የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ዋና ኮሚሽነር ዶ/ር ዳንኤል በቀለን ጨምሮ 5 የኮሚሽኑ ባለሙያዎች የሚገኙበት ቡድን በአስቸኳይ ጊዜ  አዋጅ መሠረት በቁጥጥር ሥር ውለው አዋሽ አርባ አካባቢ በሚገኘው የሀገር መከላከያ ሚኒስቴር የምዕራብ ዕዝ ወታደራዊ ማሰልጠኛ ካምፕ ውስጥ ተይዘው የሚገኙትን ታሳሪዎች ነሐሴ 26 ቀን 2015 ዓ.ም. ጎብኝቷል።

እነዚህ ታሳሪዎች የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል የሆኑት አቶ ክርስቲያን ታደለ፣ የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ ምክር ቤት አባል የሆኑት አቶ ዮሐንስ ቧያለው፣ የአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት አባል የሆኑት ዶ/ር ካሳ ተሻገር፤ እንዲሁም ጋዜጠኛ በቃሉ አላምረው፣ አባይ ዘውዱ፣ እና ቴዎድሮስ ዘርፉ፤ የተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲ አባል አቶ ስንታየሁ ቸኮል፣ አቶ በለጠ ጌትነት፤ እና በአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ውስጥ በኃላፊነት ይሠሩ የነበሩት አቶ ከፋለ እሱባለውን ጨምሮ በአጠቃላይ 53 ወንድ እስረኞች ሲሆኑ፤ ከአዲስ አበባ ከተማና ከአማራ ክልል የተለያዩ ቦታዎች በተለያየ ጊዜ ተይዘው ከነሐሴ 15 ቀን እስከ ነሐሴ 24 ቀን 2015 ዓ.ም. ባለው ጊዜ ውስጥ ወደ አዋሽ አርባ ወታደራዊ ካምፕ ውስጥ የሚገኝ ጊዜያዊ/መደበኛ ያልሆነ ማቆያ ጣቢያ የተወሰዱ ናቸው፡፡     

ኮሚሽኑ በተለመደው አሠራሩ መሠረት ታሳሪዎቹን ለብቻቸው አነጋግሯል፣ ቦታውን ጎብኝቷል እንዲሁም ጉዳዩ የሚመለከታቸውን የፖሊስ ኃላፊዎች አነጋግሯል፡፡ የፖሊስ ኃላፊዎች ለኮሚሽኑ እንደገለጹት ታሳሪዎችን ወደዚህ ጊዜያዊ ማቆያ ጣቢያ ማምጣት ያስፈለገው አዲስ አበባ የሚገኘው የፌዴራል ፖሊስ ማቆያ ጣቢያ ላይ ከፍተኛ መጣበብ በመፈጠሩ መሆኑን፣ የአዋሽ አርባ አካባቢ ከፍተኛ ሙቀት ያለበት አካባቢ ስለሆነ በተቻለ መጠን በግቢው ውስጥ ካሉት ቤቶች ውስጥ የተሻለ በሆነው ሰፊ አዳራሽ ውስጥ የመኝታ አልጋ ተዘጋጅቶ ታሳሪዎቹ በአንድ ላይ አብረው የተያዙ መሆኑን፣ ነፋስ ለመቀበል መንቀሳቀስ እንደሚቻል፣ በካምፑ በኩል ቁርስ፣ ምሳ እና እራት ተዘጋጅቶ እንደሚቀርብ፣ አስቸኳይ የሕክምና ዕርዳታ በካምፑ በኩል ሊሰጥ እንደሚችል፣ ከዚህ በላይ ለሆነ የሕክምና አገልግሎት ወደ ሆስፒታልም መውሰድ እንደሚቻል፤  ለምሳሌ አቶ ክርስቲያን ታደለ እና አቶ ዮሐንስ ቧያለው ወደ አዲስ አበባ ለሕክምና ተወስደው የህክምና አገልግሎት አግኝተው መመለሳቸውን ገልጸዋል። በተጨማሪም የቤተሰብ ጉብኝት ሊመቻች እንደሚችል ሆኖም ከቦታው ርቀት አንጻር አብዛኛዎቹ ታሳሪዎች ቤተሰብ እንዳይጉላላ ጉብኝቱን እንደማይፈልጉ መግለጻቸውንና ይልቁን በስልክ ለመነጋገር እንዲችሉ መጠየቃቸውንና ይህም ዝግጅቱ እየተጠናቀቀ ስለሆነ በቅርቡ በስልክ ለመነጋገር እንዲችሉ እንደሚደረግ፣ ቃላቸውን ለመስጠት ፈቃደኛ ያልሆኑ የተወሰኑ ታሳሪዎች ቢኖሩም የምርመራ ሥራውን በአፋጣኝ ለማጠናቀቅ ፖሊስ የተቻለውን ጥረት እያደረገ መሆኑንና አጠቃላይ አያያዛቸው የሰብአዊ መብቶችን ያከበረ እንዲሆን ፖሊስ ዐቅም በፈቀደው መጠን ሁሉ የተቻለውን ጥረት እያደረገ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

