የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) በምግብ ሥርዓት፣ ምግብ የማግኘት መብት እና ሰብአዊ መብቶችን መሠረት ያደረገ አቀራረብ (human rights-based approach) ዙሪያ በሦስት ክልሎች የስልጠና መድረኮች አካሂዷል፡፡ በሦስቱ ዙሮች ለፌዴራል ደረጃ ባለድርሻ አካላት ከነሐሴ 3 እስከ 5 ቀን 2015 ዓ.ም.፣ በኦሮሚያ ክልል ለሚገኙ ባለድርሻ አካላት ከነሐሴ 30 እስከ ጳጉሜን 2 ቀን 2015 ዓ.ም. እና በሲዳማ ክልል ለሚገኙ ባለድርሻ አካላት ከመስከረም 28 እስከ 30 ቀን 2016 ዓ.ም. ተከናውኗል። በስልጠናዎቹ ከግብርና፣ ከጤና፣ ከዕቅድ እና ልማት እንዲሁም ከፋይናንስ ዘርፍ አስፈጻሚዎች የተውጣጡ ተሳታፊዎችን ጨምሮ ሌሎች የሚመለከታቸው መንግሥታዊ እና መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማት ተወካዮች ተሳትፈዋል፡፡
የስልጠና መድረኮቹ ኢንተርናሽናል ኢንስቲትዩት ፎር ሩራል ሪኮንስትራክሽን (International Institute for Rural Reconstruction) ከተባለ ተቋም ጋር በመተባበር የተዘጋጁ ሲሆን በመድረኮቹ ኢሰመኮ በቂ ምግብ የማግኘት መብትን እና ሰብአዊ መብቶችን መሠረት ያደረገ አቀራረብን በተመለከተ ገለጻ አድርጓል። በስልጠናዎቹ የሰብአዊ መብቶች ምንነት፣ በቂ ምግብ የማግኘት መብት፣ የሰብአዊ መብቶች እና የምግብ ሥርዓት ግንኙነት እና ተያያዥ የሕግ ማዕቀፎች እንዲሁም በምግብ ሥርዓት ውስጥ ሰብአዊ መብቶችን መሠረት ያደረገ አቀራረብ የመከተል አስፈላጊነት ላይ ሰፊ ውይይት ተካሂዷል፡፡
በተመሳሳይ ምግብ የማግኘት መብትን በተመለከተ በመጠን እና በጥራት በቂ የሆነ የተመጣጠነ፣ ደኅንነቱ የተጠበቀ እና ከብክለት የጸዳ እንዲሁም በተጠቃሚው ባህል ተቀባይነት ያለው ምግብ ማግኘት እና ዘለቄታዊ ተደራሽነትን በተመለከተ ማብራሪያ ቀርቦ የሚስተዋሉ ተግዳሮቶች እና መልካም አጋጣሚዎች ላይ ውይይት ተካሂዷል፡፡ የስልጠናው ተሳታፊዎች ከማሳ እስከ ገበታ ባለው የምግብ ሥርዓት ውስጥ ያሉ መንግሥታዊ እና መንግሥታዊ ያልሆኑ ባለድርሻ አካላትን፣ በሥርዓቱ ውስጥ ለመብቶች ጥሰት ተጋላጭ የሆኑ የማኅበረሰብ ክፍሎችን እንዲሁም ሊጣሱ የሚችሉ መብቶችን የመለየት ሥራ አካሂደዋል፡፡ በስልጠና መድረኮቹ በምግብ ሥርዓት ውስጥ ሰብአዊ መብቶችን መሠረት ያደረገ አቀራረብ ዋና ዋና መርሖች፣ አስፈላጊነት እና በመርኃ ግብሮችና ፕሮጀክቶች ውስጥ ማካተት የሚቻልበትን ሂደት በተመለከተ ውይይት ተደርጓል፡፡ ተሳታፊዎች ከማሳ እስከ ገበታ በምግብ ሥርዓት ውስጥ የሚስተዋሉ የመብት ጥሰቶችን መቅረፍ የሚቻልበትን መንገድ እና በቂ ምግብ የማግኘት መብትን ለማረጋገጥ የእያንዳንዱን ባለድርሻ አካል ሚና በተመለከተ አስተያየት ሰጥተዋል።