የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) የሴት ልጅ ግርዛትን አስመልክቶ በሐረሪ እና ሶማሊ ክልሎች ለሚያካሂደው ግልጽ የአቤቱታ መቀበያ መድረክ (Public Hearing) የባለድርሻ አካላትን ግንዛቤ ለማሳደግ እና ትብብሮችን ለማጠናከር ያለመ ውይይት ኅዳር 9 ቀን 2018 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ከተማ አካሂዷል። በውይይቱ የፌዴራል እና የሁለቱ ክልሎች መንግሥታዊ ተቋማት፣ በሴት ልጅ ግርዛት ዙሪያ የሚሠሩ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች እና የሃይማኖት ተቋማት ተወካዮች ተሳትፈዋል፡፡

በመድረኩ የግልጽ አቤቱታ ቅበላ (Public Hearing) ምንነት እና ዓላማ፣ የሴት ልጅ ግርዛትን በግልጽ የአቤቱታ ቅበላ መድረክ አማካኝነት የመመርመር አስፈላጊነት፣ በሐረሪ እና ሶማሊ ክልሎች ያለው የሴት ልጅ ግርዛት ሁኔታ እንዲሁም የባለድርሻ አካላት ሚና ቀርቦ ውይይት ተደርጎበታል፡፡ በውይይቱ የተሳተፉ ባለድርሻ አካላት የሴት ልጅ ግርዛትን በተመለከተ እያከናወኗቸው የሚገኙ ሥራዎችን የገለጹ ሲሆን፣ በግልጽ የአቤቱታ ቅበላ ሂደቱ ሊያከናውኗቸው የሚገቡ ተግባራትን በመለየት በጋራ እና በተናጠል ለመሥራት ስምምነት ላይ ደርሰዋል፡፡


የውይይቱ ተሳታፊዎቹ የሴት ልጅ ግርዛት በሁለቱ ክልሎች በስፋት እየተፈጸመ የሚገኝ ጎጂ ልማዳዊ ድርጊት መሆኑን ጠቅሰው፣ በየአካባቢው ያለው የግርዛት ዐይነት፣ መጠን እና የማኅበረሰብ አረዳድ እንደሚለያይ ገልጸዋል። በተለይም ይህ ጎጂ ልማዳዊ ድርጊት ከሚያስከትለው የጤና ችግር ባሻገር የወንጀል ተጠያቂነትን የሚያመጣ እንደሆነ ለማኅበረሰቡ በቂ ግንዛቤ የመፍጠር ሥራ በስፋት አለመከናወኑና ለጉዳዩ መፍትሔ ለመስጠት በሚተገበሩ ሥራዎች ውስጥ የወንዶች ተሳትፎ ውስን መሆን ችግሩን ለመቀነስ የሚደረጉ ጥረቶች ውጤታማ እንዳይሆኑ እክል መፍጠሩን አንስተዋል። ድርጊቱን ለማስቆም ባለድርሻ አካላት የግንዛቤ ማሳደግ ሥራዎችን ጨምሮ በርካታ ተግባራትን እያከናወኑ መሆኑን ሆኖም ተጠያቂነትን በማረጋገጥ ረገድ ውጤታማ ሥራዎች ባለመሠራታቸው በቂ ውጤት ማምጣት አለመቻሉን በማንሳት፣ ኢሰመኮ ሊያከናውን ያቀደው ግልጽ የአቤቱታ መቀበያ መድረክ በዚህ ረገድ ቁልፍ አስተዋጽዖ እንደሚኖረው ገልጸዋል።

የኢሰመኮ የሲቪል፣ የፖለቲካ፣ የማኅበራዊ እና የኢኮኖሚ መብቶች ኮሚሽነር
የኢሰመኮ የሲቪል፣ የፖለቲካ፣ የማኅበራዊ እና የኢኮኖሚ መብቶች ኮሚሽነር ዶ/ር አብዲ ጅብሪል የሴት ልጅ ግርዛት ከጤና ጉዳት በተጨማሪ ሌሎች ዘርፈ ብዙ የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶችን የሚያስከትል፣ በፈጻሚዎችም ላይ የወንጀል ተጠያቂነትን የሚያመጣ መሆኑን ጠቅሰው፣ ድርጊቱን ለማስቆም ከግንዛቤ ማሳደጊያ ሥራዎች ጎን ለጎን ተጠያቂነትን ለማረጋገጥ በቂ ጥረት ሊደረግ እንደሚገባ ገልጸዋል፡፡ አክለውም የሴት ልጅ ግርዛትን አስመልክቶ ኢሰመኮ በሐረሪ እና ሶማሊ ክልሎች በሚያካሂደው ግልጽ የአቤቱታ መቀበያ መድረክ (Public Hearing) ላይ ሁሉም መንግሥታዊ እና መንግሥታዊ ያልሆኑ ባለድርሻ አካላት በንቃት እንዲሳተፉ እና እገዛ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል።