የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) በአማራ ክልል፣ በአዊ ብሔረሰብ ዞን፣ በአየሁ ጓጉሳ ወረዳ እና በምዕራብ ጎጃም ዞን፣ ቡሬ ዙሪያ ወረዳ፤ እንዲሁም በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል፣ አሶሳ ዞን፣ ኦዳ ብልድግሉ ወረዳ፤ በተጨማሪም በኦሮሚያ ክልል፣ በአርሲ ዞን፣ ሸርካ ወረዳ እና በቄለም ወለጋ ዞን፣ ጊዳሚ ወረዳ በሲቪል ሰዎች ላይ የተፈጸሙ ጥቃቶችን በተመለከተ የደረሱትን ጥቆማዎችና አቤቱታዎች መሠረት በማድረግ የተጎጂ ቤተሰቦችን፣ ነዋሪዎችን እና የየአካባቢዎቹን የመንግሥት ኃላፊዎች በማነጋገር ክትትል ሲያደርግ ቆይቷል።

በአማራ ክልል፣ በአዊ ብሔረሰብ ዞን አስተዳደር፣ በአየሁ ጓጉሳ ወረዳ፣ አምበላ ቀበሌ እና በዚገም ወረዳ ሶሪት ቀበሌ ከጥቅምት 29 ቀን 2016 ዓ.ም. ጀምሮ በተለያዩ ቀናት በተፈጠረው ብሔር ተኮር ግጭት ሞት እና የአካል ጉዳት እንዲሁም በኢንቨስትመንት ቦታዎች ላይ ጉዳት ደርሷል። በአማራ ክልል ምዕራብ ጎጃም ዞን፣ ቡሬ ዙሪያ ወረዳ፣ ፈጣም ሰንቶም እና በቆጣቦ ቀበሌዎች ጥቅምት 30 ቀን 2016 ዓ.ም. እና በኅዳር 1 ቀን 2016 ዓ.ም. ኢመደበኛ የአማራ ታጣቂዎች መሆናቸው የተገለጸ ቡድኖች በሰነዘሩት ብሔር ተኮር ጥቃት እና ይህንኑ ተከትሎ በተፈጠረው ግጭት በርካታ ሰዎች ላይ የሞት፣ የአካልና የንብረት ጉዳት ደርሷል። በተፈጠረው ግጭት ምክንያት ነዋሪዎች ተፈናቅለው በቡሬ ዙሪያ ወረዳ በሚገኙ አጎራባች ቀበሌዎች እና ወደ ኦሮሚያ ክልል ለመሄድ ተገደዋል። የቀንድ ከብቶች ተዘርፈዋል።

በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል፣ አሶሳ ዞን፣ ኦዳ ብልድግሉ ወረዳ ሥር በሚገኙ ቤልሚሊ፣ አልከሻፊ እና ቤላደሩ ቀበሌዎች በሚኖሩ የቤኒሻንጉል ብሔር ተወላጆች እና አብረው በሚኖሩት የኦሮሞ ብሔር ተወላጆች ላይ ኅዳር 19 ቀን 2016 ዓ.ም. ከንጋቱ 11፡00 ሰዓት ጀምሮ እስከ ቀኑ 5፡00 ሰዓት አካባቢ በኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት (በተለምዶ ኦነግ-ሸኔ) ታጣቂ ቡድን አባላት በተፈጸመ ጥቃት በሰው ሕይወትና በንብረት ላይ ጉዳት ደርሷል፡፡ ይህ መግለጫ ይፋ እስከተደረገበት ቀን ድረስ በተሰበሰበ መረጃ በጥቃቱ 17 (አስራ ሰባት) ሰዎች መገደላቸውን፣ አንድ ሽማግሌ ታፍነው መወሰዳቸውን፣ በ7 (ሰባት) ሰዎች ላይ ደግሞ ከባድ የአካል ጉዳት የደረሰ መሆኑን ማወቅ ተችሏል። በሦስቱ ቀበሌዎች ያሉ መንደሮች በአብዛኛው የተቃጠሉና የወደሙ መሆኑን፣ የእርሻ ሰብልና የቤት እንስሳትን ጨምሮ የንብረት ውድመት የደረሰ መሆኑን፣ እንዲሁም የቀበሌዎቹ ነዋሪዎች ጥቃቱን በመሸሽ ወደ አጎራባች ቀበሌዎችና በአቅራቢያው ወደ ሚገኘው ኦሮሚያ ክልል መነሲቡ ወረዳ የተፈናቀሉ መሆኑም ታውቋል።

በኦሮሚያ ክልል በአርሲ ዞን፣ ሸርካ ወረዳ ኅዳር 13 ቀን 2016 ዓ.ም. በጢጆ ለቡ ቀበሌ በግምት ከምሽቱ 1፡00 ሰዓት በኋላ ማንነታቸው በውል ያልተለየ ታጣቂዎች በፈጸሙት ብሔር/ማንነት ተኮር ጥቃት 7 (ሰባት) የአንድ ቤተሰብ አባላት እና ሦስት ጎረቤቶቻቸው ጨምሮ በአጠቃላይ 10 (አስር) ሰዎችን መግደላቸውን እና በዚያው ዕለት ታጣቂዎቹ በሶሌ ዲገሉ ቀበሌ ቢያንስ 12 (አስራ ሁለት) ሲቪል ሰዎችን መግደላቸውን የሚያመላክቱ መረጃዎችና ማስረጃዎች ኮሚሽኑ አሰባስቧል፡፡ በሶሌ ዲገሉ ቀበሌ ከተገደሉ 12 ሰዎች መካከል አሥራ አንዱ የአንድ ቤተሰብ አባላት መሆናቸውም ተገልጿል። በኅዳር 17 ቀን 2016 ዓ.ም. በወረዳው በኮኘ ቀበሌ ታጣቂዎቹ በፈጸሙት ጥቃት የአንድ ቤተሰብ አባላት የነበሩ 8 (ስምንት) ሰዎችን ገድለዋል። ጥቃት አድራሾች ሟቾችን ከቤት እያስወጡ አሰልፈው እንደገደሏቸው፣ የተወሰኑትም በቤታቸው ውስጥ እንደተገደሉ ለማወቅ ተችሏል። ከሟቾች መካከል ጨቅላ ሕፃንን ጨምሮ ነፍሰጡር ሴቶች እና ከ80 ዓመት በላይ የሆናቸው አረጋዊ ይገኙበታል፡፡ ከተገደሉት ሰዎች በተጨማሪ ቁጥራቸው በውል ያልታወቀ ሰዎች ጉዳት ደርሶባቸው በሕክምና ላይ ይገኛሉ፡፡ የአካባቢው ነዋሪዎች አሁንም ተደጋጋሚ ዛቻ እየደረሳቸው መሆኑን ለኮሚሽኑ ገልጸው መንግሥት በአስቸኳይ እንዲደርስላቸው ተማጽነዋል፡፡

በተጨማሪም በኦሮሚያ ክልል፣ ቄለም ወለጋ ዞን፣ ጊዳሚ ወረዳ፣ በቤጊ-ጊዳሚ ሲኖዶስ ጊዳሚ ሰበካ ሥር የምትገኘው የመናኮ መናሞ ቀበሌ የሃሞ ቶኩማ አጥቢያ የመካነ ኢየሱስ ቤተ-ክርስቲያን አባላት የነበሩት 9 (ዘጠኝ) ምዕመናን፣ የቤተ-ክርስቲያኗ ሽማግሌዎች፣ የወጣቶች ኮሚቴ አባላት እንዲሁም ሌሎች አገልጋዮችን ኅዳር 14 ቀን 2016 ዓ.ም. ከሌሊት 8፡00 ሰዓት አካባቢ እስካሁን ማንነታቸው ባልተለዩ በታጠቁ ቡድኖች ተገድለዋል። ግድያው የተፈጸመው ጸሎት ላይ በነበሩ ሰዎች ላይ ሲሆን፣ በቤተ-ክርስቲያን ውስጥ ከነበሩ 12 ሰዎች መካከል ሁለት ሴቶች እና አንድ አዛውንት በማስቀረት ዘጠኙን ሰዎች ስም በመጥራት ከቤተ-ክርሲቲያኗ በማውጣት በአቅራቢያው መላኮ መናሞ ቀበሌ ባለው ጫካ ውስጥ ገድለው አስክሬናቸውን መጣላቸው ኮሚሽኑ ለማረጋገጥ ችሏል። ከዘጠኙ ሟቾች የተወሰኑት የቤተሰብ አባላት እንደሆኑም ተገልጿል።

