የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ከኢንተርናሽናል ሚዲያ ሳፖርት (International Media Support) ጋር በመተባበር በጋዜጠኞች የሕግ ጥበቃዎች ላይ የግንዛቤ ማስጨበጫ ውይይት ሐምሌ 17 ቀን 2017 ዓ.ም. በአዲስ አበባ አካሂዷል ውይይቱ በጋዜጠኞች የሕግ ጥበቃ (ከለላ) እና ሐሳብን በነጻነት የመግለጽ መብት ላይ ያሉ ዓለም አቀፍ እና ሀገራዊ ሕጎችን ለባለድርሻ አካላት ለማስገንዘብ እና በአፈጻጸሙ ላይም የጋራ መግባባት ለመፍጠር ያለመ ነው።




በመድረኩ ሐሳብን በነጻነት የመግለጽ መብትን የተመለከቱ ዓለም አቀፍ እና ሀገራዊ የሕግ ማዕቀፎች፣ በጋዜጠኞች የሕግ ጥበቃ (ከለላ) ላይ የተደረጉ የቅርብ ጊዜ ለውጦች፣ ክፍተቶች፣ የመንግሥት ተቋማት ኃላፊነቶች፣ የመገናኛ ብዙኃን ነጻነት እና ሐሳብን የመግለጽ መብት ላይ ኢሰመኮ ባከናወናቸው ክትትሎች የተለዩ ግኝቶች፣ የመብቶቹ መከበር ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ያለው ሚና፣ የመገናኛ ብዙኃን ነጻነቶች እና የሚጣሉባቸው ገደቦች፣ በጋዜጠኞች መብቶች ጥበቃ ላይ የሚስተዋሉ ችግሮች ቀርበው ውይይት ተደርጎባቸዋል።


በጋዜጠኝነት እና የማኅበረሰብ አንቂነት መካከል መደበላለቅ እንደሚስተዋል፣ ሐሰተኛ ስሞችን በመጠቀም በማኅበራዊ ትስስር ገጾች የጥላቻ ንግግር እንደሚሰራጭ፣ በማኅበረሰቦች መካከል ግጭት የሚያነሳሱ ይዘቶች መስተዋላቸው፣ ጋዜጠኞች በወንጀል ተግባር ተጠርጥረው በሕግ ሲጠየቁ በሙያቸው ምክንያት እንደታሰሩ ተደርጎ መረጃ የማስተላለፍ ሁኔታዎች መኖራቸው በውይይቱ ተገልጿል። ጋዜጠኞች መደበኛ ሥራቸውን በሚያከናውኑበት ጊዜ ለሀገር እና ለሕዝብ ደኅንነት ቅድሚያ መስጠት እንደሚገባቸውና ተልዕኳቸውን በአግባቡ እንዲወጡ ስልጠና እና የዐቅም ግንባታ ሥራዎችን ማከናወን አስፈላጊ መሆኑ ተመላክቷል። የባለድርሻ አካላት በትብብር መሥራት ሐሳብን የመግለጽ መብት እና የመረጃ ነጻነት ላይ የሚስተዋሉ ችግሮችን ለማስወገድ እንዲሁም በጋዜጠኞች ላይ የሚደርሱ የመብት ጥሰቶችን ለመከላከል እንደሚረዳም ተገልጿል።

በተጨማሪም ሐሳብን የመግለጽ መብትን እና የመገናኛ ብዙኃን ነጻነትን ለማስጠበቅ የወጡ ሕጎችን ተግባራዊ ለማድረግ የሚመለከታቸው አካላት ኃላፊነት እንዳለባቸው፣ የመገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎች ከመንግሥት ተቋማት መረጃ ለማግኘት ሲሞክሩ ክልከላ በሚገጥማቸው ጊዜ ለተቋሙ የበላይ ኃላፊዎች አቤቱታ በማቅረብ ምላሽ ማግኘት እንደሚችሉ ተጠቁሟል።

የኢሰመኮ የሲቪል፣ የፖለቲካ፣ የማኅበራዊ እና የኢኮኖሚ መብቶች ኮሚሽነር ዶ/ር አብዲ ጅብሪል የጋዜጠኞች መብቶች መከበርን እና መስፋፋትን በተሟላ ሁኔታ ተግባራዊ ለማድረግ ሐሳብን በነጻነት የመያዝና የመግለጽ መብት እና የመረጃ ነጻነት መሠረታዊ መብቶች ወሳኝ መሆናቸውን ገልጸዋል። ኢሰመኮ በርዕሰ ጉዳዩ ዙሪያ ተከታታይነት ያለው ክትትል እና የውይይት መድረኮችን በማካሄድ ለዘርፉ መብቶች መስፋፋት፣ ጥበቃና መከበር ተቋማዊ አስተዋጽዖ ማበርከቱን እንደሚቀጥል አሳውቀዋል። አክለውም ለጋዜጠኞች መብቶች ጥበቃ ሁሉም ባለድርሻ አካላት የበኩላቸውን ኃላፊነት እንዲወጡ እና በመገናኛ ብዙኃን ዘርፍ የተሰማሩ አካላት ትክክለኛ መረጃን እና ማስረጃን በመጠቀም ሐሳብን የመግለጽ መብታቸውን እንዲጠቀሙ ጥሪ አቅርበዋል።