በመገናኛ ብዙኃን አማካኝነት ተፈጽሟል የሚባል ወንጀል እና ቅድመ ክስ እስር (Allegations of offence committed through media and pre-trial detention)

የቅድመ ክስ ወይም ቅድመ ፍርድ እስር (Pre-trial detention) ምን ማለት ነው?

አንድ በወንጀል የተጠረጠረን ሰው ፖሊስ በቁጥጥር ስር አውሎ የወንጀል ምርመራ የሚያካሂድበት ጊዜ የቅድመ ክስ ወይም ቅድመ ፍርድ እስር (pre-trial detention) ይባላል። የዚህ ዓይነቱ የቅድመ ክስ እስር በፌዴራሉ ሕገ መንግሥትና በወንጀል ሥነ ሥርዓት ሕግ መሰረት በፍርድ ቤት ትዕዛዝ ብቻ የሚፈቀድ ሲሆን፤ ፖሊስ ለምን ተጠርጣሪው በእስር ቆይቶ ምርመራ ሊደረግ እንደሚገባ ለፍርድ ቤት እያስረዳ፣ ፍርድ ቤቱም ምክንያቱን ከተቀበለው ፖሊስ የወንጀል ምርመራውን እስኪያጠናቅቅ ድረስ ተጠርጣሪው በእስር እንዲቆይ ፍርድ ቤት ሊፈቅድ ይችላል፡፡ 

ይህ በተለምዶ አጠራር የጊዜ ቀጠሮ የሚባለው የቅድመ ክስ እስር በፍርድ ቤት ቁጥጥርና እይታ ውስጥ መፈጸም ያለበት ሲሆን፤ ፍርድ ቤቱ ፖሊስ እያደረገ ያለውን የወንጀል ምርመራና የተጠርጣሪውን እስር ሁኔታ ለመከታተል፤ እስከ 15 ቀን ሊደርስ የሚችል የጊዜ ቀጠሮ እየሰጠ የፖሊስን የወንጀል ምርመራ ሂደት ይቆጣጠራል፡፡ ፖሊስ የወንጀል ምርመራውን ለማጠናቀቅ እና እንደ አስፈላጊነቱም ክስ ለመመስረት በቂ ጊዜ እንዳገኘ ፍርድ ቤቱ ካረጋገጠ በኃላ ወይም ተጠርጣሪው ከዚህ የበለጠ በእስር ሊቆይ አይገባም ብሎ ፍርድ ቤቱ ካመነ ታሳሪው በነጻ ወይም በዋስትና ከእስር እንዲለቀቅ ሊወስን ይችላል፡፡ 

የቅድመ ክስ እስር የሚፈቀድባቸው ሁኔታዎች ምንድን ናቸው?

የቅድመ ክስ እስር የወንጀል ምርመራ ሥራን ለማጠናቀቅ ሲባል በፍርድ ቤት ትዕዛዝ ብቻ የሚፈጸም እስር ሲሆን፤ ፍርድ ቤቶች ግን የቅድመ ክስ እስር ወይም የጊዜ ቀጠሮ ከመፍቀዳቸው በፊት በተለይ ከዚህ በታች የተመለከቱትን ነጥቦች ከግምት በማስገባት ይወስናሉ፡፡ እነዚህም፡-

  • ተጠርጣሪው ፈጽሟል የተባለውን የወንጀል ዓይነት፣ ክብደት፣ እና ክስ ቢቀርብ ሊሰጥ የሚችለው የቅጣት ዓይነትና መጠን፣
  • የወንጀል ምርመራውን ለማካሄድ የተጠርጣሪው በእስር መቆየት አስፈላጊነት መጠን፣
  • ተጠርጣሪው በወንጀል ምርመራ ሥራ ላይ ሊፈጥረው የሚችለው ማደናቀፍ፣
  • የተጠርጣሪው ሊጠፋ መቻል፣
  • ተጠርጣሪው በእስር ባይቆይ ሌላ ወንጀል ሊፈጽም የሚችል መሆኑ የሚሉት ናቸው።

ፍርድ ቤቱ እነዚህንና ተዛማጅ ጥያቄዎችን፣ የተጠርጣሪውን ታሳሪና የቤተሰብ ሁኔታ እና አጠቃላይ የነገሩን ሁኔታ በማገናዘብ ተገቢ ሆኖ ያገኘውን የተጨማሪ ጊዜ ቀጠሮ ሊፈቅድ ወይም ሊከለክል፣ ወይም ታሳሪው በዋስትና እንዲለቀቅ ሊወስን ይችላል፡፡

