የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ከአረጋውያንና ጡረተኞች ብሔራዊ ማኅበር እና ሄልፕኤጅ ኢንተርናሽናል ኢትዮጵያ ጋር በአረጋውያን ላይ ስለሚደርስ ጥቃት ግንዛቤ የማስጨበጫ ቀንን (World Elder Abuse Awareness Day) አስመልክቶ መንግሥታዊ እና መንግሥታዊ ያልሆኑ ባለድርሻ አካላትን ያሳተፈ የውይይት መድረክ ሰኔ 8 ቀን 2015 ዓ.ም. በአዲስ አበባ አከናውኗል፡፡

በውይይቱ በአረጋውያን ላይ የሚፈጸሙ ጥቃቶች ምንነትና ዓይነቶች እንዲሁም በኢትዮጵያ ያሉት የሕግ ማዕቀፎችና ክፍተቶቻቸው በስፋት ተዳስሰዋል፡፡ በተጨማሪም የሰብአዊ መብቶች ጥሰት ተጎጂ የሆኑ አረጋውያን ታሪኮች የቀረቡ ሲሆን፤ ለተመሳሳይ ጥሰቶች ዘላቂ መፍትሔ ለማምጣት በሚቻልባቸው ጉዳዮች ላይ የፓናል ውይይት ተካሂዷል፡፡

የውይይቱ ተሳታፊዎች አረጋውያን መብቶቻቸውን አውቀው መጠየቅ እና ከጥቃት ራሳቸውን መከላከል እንዲችሉ የዐቅም ማጎልበቻ ስልጠናዎች ሊሰጣቸው እንደሚገባ እና በልዩ ሁኔታ ሴት አረጋውያን ላይ የሚደርሱ ጾታዊ ጥቃቶችን ለመከላከል የሁሉም ባለድርሻ አካላት ርብርብ የሚያስፈልግ መሆኑን አብራርተዋል፡፡ በተጨማሪም አረጋውያን የትራንስፖርት አገልግሎትን ጨምሮ ሌሎች መሠረታዊ አገልግሎቶችን ለማግኘት በሚሄዱባቸው ተቋማት ቅድሚያ ሊያገኙ የሚችሉበት አሠራር መዘርጋት አስፈላጊ መሆኑን እና ሌሎች ስለ ጉዳዩ ግንዛቤ ለማስፋፋት ሊደረጉ ይገባቸዋል ያሏቸውን ተግባራት በዝርዝር አንስተዋል፡፡

የውይይቱ ተሳታፊዎች በስብሰባ አዳራሽ ውስጥ
የውይይቱ ተሳታፊዎች በስብሰባ አዳራሽ ውስጥ

የኢሰመኮ የአካል ጉዳተኞች እና አረጋውያን መብቶች ኮሚሽነር ርግበ ገብረሐዋርያ በውይይቱ መክፈቻ “አረጋውያን ላይ ለሚደርሱ ጥቃቶች በቂ እና ግልጽ ምላሽ መስጠት የሚያስችሉ የሕግ ማዕቀፎች እንዲወጡ፣ አካታች የፍትሕ ተቋማትና ሥርዓት እንዲዘረጋ እንዲሁም ማኅበረሰቡ ስለ ጉዳዩ በቂና ትክክለኛ መረጃ እንዲያገኝ ለማድረግ የሚያስችሉ ሥራዎችን በሰፊው ልናከናውን ይገባል” ሲሉ መልእክታቸውን አስተላለፍዋል፡፡

የኢሰመኮ የአካል ጉዳተኞች እና አረጋውያን መብቶች ኮሚሽነር ርግበ ገብረሐዋርያ
የኢሰመኮ የአካል ጉዳተኞች እና አረጋውያን መብቶች ኮሚሽነር ርግበ ገብረሐዋርያ

የኢትዮጵያ አረጋውያንና ጡረተኞች ብሔራዊ ማኅበር ምክትል ቦርድ ፕሬዚደንት ጌታቸው ክፍሉ በበኩላቸው “አረጋውያን ላይ የሚደርሱ ጥቃቶችን ከመከላከል እና ድርጊቶቹ ተፈጽመው ሲገኙ ለአረጋውያኑ ፍትሕ ከማሰጠት አኳያ ዓለም አቀፍ የአረጋውያን መብቶች ስምምነት ከፍተኛ ሚና የሚኖረው በመሆኑ መንግሥታት ይህ ዓለም አቀፍ ስምምነት እንዲኖር ለማስቻል በቁርጠኝነት ሊሠሩ ይገባል” ብለዋል፡፡

በአረጋውያን ላይ ስለሚደርስ ጥቃት ግንዛቤ ማስጨበጫ (World Elder Abuse Awareness Day) ቀንን ምክንያት በማድረግ ኢሰመኮ ያዘጋጀውን ማብራሪያ እዚህ ያንብቡ፡፡