በዚህ ዓመት “ማንም ተጎጂ ወደኋላ ሳይተው በሰው የመነገድ ወንጀል ለተጎዱ ሁሉ ተደራሽ መሆን” (Reach Every Victim of Trafficking, Leave No One Behind) በሚል መሪ ቃል በሰው የመነገድ ወንጀልን ለመከላከል በዓለም አቀፍ ደረጃ በየዓመቱ እ.ኤ.አ. ሐምሌ 30 የሚታሰበውን ቀን አስመልክቶ የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ለወንጀሉ ተጎጂዎች የሚቀርበው ጥበቃ እና ድጋፍ ሰብአዊ መብቶቻቸውን መሠረት ያደረገ እንዲሆን ተገቢው እርምጃ እንዲወሰድ ያሳስባል።

በዓለም አቀፍ ደረጃ ይህንን የሰብአዊ መብቶች ጥሰት ለመከላከል፣ ለመግታት እና ወንጀለኞችን ለመክሰስና ለማስቀጣት የተዘጋጀው ሰነድ የፓሌርሞ ፕሮቶኮል (Palermo Protocol) ወይም በሙሉ መጠሪያው በሰዎች በተለይም በሴቶችና ሕፃናት ላይ የሚደርሰውን በሰው የመነገድ ወንጀል ለመከላከል፣ ለመግታትና ለመቅጣት የወጣ ፕሮቶኮል በመባል የሚታወቅ ሲሆን፣ ሰነዱ የተዘጋጀውም በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ነው፡፡ የፕሮቶኮሉ አንቀጽ 3 በሰው የመነገድ ወንጀል ማለት ግለሰቦችን ለብዝበዛ በማስገደድ፣ በመጥለፍ፣ በማታለል ወይም በኃይል በመመልመል፣ በማጓጓዝ፣ በማሸጋገር፣ በመቀበል፣ ወይም በማስጠለል የሚፈጸም ድርጊት እንደሆነ ያስረዳል። ድርጊቱ ከባድ የሰብአዊ መብቶች ጥሰትን የሚያስከትል ሲሆን፣ ወንጀሉ የተጎጂዎችን ነጻነትና ክብራቸውን የሚገፍም ነው። የወንጀል ፈጻሚዎቹ ዋና ዓላማ በግዳጅ ሥራ፣ በልመና፣ በወሲባዊ ብዝበዛ፣ በሰውነት አካል ክፍል ስርቆት፣ በእገታ ክፍያ እና በሌሎች የብዝበዛ ድርጊቶች ገንዘብ ማግኘት ሲሆን በዚህም ሂደት የድርጊቱ ተጠቂዎች አብዛኛውን ጊዜ ለተለያዩ አካላዊ፣ ሥነ ልቦናዊ፣ ጾታዊ እና ኢኮኖሚያዊ ጥቃቶች ይዳረጋሉ፡፡

ኢትዮጵያም ይህን ፕሮቶኮል በ2012 ዓ.ም. ያጸደቀች ሲሆን፣ ይህንኑ ተከትሎ የተሻሻለውን በሰው የመነገድ እና ሰዎችን በሕገወጥ መንገድ ድንበር ማሻገርን የሚከለክል አዋጅ ቁጥር 1178/2020 አጽድቃለች፡፡ ይህ አዋጅ በሰው የመነገድ ወንጀል ተጎጂዎች ሁኔታቸውንና ልዩ ፍላጎታቸውን ያገናዘበ፣ ግላዊ ሚስጥራቸውን እና ሰብአዊ ክብራቸውን በጠበቀ መልኩ የጤና፣ የማኅበራዊ አገልግሎት፣ የሕግ እና ሥነ-ልቦና ምክርና ድጋፍ፣ ጊዜያዊ መጠለያ እና መሰል አገልግሎቶችን እንዲያገኙ ይደነግጋል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ተጎጂዎች በፍርድና በምርመራ ሂደት ወቅት ጉዳዩ የደረሰበትን ደረጃ የማወቅ እና መረጃ የመጠየቅ መብት፣ የመልሶ ማቋቋም ድጋፎች እና ካሳ ሊከፈላቸው እንደሚገባ እንዲሁም በማንኛውም ሁኔታ በፖሊስ ጣቢያ፣ በማረፊያ ቤት ወይም በማረሚያ ቤት እንዲቆዩ መደረግ እንደሌለበት ይደነግጋል፡፡

ሆኖም የሕጉን አተገባበር አስመልክቶ አሁንም በርካታ ሊሻሻሉ የሚገቡ ክፍተቶች መኖራቸው ይታያል። ለምሳሌ በሶማሊ ክልል ቶጎ ውጫሌ አካባቢ በክልሉ መስተዳደር እና በዓለም አቀፍ የፍልሰተኞች ድርጅት (IOM) ትብብር በ2015 በጀት ዓመት አንድ የፍልሰተኞች ምላሽ መስጫ ማዕከል ተከፍቶ አገልግሎት መስጠት የጀመረ ሲሆን፣ ይህንኑም ኮሚሽኑ በ2015 ዓ.ም. ዓመታዊ የሰብአዊ መብቶች ሁኔታ ሪፖርቱ በክልሉ ከተመዘገቡ መልካም እመርታዎች መካከል መጥቀሱ የሚታወስ ነው። ኮሚሽኑ በዚሁ የፍልሰተኞች ምላሽ መስጫ ማዕከል በመጋቢት ወር 2015 ዓ.ም. ባከናወነው ክትትል፤ በወንጀል ፈጻሚዎቹ ተታለው ከሀገር ከወጡ በኋላ ተጎጂዎች ለሞት፣ ለአካል ጉዳት፣ የሥነ-ልቦና ቀውስ፣ እና ለገንዘብ ብዝበዛ እና ለሌሎች የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶች እንደሚጋለጡ ለመገንዘብ ተችሏል፡፡ ከእነዚህ የወንጀሉ ተጎጂዎች መካከል የተወሰኑት በተለያየ መንገድ ወደ ሀገር የሚመለሱ ቢሆንም፣ ከተመለሱ በኋላ የተሟላ ድጋፍ እንደማይደረግላቸው፤ የመልሶ ማቋቋም ድጋፎች ባለመኖራቸው ተጎጂዎች ለዳግም መደበኛ ያልሆነ ፍልሰት እና ለሰብአዊ መብቶች ጥሰት ተጋላጭ እንደሚሆኑ ለማወቅ ተችሏል፡፡

ኢሰመኮ በፌዴራል ደረጃ በሚገኙ የፍትሕ ተቋማት የሚደረገውን የወንጀል ምርመራና የክስ ሂደት፣ እንዲሁም በፍትሕ አስተዳደር ሂደት ወቅት ለተጎጂዎች የሚሰጠው ድጋፍና ጥበቃ በሚመለከት በየካቲት እና መጋቢት ወር 2015 ዓ.ም. የተለያዩ የመንግሥት አካላትን በማነጋገር ክትትል አድርጓል፡፡ በወንጀል ምርመራ ሂደት ወቅት በቂ የማቆያ ቤቶች (Safe Houses)፣ የምግብ፣ የሥነ-ልቦና፣ የጤና እንዲሁም የገንዘብ ድጋፎች ባለመኖራቸው ተጎጂዎች ሂደቱን አቋርጠው ፍትሕ ሳያገኙ እንደሚቀሩ፤ በአጥፊዎች ላይ ፍርድ በሚሰጥበት ወቅትም ለተጎጂዎች የሚሰጥ ካሳ አለመኖሩ፤ በሕጉ መሠረት የተቀመጠው የተሟላ ድጋፍ እና ጥበቃ ባለመፈጸሙ ተጎጂዎች ዳግም መደበኛ ላልሆነ ፍልሰት ተጋላጭ እንደሚሆኑ መረዳት ተችሏል። በተጨማሪም ለምስክሮች የሚደረገው ጥበቃ አነስተኛ በመሆኑ ምስክርነት ሳይሰጡ እንደሚቀሩና ለወንጀል ክስ ሂደቱ ተግዳሮት መሆኑን የፍትሕ አካላቱ ይገልጻሉ።