በፌዴራል ሕገ መንግሥቱ ላይ በግልጽ እንደተደነገገውና ከዚህ በላይ እንደተገለጸው ፍትሕ እንዳይጓደል ሁኔታው የሚጠይቅ ከሆነ ብቻ ፍርድ ቤቱ የተያዘው ሰው በጥበቃ ስር እንዲቆይ ለማዘዝ፣ ወይም ምርመራ ለማካሄድ ተጨማሪ ጊዜ ሲጠየቅ አስፈላጊ በሆነ መጠን ብቻ ተጠርጣሪው በእስር እንዲቆይ ሊፈቅድ ይችላል፡፡ 

በሰብአዊ መብቶች መርሆች መሰረት የተራዘመ የቅድመ ክስ እስር (prolonged pre-trial detention) ለብዙ ዓይነት የሰብአዊ መብቶች ጥሰት የሚያጋልጥ በመሆኑ፤ ፍርድ ቤቶች የተራዘመ የቅድመ ክስ እስር እንዳይፈቅዱ ይመከራል፡፡

የቅድመ ክስ እስርና በተለይም የተራዘመ የቅድመ ክስ እስር የተከሰሱና የተያዙ ሰዎችን መብቶች፣ በተለይም የሰዎችን የአካል ደኅንነት መብት፣ የነፃነት መብት፣ ከኢሰብአዊ አያያዝ የመጠበቅ መብት፣ እና በፍርድ ሂደት ውስጥ እያሉ እንደጥፋተኛ ያለመቆጠር መብትን ሊጥስ የሚችል በመሆኑ፤ ፍትሕ እንዳይጓደል የግድ አስፈላጊ ካልሆነ በስተቀር ሊወገድ የሚገባ ሲሆን፤ በተለይ የተራዘመ የቅድመ ክስ እስር የወንጀል ፍትሕ አስተዳደር አካላት በሙሉ እና በተለይም ፍርድ ቤቶች ሊከላከሉት የሚገባ ነው፡፡ 

በመገናኛ ብዙኃን አማካኝነት ተፈጽሟል ለሚባል ወንጀል የቅድመ ክስ እስር ይፈቀዳል?

አጭሩ መልስ አይፈቀድም ነው፤ ዝርዝሩ እንደሚከተለው ነው፡፡

በቅርቡ በጸደቀው የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን አዋጅ ቁጥር 1238/2013 አንቀጽ 86(1) ላይ በግልጽ እንደተደነገገው “በመገናኛ ብዙኃን አማካኝነት የወንጀል ድርጊት በመፈጸም የተጠረጠረ ማንኛውም ሰው ወይም አካል በወንጀል ሥነ ሥርዓት ሕግ ድንጋጌዎች መሰረት ለተጨማሪ ምርመራ በእስር እንዲቆይ ሳይደረግ ክሱ በቀጥታ በዐቃቤ ሕግ አማካኝነት ለፍርድ ቤት መቅረብ አለበት፡፡”

የመገናኛ ብዙኃን አዋጅ ይህን ልዩ ጥበቃ (special protection) የፈቀደው ወይም የቅድመ ክስ እስር ክልከላ (prohibition of pre-trial detention) የደነገገው፣ በተለይ በአዋጁ መሰረት በሚዲያ ተቋምነት ተመዝግበውና የሕግ እውቅና አግኝተው ለሚሠሩ ጋዜጠኞች ወይም የሚዲያ ሠራተኞች እና ከዚያ አልፎም በአጠቃላይ ለሚዲያ ነፃነትና ሃሳብን በነፃነት ለመግለጽ መብት የተደረገ ጥበቃ በመሆኑ፤ ለተመዘገቡም ሆነ ላልተመዘገቡ የሚዲያ ሠራተኞች ብሎም ለማናቸውም ሃሳብን በነፃነት መግለጽ ላይ ለተሰማራ ሰው ተፈጻሚ እንዲሆን ነው። 

በመገናኛ ብዙኃን አዋጅ መሰረት “ሚዲያ” ወይም “የመገናኛ ብዙኃን” ማለት በየጊዜው የሚወጣ ሕትመት (periodicals)፣ የብሮድካስት አገልግሎትና የበይነ መረብ ሚዲያን የሚጨምር ሲሆን፤ ከእነዚህ ውስጥ በየጊዜው የሚወጣ ሕትመት እና የበይነ መረብ ሚዲያ የግድ መመዝገብ የማያስፈልገው የሚዲያ ዓይነት በመሆኑ፤ በአዋጁ አንቀጽ 86(1) የተመለከተው ጥበቃ ከአዋጁ አንቀጽ 3(1) እና 6(3) ጋርም ተቀናጅቶ ሲነበብ ለተመዘገበ ሚዲያ ብቻ ሳይሆን ለሁሉም ዓይነት ሚዲያዎች የተቀመጠ የሕግ ጥበቃ መሆኑን የሚያመለክት ነው፡፡

ይህ ልዩ ጥበቃ ለምን አስፈለገ?