በአንጻሩ እጅግ አብዛኛዎቹ ታሳሪዎች ብሔራቸው አማራ፣ እምነታቸው ኦርቶዶክስ ክርስቲያን መሆኑንና ለእስር የተዳረጉት በብሔር ማንነታቸው ብቻ መሆኑን እንደሚያምኑ፣ ከፊሎቹ በመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች በተያዙበትና ቤታቸው በተበረበረበት ወቅት በራሳቸውና በቤተሰብ አባል ላይ ድብደባ፣ ብሔር ተኮር ስድብ፣ ማጉላላት፣ ዛቻና ማስፈራራት እንደደረሰባቸው ሆኖም በፌዴራል ፖሊስ ቁጥጥር ስር ከሆኑ በኋላ የተፈጸመ ድብደባ ወይም አካላዊ ጥቃት አለመኖሩን፣ ከፊሎቹ በተለይም ከአማራ ክልል ተይዘው የመጡ ሰዎች ከተያዙበት ጊዜ ጀምሮ ቤተሰቦቻቸው የት እንዳሉ እንኳን እንደማያውቁ አስረድተዋል። አክለውም የአዋሽ አርባ አካባቢ እጅግ ከፍተኛ ሙቀት ያለው በመሆኑና ከአካባቢው የአየር ጠባይ እንዲሁም ቦታው የወታደራዊ ካምፕ እንጂ መደበኛ የተጠርጣሪዎች ማቆያ ስፍራ ስላልሆነ ለጤንነታቸው፣ ለደኅንነታቸውና ለሕይወታቸው ሥጋት እንዳላቸው፣ አልባሳትን ጨምሮ ከቤተሰብ የሚፈልጉትን አቅርቦት ለማግኘት እንዳልቻሉ፣ ከፊሎቹ በሥራቸውም ሆነ በግል ሕይወታቸው ፈጽሞ በፖለቲካ ነክ ጉዳይ ተሳትፎ እንደሌሉና እንዴት ለእስር እንደበቁ መገረማቸውንና መደንገጣቸውን ገልጸዋል።

ኮሚሽኑም ከፖሊስ ኃፊዎች ጋር ባደረገው ውይይት በእስር ወቅት ተፈጽመዋል ስለተባሉ የሥነ ምግባር ጥሰቶች ተገቢው ማጣራት እንዲደረግ፣ ታሳሪዎቹ ከቤተሰብ ለሚፈልጉት አቅርቦት አዲስ አበባ በሚገኘው የፖሊስ ቢሮ አማካኝነት እንዲመቻች፣ ከቤተሰብ መገናኛ ስልክና ጉብኝት ለሚፈልጉም በአፋጣኝ እንደሚመቻች መግባባት ላይ ተደርሷል።