በአማራ፣ በቤኒሻንጉል ጉሙዝና በኦሮሚያ ክልሎች የተለያዩ አካባቢዎች በግጭት ዐውድ ውስጥ እና ከግጭት ዐውድ ውጪ በሲቪል ሰዎች ላይ የሚደርሱ የሰብአዊ መብቶች ጥሰት እጅግ አሳሳቢነት የቀጠለ ነው። በተለይም በአማራና ኦሮሚያ ክልሎች ተስፋፍተው በቀጠሉት ግጭቶች ዐውድ ውስጥ ሲቪል ሰዎች ላይ የሚፈጸሙ ግድያዎች፣ ማፈናቀሎች፣ እገታዎች እና ዘረፋዎች የነዋሪውን ሕይወት እጅግ የከፋ አድርገውታል፡፡ ይህ መግለጫ እስከወጣበት ጊዜ ድረስም በእነዚህ አካባቢዎች የደረሱ ተጨማሪ ጥቃቶችን በተመለከተ አሁንም ለኮሚሽኑ መረጃዎች እየደረሱት ሲሆን የማጣራትና የማረጋገጥ ሥራውን ቀጥሏል። እንዲሁም ከዚህ በላይ በተገለጹት ክስተቶችም ተጨማሪ ምርመራ በማድረግ ዝርዝር መረጃዎችና ማስረጃዎችን ለማሰባሰብ የሚያደርገውን ጥረት የሚቀጥል ይሆናል።

የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር ዶ/ር ዳንኤል በቀለ “በዚህ የግጭት ዐውድ እየደረሰ ያለው እጅግ አሠቃቂ ጉዳት ከዚህ የበለጠ ከመባባሱ እና የበለጠ ጉዳት ከመድረሱ በፊት መንግሥት ተገቢውን ሰላማዊና ፖለቲካዊ መፍትሔ ተግባራዊ እንዲያደርግ፣ ሁሉም ታጣቂ ቡድኖችና መንግሥት ሰብአዊ የተኩስ ማቆም አድርገው ወደ ውይይት እንዲያመሩ፣ መንግሥት በተለይ ለሰብአዊ መብቶች ጥሰትና ለጥቃት ተጋላጭ ለሆኑ አካባቢዎችና ነዋሪዎች በሙሉ የተሟላ ጥበቃና ደኅንነት እንዲያረጋግጥ ያስፈልጋል” ብለዋል፡፡ ዋና ኮሚሽነሩ አክለውም “የጥፋተኞችን ተጠያቂነትና ፍትሕ ከማረጋገጥ በተጨማሪ፤ መንግሥትና ሌሎች አጋር አካላት በጥቃቶቹ ምክንያት ከቀያቸው ለተፈናቀሉ ነዋሪዎች በቂ የሆነ አስቸኳይ የሰብአዊ ድጋፍ እንዲያቀርቡ፣ ተፈናቃዮች ወደ ቀያቸው ተመልሰው በዘላቂነት የሚቋቋሙበት ሁኔታ እንዲመቻች ማድረግ” አስፈላጊ መሆኑን ገልጸዋል፡፡