በተመሳሳይ ኮሚሽኑ ከግንቦት 15 እስከ ሰኔ 4 ቀን 2015 ዓ.ም. በደቡብ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ክልል በጋሞ፣ ሀዲያ፣ በከምባታ ጠምባሮ እና ወላይታ ዞኖች ሕፃናትን በሰው ከመነገድ ወንጀል መጠበቅን አስመልክቶ ባከናወነው ክትትል፣ በተለይ ሕፃናት ለዚህ ወንጀል በከፍተኛ ሁኔታ ተጋላጭ መሆናቸውን፣ በዚህም ምክንያት ለአካል ጉዳት፣ የሥነ-ልቦና ቀውስ፣ ጾታዊ ጥቃቶች እና ሌሎችም የሰብአዊ መብቶቸ ጥሰት እንደሚጋለጡ ኮሚሽኑ ያነጋገራቸው ሕፃናት ተጎጂዎች እና የተጎጂ ቤተሰቦች አስረድተዋል፡፡ ለተጎጂ ሕፃናት የሚደረጉት ድጋፎችና መልሶ የማቋቋም ጥረቶች በመጀመሪያ ደረጃ ሕፃናቱን መደበኛ ላልሆነ ፍልሰትና ለሰብአዊ መብቶች ጥሰቶች የዳረጓቸውን ሁኔታዎች እንዲሁም የሕፃናቱን ልዩ ጥቅም (Best Interest of the Child) ያገናዘቡ አይደሉም፡፡ ለምሳሌ በቤተሰብ ጫና መደበኛ ላልሆነ ፍልሰት የተዳረጉ ተጎጂ ሕፃናት ካለምንም ዝግጅት እና ድጋፍ ወደ ቤተሰብ እንዲመለሱና እንዲቀላቀሉ በመደረጋቸው አብዛኞቹ ለዳግም መደበኛ ላልሆነ ፍልሰት ተዳርገዋል። ወደ ቤተሰብ ከተቀላቀሉ በኋላም በሕብረተሰቡ የመገለል ጫናዎች እንደሚደርስባቸው ለማወቅ ተችሏል፡፡ በሌላ በኩል በቂ የማቆያ ቤቶች ባለመኖራቸው ተጎጂ ሕፃናት በእስር ቤቶች እና ፖሊስ ጣቢያዎች እንዲቆዩ መደረጉ ጥበቃ ሊደረግላቸው ሲገባ በተቃራኒው በእስር ቤቶች ውስጥ እንዲቀመጡ በማድረግ ለተደራራቢ የሰብአዊ መብቶች ጥሰት እንደሚጋለጡ ኮሚሽኑ ባደረገው ክትትል ለማወቅ ተችሏል፡፡

በመሆኑም ለወንጀሉ ተጎጂዎች የሚደረገው ድጋፍ እና ጥበቃ በተደራጀ እና በተቀናጀ መልኩ ሊተገበር የሚገባ ሲሆን፣ በፌዴራልም ሆነ በክልል ደረጃ የማቆያ ቤቶች በመገንባት፣ ተደራሽ የሆነ ማኅበራዊ፣ ሥነ-ልቦናዊ እና የጤና አገልግሎት በማመቻቸት፣ እንዲሁም ለደረሰባቸው ጉዳት በሚገባ የሚካሱበትን የፍትሕ ሥርዓት በመዘርጋት ለተጎጂዎች የሚደረገው ድጋፍ የተሟላ ሊሆን እንደሚገባ ኮሚሽኑ ጥሪ ያደርጋል።

የኢሰመኮ ምክትል ዋና ኮሚሽነር ራኬብ መሰለ ቀኑን አስመልክቶ ባስተላለፉት መልዕክት በዘንድሮው መሪ ቃል መሠረት፣ ማንም ተጎጂ ወደኋላ ሳይተው በሰው መነገድ ወንጀል የተጎዱትን ሁሉ መድረስ እንደሚገባ አስታውሰው፣ “የተጎጂዎችን ሁኔታና ልዩ ፍላጎት ያማከለ ወቅታዊ እና አፋጣኝ ጥበቃና ድጋፍ ማረጋገጥ ትኩረት ሊሰጠው የሚገባ ጉዳይ” መሆኑን ገልጸዋል። በተጨማሪም፣ ይህንን ወንጀል ለመከላከል እና ለመቆጣጠር የተዘጋጀው ረቂቅ የስትራቴጂ ዕቅድ ጸድቆ ወደ ሥራ ሲገባ መንግሥት ይህን መሰል የጥበቃና ድጋፍ ሥርዓት እንደሚዘረጋ የሚጠበቅ መሆኑን ገልጸዋል። “ይህንኑም ለማሳካት መንግሥታዊ እና መንግሥታዊ ያልሆኑ ባለድርሻ አካላት በሰው የመነገድ ወንጀልን ለመከላከል፣ ለሁሉም ለወንጀሉ ተጎጂዎች ወቅታዊ፣ አፋጣኝ እና ተደራሽ የጥበቃ እና ድጋፍ አገልግሎት በተሟላ ሁኔታ ለማቅረብ፣ ለዳግም-ውህደት (reintegration) አስቻይ ሁኔታዎችን ለማመቻቸት እንዲሁም፣ ለተጨማሪ ጥቃት ተጋላጭ እንዳይሆኑ ተጨባጭ እርምጃዎች እንዲወሰዱ” ጥሪ አቅርበዋል።