የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ከኢንተርናሽናል ሚዲያ ሳፖርት (International Media Support) ጋር በመተባበር በጋዜጠኞች የሕግ ጥበቃ (ከለላ) ላይ ጥቅምት 25 ቀን 2018 ዓ.ም. በድሬዳዋ ከተማ ውይይት አካሂዷል። በውይይቱ ከሐረሪ እና ከሶማሊ ክልሎች እንዲሁም ከድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር የተወጣጡ የሕግ አስፈጻሚ አካላት፣ የመገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎች ማኅበራት፣ የግል እና የመንግሥት የመገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎች እና ተወካዮች ተሳትፈዋል።   

የውይይት መድረኩ ጥቅምት 4 ቀን 2018 ዓ.ም. በአርባ ምንጭ እንዲሁም ሐምሌ 17 ቀን 2017 ዓ.ም. በአዲስ አበባ በተመሳሳይ ጉዳይ ላይ የተካሄዱ ውይይቶች ቀጣይ ሲሆን፣ ሐሳብን በነጻነት የመግለጽ መብት፣ የመረጃ ነጻነት እንዲሁም የጋዜጠኞች የሕግ ጥበቃ (ከለላ) ላይ ያሉ ዓለም አቀፍ እና ሀገራዊ ሕጎችን በተመለከተ የባለድርሻ አካላትን ግንዛቤ ለማሳደግ ያለመ ነው።

የውይይቱ ተሳታፊዎች

በመድረኩ ሐሳብን በነጻነት የመግለጽ መብትን የተመለከቱ ዓለም አቀፍ እና ሀገራዊ የሕግ ማዕቀፎች፣ በጋዜጠኞች የሕግ ጥበቃ (ከለላ) ላይ የተደረጉ የቅርብ ጊዜ ለውጦች፣ ክፍተቶች፣ የመንግሥት ተቋማት ኃላፊነቶች፣ የመገናኛ ብዙኃን ነጻነት እና ሐሳብን የመግለጽ መብት ላይ ኢሰመኮ ባከናወናቸው ክትትሎች የተለዩ ግኝቶች፣ የመብቶቹ መከበር ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ያለው ሚና፣ የመገናኛ ብዙኃን ነጻነት እና የሚጣሉባቸው ገደቦች እና በጋዜጠኞች መብቶች ጥበቃ ላይ የሚስተዋሉ ችግሮች ላይ ያተኮሩ ሁለት የውይይት መነሻ ጽሑፎች ቀርበው ውይይት ተደርጎባቸዋል።

የውይይቱ ተሳታፊዎች

በክልል እና በከተማ አስተዳደሮች ደረጃ ያሉ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች መረጃ የመስጠት ሕገ መንግሥታዊ ግዴታ ያለባቸው መሆኑን አለመረዳት፣ የመንግሥት አካላት ከቦታ ቦታ ለሥራ የሚንቀሳቀሱ ጋዜጠኞችን የፈቃድ ደብዳቤ የሚጠይቁ መሆኑ፣ ጋዜጠኞች ከመንግሥት ተቋማት በቂ መረጃዎችን ለማግኘት የሚቸገሩ መሆናቸው፣ ማኅበራዊ ሚዲያዎችን በመጠቀም የሚሰራጩ የጥላቻ እና ሐሰተኛ ንግግሮች እንዲሁም ግጭት የሚያነሳሱ መልእክቶች መረጃ የማግኘት መብት ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ መፍጠራቸው በውይይት መድረኩ ተነስቷል። በተጨማሪም ሕግ ተላልፈው የሚገኙ ጋዜጠኞች እና የመገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎች ላይ የሚደረጉ የፖሊስ ምርመራዎች በተገቢው ፍጥነት፣ ዐቅምና ግንዛቤ ላይ ተመሥርተው የሚከናወኑ አለመሆናቸው ተገልጿል። ጋዜጠኞች ሐሳብን በነጻነት የመግለጽ እና መረጃ የማግኘትት መብት ከግዴታ ጋር እንደሚመጣና ተጠያቂነትን እንደሚያስከትል በመረዳት ተልዕኳቸውን በአግባቡ እንዲወጡ እና ለዚህም የዐቅም ግንባታ ሥራዎችን ማከናወን አስፈላጊ መሆኑ ተመላክቷል።

ዶ/ር አብዲ ጅብሪል፣ የኢሰመኮ የሲቪል፣ የፖለቲካ፣ የማኅበራዊ እና የኢኮኖሚ መብቶች ኮሚሽነር

የኢሰመኮ የሲቪል፣ የፖለቲካ፣ የማኅበራዊ እና የኢኮኖሚ መብቶች ኮሚሽነር ዶ/ር አብዲ ጅብሪል ሐሳብን በነጻነት የመግለጽ እና መረጃ የማግኘት መብቶች ለሌሎች ሰብአዊ መብቶች መከበር አስፈላጊ መሆናቸውን አስታውሰው፣ ጋዜጠኞች በቂ የሕግ ጥበቃ (ከለላ) የሚያገኙበት ነጻ የመገናኛ ብዙኃን ከባቢ መፈጠሩን ለማረጋገጥ ሁሉም ባለድርሻዎች በጋራ መሥራት እንደሚገባቸው እና ኢሰመኮ በዘርፉ የሚያከናውናቸውን የውትወታ ተግባራት አጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸዋል።