የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ጋዜጣዊ መግለጫ 

ጥር 26 ቀን 2014 ዓ.ም.

በኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) እና በተ.መ.ድ. ከፍተኛ የሰብአዊ መብቶች ኮሚሽነር ጽሕፈት ቤት (UNOHCHR) አዘጋጅነት፣ በትግራይ ክልል ግጭት ተፈጸሙ የተባሉ የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶችን በተመለከተ በሁለቱ ተቋማት የተደረገውን ጣምራ ምርመራ ሪፖርት ምክረ ሃሳቦች አፈጻጸምና ክትትል አስመልክቶ ከሚመለከታቸው የመንግሥት አካላት፣ከዲፕሎማቲክ ማኅበረሰቡ፣ ከዓለም አቀፍ ድርጅቶች፣ ከምኁራንና ከሀገራዊና ዓለም አቀፍ ሲቪክ ማኅበረሰብ አባላት ጋር የምክክር መድረክ ጥር 26 ቀን 2014 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ተካሂዷል።

ከግንቦት 8 ቀን እስከ ነሃሴ 24 ቀን 2013 ዓ.ም. ድረስ በኢሰመኮ እና በተ.መ.ድ. ከፍተኛ የሰብአዊ መብቶች ኮሚሽነር ጽሕፈት ቤት በኢትዮጵያ ትግራይ ክልል ከተከሰተው ጦርነት ጋር በተያያዘ የደረሱ የሰብአዊ መብቶች፣ የዓለም አቀፍ የሰብአዊነት ወይም የጦርነት ሕጎች እንዲሁም የስደተኞች መብቶች ድንጋጌዎችን ጥሰቶችን በተመለከተ የጣምራ ምርመራ ሲያካሄዱ ቆይተው፣ ሪፖርቱ እ.ኤ.አ. ኅዳር 3 ቀን 2021 ይፋ መደረጉ ይታወሳል።

የተ.መ.ድ. ከፍተኛ የሰብአዊ መብቶች ኮሚሽነር ጽ/ቤት እና ኢሰመኮ የጣምራ ምርመራ ሪፖርቱን ምክረ ሃሳቦች አፈጻጸምና ክትትል አስመልክቶ ተከታታይነት ያላቸው ውይይቶችን ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር አድርገዋል። በዚህ ረገድ በኢሰመኮና በተ.መ.ድ. ከፍተኛ የሰብአዊ መብቶች ኮሚሽነር ጽ/ቤት የምክረ ሃሳቦቹን አፈጻጸም በውትወታ፣ በቴክኒካዊ ድጋፍና በአቅም ግንባታ የሚያግዝ ቡድን ተቋቁሟል። ጥር 26 ቀን 2014 ዓ.ም. የተካሄደው የውይይት መድረክ ዋና ዓላማ ባለድርሻ አካላት የጋራ መግባባት ላይ እንዲደርሱና እያንዳንዳቸው የሚኖራቸውን ሚና በተመለከተ ተመሳሳይ አረዳድ እንዲኖር ማስቻል ነው። 

በዝግጅቱ መክፈቻ ባሰሙት ንግግር የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር ዶ/ር ዳንኤል በቀለ “የጣምራ ሪፖርቱ ግኝቶች ለክርክር ሊቀርቡ አይገባም። ሁሉም የግጭቱ ተሳታፊ ወገኖች በጦርነቱ ለተከሰቱ ጥሰቶች ያለባቸውን ኃላፊነት ሊያምኑና ሊቀበሉ እና ፍትሕ ለማስገኘት የሚያስፈልጉ እርምጃዎችን ሊወስዱ ይገባል” ብለዋል። አክለውም በዝግጅቱ የተሳተፉ ሁሉም አካላት ያለምንም ቅድመ ሁኔታ የሪፖርቱን ምክረ ሃሳቦች እንዲደግፉ ጥሪ አቅርበው፣ “በተለይም በግጭቱ የተሳተፉ ወገኖች የሪፖርቱን ምክረ ሃሳቦች ተቀብለው ለመተግበር የሚያስፈልጉትን እርምጃዎች እንዲወስዱ ግፊት ሊያደርጉ ይገባል” ብለዋል። 

የተ.መ.ድ. ከፍተኛ ኮሚሽነር የሰብአዊ መብቶች ጽሕፈት ቤት (UNOHCHR) የምሥራቅ አፍሪካ ጽ/ቤት ተወካይ ማርሴል አክፖቮ በበኩላቸው በጣምራ ሪፖርቱ የተመለከቱትን ምክረ ሃሳቦች የማስፈጸምና የመተግበር ኃላፊነት ያለባቸው አካላት በሙሉ ሚናቸውን እንዲጫወቱ ጥሪ አቅርበዋል። በተጨማሪም “ዓለም አቀፍ ሕጋዊ ማዕቀፎችንና ደረጃዎችን በሙሉ እስካሟሉ ድረስ፣ ተጠያቂነትን ለማምጣት ሀገር በቀልና ሀገራዊ መፍትሔዎች ቅድሚያ የሚሰጣቸው ይሆናል። ስለሆነም መንግሥታት ሰብአዊ መብቶችን የመጠበቅ ያለባቸውን ቀዳሚ ኃላፊነት ለመወጣት ተነሳሽነትና ፖለቲካዊ ፍላጎት ካሳዩ፣ ሊኖርብን የሚችሉ ማንኛውንም ጥርጣሪዎች ወደ ጎን ብለን ልንደግፋቸውና ልናበረታታቸው ይገባል” ብለዋል።

የእንግሊዝኛውን ቅጂ እዚህ ያንብቡ