የመገናኛ ብዙኃን አዋጅ ይህን ልዩ ጥበቃ (special protection) የፈቀደው ወይም የቅድመ ክስ እስር ክልከላ (prohibition of pre-trial detention) ለሚዲያና ብሎም ማናቸውም ሃሳብን በነፃነት የመግለጽ መብት ለተሰማሩ ሰዎች ከደነገገበት ምክንያቶች ውስጥ፡-

  • በኢትዮጵያ ፌዴራል ሕገ መንግሥት አንቀጽ 29(3) እና (4) መሰረት ሚዲያ በተቋምነቱ የሕግ ጥበቃ እንደሚደረግለት በግልጽ በመደንገጉ፣
  • በዲሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ውስጥ ሃሳብን በነፃነት መግለጽና የሚዲያ ነፃነት፣ ሃሳቦችና አመለካከቶች በነፃ መንሸራሸራቸው እንዲሁም የሚዲያ ሠራተኞች ተገቢ ካልሆነ ቁጥጥርና ተጽዕኖ ነፃ ሆነው መሥራታቸውን ማረጋገጥ አስፈላጊ ስለሆነ፣
  • በሚዲያ አማካኝነት ተፈጽሟል ለሚባል ወንጀል ተፈጸመ የሚባለው ተግባር በጽሑፍ፣ በድምጽ ወይም በምስል ተቀርጾ የሚገኝ በመሆኑ ድርጊቱ የሚያስከስስ ከሆነ በቀጥታ ክሱ ከሚቀርብ በስተቀር ለተጨማሪ ምርመራ በሚል ምክንያት ሰው በእስር እንዲቆይ የሚያስፈልግበት ምንም ምክንያት ባለመኖሩ እና   
  • በኢትዮጵያ የቅርብ ጊዜ ጨቋኝ የፖለቲካ ታሪክ በተለይ በሚዲያ ላይ አነጣጥሮ የነበረው ፖለቲካዊ ጥቃት እንደመሳሪያ ሲጠቀም የነበረው ለተጨማሪ የወንጀል ምርመራ በሚል ምክንያት የሚዲያ ሠራተኞችን ለተራዘመ የቅድመ ክስ እስር መዳረግ የነበረ በመሆኑ የሚሉት ዋነኞቹ ናቸው። 

አዲሱ የመገናኛ ብዙኃን አዋጅ ያለፈውን ብልሹ አሠራር እንዳይቀጥል ለመከላከል፣ ለሚዲያ ነፃነትና ሃሳብን በነፃነት የመግለጽ መብት የተሟላ የሕግ ጥበቃ ለማድረግ እና የዲሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ በተገቢው መንገድ ለማገዝ በመገናኛ ብዙኃን አማካኝነት ተፈጽሟል ለሚባል ወንጀል በዐቃቤ ሕግ በኩል በቀጥታ ክስ ሊቀርብ የሚችል ከመሆኑ በስተቀር በወንጀል ሥነ ሥርዓት ሕግ መሰረት የምርመራ ጊዜ እስር ወይም የቅድመ ክስ እስር ሙሉ በሙሉ የተከለከለ መሆኑን በግልጽ ደንግጓል፡፡ 

ስለሆነም በመገናኛ ብዙኃን (ሚዲያ) አማካኝነት የወንጀል ድርጊት በመፈጸም የተጠረጠረ ማንኛውም ሰው ወይም ጋዜጠኛ ወይም የሚዲያ ሠራተኛ የወንጀል ምርመራ ለማካሄድ ወይም ለማጠናቀቅ በሚል ምክንያት ሊታሰር የማይችል ሲሆን፤ በዚህ ዓይነት ሁኔታ የተፈጸመን እስር ፍርድ ቤቶች ሊከላከሉ እና አላግባብ የታሰሩ ሰዎችን ነፃነት ሊያረጋግጡ ይገባል፡፡