኛ አረጋውያን ሴቶች ደግሞ ለተደራራቢ የመብት ጥሰቶች ተጋላጭ ናቸው’’ ብለዋል፡፡ 

እንዲሁም በኢሰመኮ የአካል ጉዳተኞች እና አረጋውያን መብቶች ኮሚሽነር ርግበ ገብረሐዋርያ በበኩላቸው “ይህንን ዓለም አቀፍ የግንዛቤ ማስጨበጫ ቀን ታስቦ የሚውለው አረጋውያን እየደረሱባቸው ያሉትን ዘርፈ ብዙ የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶች ለመፍታት መንግሥት ልዩ ጥበቃ የሚሰጡ ሕጎችና ፖሊሲዎችን በማውጣትና ተፈጻሚነታቸውንም ለማረጋገጥ የሚያስችሉ እርምጃዎችን በመውሰድ ሊሆን ይገባል” በማለት ጥሪ አቅርበዋል፡፡