የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ሐሳብን በነጻነት የመግለጽ መብት ከሚዲያ አንጻር የሦስት ባለድርሻ አካላት ሚና በሚል ርዕስ በሰኔ 27 ቀን 2015 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ውይይት አካሂዷል። የውይይት መድረኩ ሐሳብን በነጻነት የመግለጽ መብት እንዲስፋፋና እንዲከበር በኮሚሽኑ፣ በሲቪል ማኅበራት እና በመገናኛ ብዙኃን መካከል ሊኖር የሚገባውን የሦስትዮሽ ቅንጅትና ስትራቴጂያዊ አጋርነት እንዴት ማጠናከር እንደሚቻል ለመወያየት የተዘጋጀ ሲሆን ውጤቱም በሀገራችን ሰብአዊ መብቶች እንዲስፋፉ እና እንዲከበሩ በተናጠልም ሆነ በጋራ አስተዋጽዖ እንዲያደርጉ ግፊት ማድረግ ነው። የምክክር መድረኩ በ2014 ዓ.ም. ከመገናኛ ብዙኃን እና ከሲቪል ማኅበራት ጋር በመሆን ከተጀመረው የሦስትዮሽ ምክከር የቀጠለ ሲሆን በመድረኩ የመገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎች እና የሲቪል ማኅበራት ተወካዮች ተሳትፈዋል።

በውይይት መድረኩ የሲቪል ምህዳሩን የተመለከቱ ዓለም አቀፍና አህጉራዊ የሰብአዊ መብቶች ድንጋጌዎች እና ማዕቀፎች ተብራርተዋል። የሰብአዊ መብቶች ድርጅቶች ኅብረት ዳይሬክተር መሱድ ገበየሁ እና የሚዲያ ካውንስል ፕሬዝዳንት አማረ አረጋዊ ባቀረቡት የውይይት መነሻ ሐሳብ የሦሰትዮሽ አጋርነቱ ቅንጅታዊ አሠራርንና ትብብርን ለማጎልበትና በሀገራችን በመብት ተሟጋቾች እንዲሁም በጋዜጠኞች ላይ የሚደርሱትን የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶች በመቀነስ ረገድ ዓይነተኛ አስተዋጽዖ እንዳለው ገልጸዋል።

የመገናኛ ብዙኃን እና የሲቪል ማኅበራት ከኢሰመኮ ጋር ያላቸውን ትብብር ማጠናከር ስለሚቻልባቸው መንገዶች እና እያንዳንዳቸው ሊጫወቱ ስለሚገባቸው ሚና ሰፊ ውይይት ተደርጓል፡፡ የመገናኛ ብዙኃንን በመወከል የሚዲያ ካውንስል፣ የሲቪል ማኅበራትን በመወከል የሰብአዊ መብቶች ድርጅቶች ኅብረት እና የሲቪል ማኅበራት ካውንስል ከኮሚሽኑ ጋር በመሆን በሦስትዮሽ ማዕቀፍ ሊሠሩ የሚችሉ አንኳር ሥራዎችን በመለየት ለሦስቱ ዘርፎች ተወካዮች እንዲያቀርቡና ቀጣይነት ያለው ሥራ እንዲሠራ መግባባት ላይ ተደርሷል።

የኢሰመኮ ምክትል ዋና ኮሚሽነር ራኬብ መሰለ ኢሰመኮ ከተለያዩ አካላት ጋር በቅንጅት እና በአጋርነት እንደሚሠራ ጠቁመው፣ ይህ መድረክ በኮሚሽኑ፣ በሲቪክ ማኅበራት እና በመገናኛ ብዙኃን መካከል ያለውን ትብብር እና አጋርነት ለማጠናከር የሚያስችሉ ሁኔታዎችን በመለየት ትብብሩን ወደ ስትራቲጂያዊ አጋርነት የሚያሳድግ መሆኑን ገልጸዋል። አክለውም ሐሳብን በነጻነት የመግለጽ፣ መረጃ የማግኘት፣ የመሰብሰብ እና የመደራጀት መብቶችን ለማስፋፈትና ለማስከበር፣ እንዲሁም የሲቪል ምህዳሩን ለማስፋትና ምቹ የሆነ የፖሊሲ ማዕቀፍ እንዲኖር ለማድረግ በሦስቱ ዘርፎች መካከል ጠንካራ ትብብር እና አጋርነት አስፈላጊ መሆኑን አሳስበዋል። የሦስትዮሽ ትብብሩ መጠናከር እነዚህን ሰብአዊ መብቶች ተጠቅመው የሚንቀሳቀሱ የመብት ተሟጋቾች ሊደርስባቸው የሚችለውን ጫና እና እንግልት በጋራ ለመከላከል እና ለመቋቋም ትልቅ ሚና ይኖረዋል ብለዋል።