የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ደኅንነቱ የተጠበቀ እና ጤናማ የሥራ ሁኔታ መብትን በተመለከተ የግንባታ ሥራ ዘርፍ ላይ ያተኮረ ባለ 36 ገጽ የሰብአዊ መብቶች ሁኔታ ክትትል ሪፖርት ዛሬ ይፋ አድርጓል።
ደኅንነቱ እና ጤንነቱ የተጠበቀ የሥራ ሁኔታ የማግኘት መብት ያለምንም መድልዎ በማንኛውም የሥራ ዘርፍ እና የቅጥር ዓይነት ለሚሠሩ ሠራተኞች የተሰጠ መብት ሲሆን፣ ከፍትሐዊ እና ምቹ የሥራ ሁኔታዎች መብት መሠረታዊ ክፍሎች መካከል አንዱ እና ከሌሎች መብቶች በተለይም ከአካላዊ እና አእምሯዊ ጤና መብት ጋር የተቆራኘ ነው። የግንባታ ኢንዱስትሪ ከፍተኛ የሥራ ላይ አደጋዎች የሚከሰቱበት እና ለደኅንነት እና ለጤንነት አስጊ ከሆኑ ዘርፎች መካከል በመሆኑ፣ ደኅንነቱ የተጠበቀ እና ጤናማ የሥራ ሁኔታ መብት ላይ ሀገር አቀፍ የሕግና ፖሊሲ ማዕቀፎችን እና አተገባበራቸውን ለመፈተሽ ጥሩ ማሳያ ነው።
ሪፖርቱን ለማዘጋጀት በአጠቃላይ ከ182 ሰዎች መረጃ፣ ሰነዶች እና ማስረጃዎች የተሰበሰቡ ሲሆን፣ 44 ከሚመለከታቸው የመንግሥት ቢሮዎች፣ 33 ከሕንጻ ተቋራጮች፣ 72 የግንባታ ሠራተኞች እና 10 ጉዳዩ ከሚመለከታቸው መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማት ተሳተፈዋል። በተጨማሪም በጉዳዩ ላይ በተዘጋጀ የውይይት መድረክ የተለያዩ ተቋማትን እና ባለድርሻዎችን የወከሉ 23 ተሳታፊዎች ተካተዋል፡፡ ክትትሉ በአዳማ፣ በአዲስ አበባ፣ በባሕር ዳር፣ በሃዋሳ እና በጅግጅጋ ከተሞች የተደረገ ነው።
በሁሉም የሥራ ዘርፎች ተፈጻሚ መሆን ካለባቸው ዓለም አቀፍ እና አህጉራዊ ጤናማ እና ደኅንነቱ የተጠበቀ የሥራ ሁኔታ/ከባቢ ከማግኘት መብት በተጨማሪ፣ በተለይ በሀገር አቀፍ ደረጃ ለግንባታ ሥራ ዘርፉ በአዋጅ እና በመመሪያ ደረጃ የተደነገጉ እና መንግሥታዊ ተቋማትም ሆነ እና ቀጣሪዎች (የግንባታ ተቋራጮች) ሊተገብሯቸው የሚገቡ መስፈርቶች እና መመሪያዎች አሉ። ሆኖም በአስፈጻሚ አካላት ጭምር ያለው የግንዛቤ እጥረት ይህም የፈጠረው ሕጉን ለማስፈጸም እና ለማረጋገጥ የሚወሰዱ እርምጃዎች ዝቅተኛ መሆን ለእነዚህ መስፈርቶች አለመከበር ዋነኛው ምክንያት መሆኑን ክትትሉ አረጋግጧል። ለምሳሌ ለሴት ሠራተኞች ከባድ ወይም ለጤና ጎጂ የሆኑ ወይም የመውለድ ሁኔታን የሚያውኩ ሥራዎችን የተመለከቱ ድንጋጌዎች፣ በተለይም የሴት ሠራተኞችን ጉልበት በመጠቀም የሚካሄድ ማናቸውም ክብደትን ከቦታ ቦታ የማንቀሳቀስ፣ የመሸከም፣ የማጓጓዝ፣ የማንሳት፣ የማውረድ፣ የማውጣት፣ የመጎተት፣ የመሳብና የመሳሰሉት ሥራዎች፣ የክብደት መጠን ጣሪያ እና የመሳሰሉት በአብዛኛው ክትትል በተደረገባቸው የግንባታ ሥራዎች ሲጣስ አልያም በተሟላ መልኩ አለመተግበሩ ተመልክቷል።
በተጨማሪም ደኅንነቱ የተጠበቀ እና ጤናማ የሥራ ከባቢ ከማግኘት መብት የተመለከቱ ድንጋጌዎችን የመተግበር ኃላፊነት ያለባቸው ተቋማት ተቋማዊ ችግሮች፤ ጉዳዩ የሚመለከታቸው አካላትን አስተባብሮ እና አቀናጅቶ የሚመራ ጠንካራ ሥርዓት አለመኖር፤ ደካማ የመረጃ አያያዝ እና የአጠቃቀም ሥርዓት፤ የግንባታ ግዢ ጨረታዎች ዝቅተኛ ዋጋን መሠረት ያደረጉ መሆናቸው እና ሠራተኞች ሊያጋጥሟቸው የሚችሉ በሂደት የሚገለጡ የጤና መጓደሎች እና በሽታዎች ችላ የተባሉ መሆናቸው መሻሻል ከሚገባቸው ክፍተቶች መካከል ተጠቅሰዋል፡፡
በግንባታ ሥራ ዘርፍ ደኅንነቱ የተጠበቀ እና ጤናማ የሥራ ሁኔታ መብት በተሻለ ሁኔታ እንዲተገበር እና ከላይ የተዘረዘሩትን ተግዳሮቶች ለመቅረፍ ይረዳሉ በማለት ከተለዩ የአሠራር፣ የፖሊሲ እና የሕግ ማሻሻያ ምክረ ሐሳቦች መካከል ሕጎችን ማስተዋወቅ እና የመብቱን ተፈጻሚነት ለማረጋገጥ የሚረዱ ሥርዓቶችን መዘርጋት እንዲሁም የሙያ ደኅንነት እና ከጤንነት ጋር ተያያዥነት ያላቸውን የዓለም አቀፍ የሥራ ድርጅት ስምምነቶችን በማጽደቅ ሥራ ላይ ማዋል የሚሉት ይገኙበታል።
የኢሰመኮ የሲቪል፣ የፖለቲካ እና ማኅበራዊ-ኢኮኖሚያዊ መብቶች ኮሚሽነር ዶ/ር አብዲ ጅብሪል “በግንባታ ሥራ ዘርፍ ደኅንነቱ የተጠበቀ እና ጤናማ የሥራ ሁኔታ መብትን ለማረጋገጥ ጉዳዩ የሚመለከታቸውን አካላት አስተባብሮ እና አቀናጅቶ የሚመራ ጠንካራ ሥርዓት መዘርጋት ያስፈልጋል” ብለዋል። አክለውም “ሕጎችን ከማርቀቅ ተፈጻሚነታቸውን እስከ ማረጋገጥ ባለው ሂደት ውስጥ ሁሉም የሚመለከታቸው ተቋማት በመናበብ እና በትብብር መሥራት አለባቸው” ብለዋል።