በኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) አዘጋጅነት ነጻነታቸውን ከሕግ አግባብ ውጪ እና በዘፈቀደ የተነፈጉ ሰዎች መብቶች ላይ ያተኮረ ሕዝባዊ የአቤቱታ መቀበያ መድረክ ከሰኔ 27 እስከ ሰኔ 30 ቀን 2014 ዓ.ም. በሃዋሳ ከተማ መካሄዱ የሚታወስ ነው።  መሰል ብሔራዊ ምርመራዎች በሌሎች ክልሎች ለማካሄድ በተያዘው እቅድ መሰረት ከታኅሣሥ 11 እስከ 14 ቀን 2015 ዓ.ም. በጂግጂጋ ከተማ ሕዝባዊ የአቤቱታ ቅበላ ይካሄዳል። 

ሕዝባዊ የአቤቱታ መቀበያ መድረክ ግልጽ እና ሕዝባዊ ተሳትፎ የሚደረግበትና መብቶቻቸው የተጣሱ ተጎጂዎች፣ ምስክሮች፣ ሌሎች ባለድርሻ አካላት እንዲሁም የሚመለከታቸው የመንግሥት አካላት በተገኙበት የሚከናወን የምርመራ ስልት ነው። በሀገር አቀፍ ደረጃ ወይም በበርካታ አካባቢዎች የሚታዩ ውስብስብና ተደጋጋሚ የሆኑ የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶችን በጥልቀት ለመመርመር እና ሰፋ ያሉ መፍትሔዎችን ለማፈላለግ የሚጠቅምም ዘዴ ነው። በተለይ በአንድ ተቋም በበርካታ አካባቢዎች በተደጋጋሚ የሚፈጸሙ፣ ለመመርመር አዳጋች የሆኑ የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶችን ለመመርመር ምቹ ሁኔታን የሚፈጥር እና ትኩርት ያልተሰጣቸውን ወይም አነስተኛ የሕዝብና የፖለቲካ ትኩረት የተሰጣቸውን የሰብአዊ መብቶች ጉዳዮች ጎልተው እንዲታዩ እና የሚሹትን ትኩርት አግኝተው መፍትሔ እንዲገኝላቸው የሚያስችል መንገድ ነው።  

ኢሰመኮ በሃዋሳ ከተማ ባዘጋጀው ሕዝባዊ የአቤቱታ መቀበያ መድረክ ከ30 በላይ የሚሆኑ ተጎጂዎችን አቤቱታና ደርሶብናል ያሉትን የሰብአዊ መብቶች ጥሰት አድምጧል፡፡ ከተነሱ የሰብአዊ መብቶች ጥሰት መካከል፤ ያለክስ እና ያለ ፍርድ ቤት ትዕዛዝ በተደጋጋሚ እና ለረጅም ጊዜ የታሰሩ፣ “የፓለቲካ ልዩነትን መሰረት ያደረገ” መሆኑ የተገለጸ እና ከሕግ አግባብ ውጪ እና በዘፈቀደ ለተደጋጋሚ እና ለተራዘመ ቅድመ ክስ እስር የተዳረጉ፣ ጭካኔ የተሞላበትና አሰቃቂ አያያዝ እንደደረሰባቸው የገለጹ እንዲሁም በፖሊስ ጣቢያ እና በማረሚያ ቤት ቆይታቸው በተደጋጋሚ ሕክምና ተከልክለው ለጤና እክል የተዳረጉ ይገኙበታል፡፡  

ታኅሣሥ 11 ቀን 2015 ዓ.ም. በጂግጂጋ የጀመረው ሕዝባዊ የአቤቱታ መቀበያ መድረክ ላይ በተመሳሳይ ጉዳዮች ዙሪያ ውይይት ይደረጋል። በመድረኩ የዩኒቨርሲቲ ተወካዮች፣ የሲቪክ ማኅበራት፤ የሃይማኖት አባቶች እንዲሁም የጎሳ መሪዎች የሚገኙ ሲሆን ከተለያዩ ዞኖች በዋናነት ጉዳዩ የሚመለከታቸው የመንግሥት ተወካዮች በተለይም ከፍትሕ ዘርፉ ተወክለው የሚሳተፉ ባለሥልጣናት ይገኛሉ። 

ሕዝባዊ የአቤቱታ መቀበያ መድረኩ የሚመራው በኢሰመኮ ምክትል ዋና ኮሚሽነር ራኬብ መሰለ፣ የሲቪል፣ የፖለቲካ እና ማኅበራዊ-ኢኮኖሚያዊ መብቶች ኮሚሽነር አብዲ ጅብሪል እና በሴቶች እና ሕፃናት መብቶች ኮሚሽነር መስከረም ገስጥ ነው። በተጨማሪም ሌሎች የኮሚሽኑ አመራሮች፣ ከፍተኛ ባለሙያዎች፣ አማካሪዎች እና ሠራተኞች ከዚሁ መድረክ ጋር የተያያዙ በርካታ ተግባራቶችን በማከናወን ይሳተፋሉ። 

የኢሰመኮ ምክትል ዋና ኮሚሽነር ራኬብ መሰለ በጂግጂጋ የሚካሄደውን ሕዝባዊ የአቤቱታ መቀበያ መድረክ ለማስጀመር በተዘጋጀው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ባሰሙት ንግግር፤ ብሔራዊ ምርመራ የፍርድ ሂደት ሳይሆን ኮሚሽኑ በሰዎች ላይ የደረሰውን የሰብአዊ መብቶች ጥሰት በመስማት ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በመመካከር መፍትሔ የሚያፈላልግበት መንገድ ነው ሲሉ አብራርተዋል፡፡ አክለውም ኮሚሽኑ በመድረኩ ላይ የቀረቡ አቤቱታዎች ላይ ተጨማሪ መረጃዎችን እና ማስረጃዎችን በማሰባሰብ፣ በመመዘን፣ በዓለም አቀፍ አጣሪ ኮሚሽኖች ጥቅም ላይ የሚውለውን “ምክንያታዊ አሳማኝነት” ተብሎ የሚታወቀውን የማስረጃ ምዘና መስፈርትን በመጠቀም የሚሰንድና የመፍትሔ አቅጣጫ የሚጠቁም ምክረ ሃሳብ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትን ጨምሮ ለሚመለከታቸው የፍትሕ አካላትና በየደረጃው ለሚገኙ የመንግሥት መዋቅሮች በዝርዝር እንደሚቀርብ አስረድተዋል።  

ዝግጅቱ የነጻነት መብታችን ከሕግ አግባብ ውጪ ወይም በዘፈቀደ ተነፍጓል የሚሉ ሰዎች ለሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት እና ለሕዝብ ማካፈል እንዲችሉ እና በቀጣይ መሰል ውስብስብ የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶች ለመቀነስ፣ ተፈጽመው ሲገኙ ተጎጂዎች የሚካሱበት እንዲሁም አጥፊዎች ተጠያቂ የሚደረጉበት ጠንካራ ሕግ፣ ተቋም እንዲሁም አሠራር እንዲኖር ለማድረግ ኮሚሽኑ የሚያደርገው ጥረት አካል ነው፡፡