የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ትኩረታቸውን በሰብአዊ መብቶች ላይ አድርገው ከሚንቀሳቀሱ ሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ጋር በአጋርነት የሚሠራበትን “የኢሰመኮ-ሲቪል ማኅበራት የትብብር መድረክ” አጠናክሮ ለማስቀጠል ያለመ ውይይት የካቲት 20 ቀን 2017 ዓ.ም. በዋና መሥሪያ ቤቱ አካሂዷል። በውይይት መድረኩ በሴቶች እና በሕፃናት፣ በአካል ጉዳተኞች እና በአረጋውያን፣ በነጻ የሕግ ድጋፍ አገልግሎት፣ በመገናኛ ብዙኃን እና በሌሎች የሰብአዊ መብቶች ጉዳዮች ላይ የሚሠሩ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ኃላፊዎች እና ተወካዮች ተገኝተዋል።

መድረኩ የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር ብርሃኑ አዴሎን ከድርጅቶቹ ተወካዮች እና ኃላፊዎች ጋር ያስተዋወቀ ሲሆን ኢሰመኮ ከሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ጋር ሊኖረው የሚገባውን የትብብር ሥራ በተደራጀ እና ሥርዓት ባለው መልኩ ለመምራት ባዘጋጀው የስትራቴጂክ አጋርነት መምሪያ (Strategic Partnership Guideline) መሠረት ሲሠራባቸው የቆዩ ዘርፎችን በተመለከተ ማብራሪያ ቀርቧል።
የውይይቱ ተሳታፊዎች ለዋና ኮሚሽነሩ መልካም የሥራ ዘመን እንዲሆንላቸው ተመኝተው ኢሰመኮ ከሲቪል ማኅበራት ጋር ቀድሞ የጀመረውን የትብብር መድረክ እንዲያጠናክር፣ በረቂቅ ደረጃ የሚገኘው የተጠቃለለ የአካል ጉዳተኞች አዋጅ እንዲጸድቅ፣ የምልክት ቋንቋ የሥራ ቋንቋ እንዲሆን ተገቢውን ጥረት እንዲያደርግ፣ የሲቪልና የፖለቲካ መብቶች እንዲከበሩ ትኩረት ሰጥቶ ሊሠራባቸው ይገባል ያሏቸውን ሐሳቦች አቅርበዋል። የሴቶችና የሕፃናት መብቶችን ጨምሮ የአረጋውያን መብቶች እንዲከበሩ ኢሰመኮ በዘርፉ ከሚንቀሳቀሱ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ጋር በተሻለ ቅንጅት እና ትብብር እንዲሠራ ጥያቄ ቀርቧል።

ኢሰመኮ የሰብአዊ መብቶች ሁኔታ ክትትልና ምርመራ የማድረግ፣ ግኝቶችን መሠረት ያደረገ ምክረ ሐሳብ የማቅረብ እና በባለድርሻ አካላት እንዲፈጸሙ ውትወታ የማድረግ ሥልጣንና ኃላፊነት በሕግ የተሰጠው መሆኑን በማመላከት፤ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ለምክረ ሐሳቦቹ መፈጸም ምቹ ሁኔታን በሚፈጥሩ እና በየትኛውም ዘርፍ ሰብአዊ መብቶችን በሚያስፋፉ ተግባራት ላይ አስተዋጽዖ ማድረግ እንዳለባቸው ተገልጿል።
የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር ብርሃኑ አዴሎ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶቹ ኢሰመኮ ትኩረት ሰጥቶ እንዲሠራባቸው ያቀረቧቸውን ሐሳቦች ተቀብለው፤ “ኢሰመኮ ተቋማዊ ነጻነቱንና ገለልተኝነቱን ባከበረ መንገድ በአዋጅ የተሰጡትን ተልዕኮዎች በአግባቡ ለመፈጸም በልዩ ልዩ የሰብአዊ መብቶች ጉዳዮች ላይ ከሚሠሩ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ጋር በትብብርና በቅንጅት መሥራቱን አጠናክሮ ይቀጥላል” ብለዋል።