ኢሰመኮ በተቋቋመበት አዋጅ ቁጥር 210/1992 (በአዋጅ ቁጥር 1224/2012 እንደተሻሻለው) አንቀጽ 6/12 መሠረት በአስቸኳይ ጊዜ ወቅት ሰብአዊ መብቶችን የመከታተል ተግባርና ኃላፊነት ያለበት መሆኑን እና በአስቸኳይ ጊዜ ሁኔታም ውስጥ ቢሆን የጸጥታ እና የፍትሕ አካላት በሰብአዊ መብቶች እና ሕገ መንግሥታዊ መርሖች እንዲመሩ፣ በማናቸውም ሁኔታ ሊገደቡ የማይችሉ መብቶች ሊከበሩ እንደሚገባ፤ እንዲሁም ከአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ አፈጻጸም ጋር የሚወሰዱ ማናቸውም እርምጃዎች የጥብቅ አስፈላጊነትን፣ የተመጣጣኝነትን፣ ከአድሎ ነጻ የመሆንን እና የሕጋዊነትን መርሖች ጨምሮ በሰብአዊ መብቶች መርሖች እና ድንጋጌዎች ሊመሩ እንደሚገባ በማስታወስ፣ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በላከው  ምክረ ሐሳብ፣ እንዲሁም ይፋ ባደረጋቸው ሰነዶች ማሳሰቡ የሚታወስ ነው። በተለይም ሰዎችን ከአስገድዶ መሰወር፣ እገታ፣ አፈና ወይም ባልታወቁ ቦታዎች (unacknowledged detentions) እንዳይታሰሩ የሚደረጉ ጥበቃዎች እንዲሁም ነጻና ገለልተኛ በሆነ ፍርድ ቤት የመዳኘትና ፍትሕ የማግኘት መብት በዓለም አቀፍ ሕግ መሠረት  በማናቸውም ጊዜ ቢሆን ሊታገዱ የማይችሉ መብቶች መሆናቸውን ማሳሰቡም ይታወቃል።

ኮሚሽኑ አዋጅ ቁጥር 6/2015 ተግባር ላይ ከዋለበት ከሐምሌ 28 ቀን 2015 ዓ.ም. ጀምሮ የሚደርሱትን አቤቱታዎች እና ጥቆማዎች ከመመርመር፣ መረጃዎችን እና ማስረጃዎችን ከማሰባሰብ በተጨማሪ፣ ተጎጂዎችን፣ የተጎጂ ቤተሰቦችን፣ ምስክሮችን እና ሌሎች የመረጃ ምንጮችን፣ እንዲሁም የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ጠቅላይ መምሪያ ዕዝ፣ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መርማሪ ቦርድን ኃላፊዎችን ጨምሮ ከሚመለከታቸው የጸጥታ አካላት ጋር በመነጋገር እና የውትወታ ሥራ በመሥራት ከአዋጁ አፈጻጸም ጋር የተያያዙ የሰብአዊ መብቶች ሁኔታን በተመለከተ ክትትል በማድረግ ላይ ይገኛል።

በዚሁም መሠረት፣ በኮማንድ ፖስቱ ትዕዛዝ መታሰራቸው ከተገለጸው ታሳሪዎች በተጨማሪ በዚሁ የአስቸኳይ ጊዜ ሁኔታ ዐውድ በተለይ በአዲስ አበባ ከተማ፤ በአማራ ክልል ደብረ ታቦር፣ ባሕር ዳር እና ጎንደር ከተሞችን ጨምሮ በሌሎች አካባቢዎች፤ በኦሮሚያ ክልል  በአዳማ፣ በቢሾፍቱ፣ በገላን እና በሸገር እንዲሁም ሌሎች ከተሞች፣  መደበኛ ያልሆኑ ቦታዎች ተይዘው ስለነበሩ ሰዎች፣ ከፊሎቹ የተለቀቁ ቢሆንም ይህ ጋዜጣዊ መግለጫ ይፋ እስከሆነበት ጊዜ ድረስ በእስር ላይ ስለሚገኙ ሰዎችና ከእነዚህም መካከል የኤርትራ ፍልሰተኞችን (migrants) ጨምሮ ኮሚሽኑ ክትትል በማድረግ ላይ ይገኛል፡፡

ኢሰመኮ እስከ አሁን ስላደረገው ክትትል፣ ግኝቶች፣ ተግዳሮት እና ምክረ ሐሳቦች ነሐሴ 25 ቀን 2015 ዓ.ም. ከአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አፈጻጸም መርማሪ ቦርድ ጋር የተወያየ ሲሆን፤ ስለ አጠቃላይ ሁኔታው፣ የሰብአዊ መብቶች አከባበርና ዘላቂ ሰላማዊ መፍትሔ ሐሳቦች ከልዩ ልዩ ባለድርሻ አካላት ጋር የሚያደርገውን ውይይትና ምክክር የሚቀጥል መሆኑን ዋና ኮሚሽነር ዶ/ር ዳንኤል በቀለ ገልጸዋል፡፡