የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) በማኅበራዊ መገናኛ ብዙኃን በመዘዋወር ላይ የሚገኘውን እና በርካታ ሰዎች ከመኪና እንዲወርዱ በማድረግ በጅምላ ሲገደሉ የሚያሳየውን ተንቀሳቃሽ ምስል ሁኔታ መርምሯል። በተንቀሳቃሽ ምስሉ ላይ የሚታየው ከሕግ ውጭ የተፈጸመ የግድያ ድርጊት (Extra-judicial killings) ኢሰመኮ መጋቢት 2 ቀን 2014 ዓ.ም. “በኢትዮጵያ የአፋር እና የአማራ ክልሎች የተፈጸሙ የሰብአዊ መብቶች እና የዓለም አቀፍ የሰብአዊነት ሕግ ጥሰቶች ላይ የተደረገ ምርመራ ሪፖርት”  በሚል ርዕስ ባወጣው ሪፖርት ውስጥ ከተዘረዘሩት ክስተቶች ውስጥ አንዱ መሆኑን ተረድቷል። 

በዚሁ የኢሰመኮ የምርምራ ሪፖርት ከምስክሮች እና በስፍራው በመገኘት በመስክ ምልከታ ያሰባሰበውን መረጃ መሰረት በማድረግ፣ ድርጊቱ በአማራ ክልል የኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር ዞን ደዋ ጨፋ ወረዳ ልዩ ቦታው እንቶሊ አካባቢ በታኅሣሥ ወር 2014 ዓ.ም. የመጀመሪያ ሳምንት (ቀኑ በትክክል ያልታወቀ) መፈጸሙን፤ እንዲሁም በወቅቱ በነበረው መረጃ መሰረት የመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች በሁለት የጭነት መኪኖች ጭነው ያመጡዋቸውን እና ወደ 30 የሚጠጉ የኦነግ ሸኔ አባሎች ናቸው ያሏቸውን ሰዎች በጅምላ በጥይት ደብድበው መግደላቸውን ይገልጻል። 

ኢሰመኮ ተንቀሳቃሽ ምስሉን ከተመለከተ በኋላ ባደረገው ተጨማሪ ማጣራትና የቴክኒክ ምርመራ፣ በመስክ ምርመራ በለየው ስፍራና በተንቀሳቃሽ ምስሉ ላይ ያለውን ስፍራ በቴክኒክ ምርመራ በማነጻጸር፣ እንዲሁም ምስሉ የተቀረጸበትን ቦታ ለማነጻጸርና ለማረጋገጥ የሚያስችሉ የቴክኒክ ምርመራዎችን በማድረግ፤ ከዚህ በላይ የተገለጸው በኢሰመኮ ምርመራ የተዘገበው ከፍርድ ውጭ የተፈጸመ የግድያ ድርጊት የሚያመለክት ተጨማሪ ማስረጃ ስለመሆኑ በምክንያታዊ አሳማኝነት አረጋግጧል፡፡

ስለሆነም ኢሰመኮ ከዚህ ቀደም ባቀረበው ምክረ ሃሳብ መሰረት የተሟላ የወንጀል ምርመራ ተደርጎ ተጠያቂነት እንዲረጋገጥ በድጋሚ ያሳስባል።