የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) በሚያዝያ 27 ቀን 2015 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ከተማ በጎዳና ላይ ያሉ ሕፃናት በጅምላ ተይዘው የሚቆዩበትን ሁኔታ በተመለከተ እንዲሁም መስከረም 8 ቀን 2016 ዓ.ም. በሸገር ከተማ ገላን ክፍለ ከተማ ሲዳ አዋሽ ወረዳ በሚገኘው ማቆያ ማእከል ተይዘው የነበሩ ውሎና አዳራቸውን በጎዳና ያደረጉ ሰዎችን (በተለምዶ አጠራር ‘‘ጎዳና ተዳዳሪዎች’’ ተብለው የሚታወቁ) ሁኔታ አስመልክቶ ክትትል በማድረግ የተለዩ ክፍተቶችን እና ምክረ ሐሳቦችን የያዘ መግለጫ ማውጣቱ ይታወሳል።
ኢሰመኮ በታኅሣሥ ወር 2017 ዓ.ም. ባደረጋቸው ክትትሎች በአዲስ አበባ ከተማ በተለምዶ “ቃሊቲ አካባቢ” ተብሎ በሚጠራው የአሽከርካሪዎች ማሰልጠኛ አካባቢ ባለ ሰፊ መጋዘን ውስጥ ከጎዳና ላይ የተነሱ በርካታ ሰዎች መኖራቸውንና ይህ ሰዎችን የመያዝና ወደ ማቆያ ማእከል/ቦታ የማስገባት ድርጊት አሁንም መቀጠሉን ተገንዝቧል፡፡ ወደ ማቆያው ከገቡት ሰዎች መካከል በማእከሉ ከመቆየት እና የእርሻ ሥራ ከመሥራት እንዲመርጡ በማድረግ፤ የእርሻ ሥራ ለመሥራት የመረጡ ሰዎች በተለያዩ አካባቢዎች ወደሚገኙ እርሻ ጣቢያዎች ተወስደው እንዲሠሩ እንደሚደረግ ለመገንዘብ ተችሏል። ይህም የነጻነት መብታቸውን ጨምሮ ሌሎች መሠረታዊ የሰብአዊ መብቶቻቸውን የሚጥስ ነው።
በአዲስ አበባ ከተማ የሚከበሩ ሕዝባዊና ሃይማኖታዊ በዓላት፣ የሚደረጉ ዓለም አቀፋዊና አህጉራዊ ጉባኤዎች እንዲሁም ከሌሎች ተመሳሳይ ኹነቶች ጋር በተያያዘ ውሎና አዳራቸውን በጎዳና ላይ ያደረጉ ሰዎችን በኃይል በማንሳት በአንድ ስፍራ እንዲቆዩ የማድረግ አሠራር እንዲቆም፤ ወደመጡባቸው አካባቢዎች የመመለስ እና የመልሶ ማቋቋም ሥራዎች ሰብአዊ መብቶቻቸውን ባከበረ መልኩ ማከናወን እንደሚገባ እና ችግሩ ሁሉ አቀፍ የፖሊሲ ምላሽ የሚያስፈልገው መሆኑን በተለያዩ ጊዜያት በተካሄዱ የኢሰመኮ ክትትሎች ተጠቁሟል፡፡
ኢሰመኮ ለችግሩ ዘላቂ መፍትሔ ለመስጠት ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ከሚያደርገው ውትወታ ጎን ለጎን የነጻነት መብትን ከማክበር እና ከማስከበር አኳያ እንዲሁም በጊዜያዊ ማቆያ ማእከሉ ከንጽሕና እና ከጤና አጠባበቅ ጋር በተያያዘ በሰዎች ሕይወትና ጤና ላይ አደጋ የሚጥሉ ሁኔታዎች እንዳይፈጠሩ ከአዲስ አበባ ከተማ ሰላምና ጸጥታ ቢሮ እንዲሁም ከአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ጋር ውይይቶችን በማድረግ ጉዳዩን በመከታተል ላይ ይገኛል፡፡
የኢሰመኮ ተጠባባቂ ዋና ኮሚሽነር ራኬብ መሰለ “ኢሰመኮ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር የሚያደርገው ክትትል እንደተጠበቀ ሆኖ በቀጣይ ከሚዘጋጁ የአደባባይ በዓላት እንዲሁም ዓለም አቀፋዊና አህጉራዊ ስብሰባዎች ጋር በተያያዘ ጉዳዩ ከፍተኛ ትኩረት የሚሻ በመሆኑ፣ ውሎና አዳራቸውን በጎዳና ላይ ያደረጉ ሰዎችን በግዳጅ ወደ ማቆያ ማእከል/ቦታ አስገብቶ መያዝ ወይም ያለፈቃዳቸው ወደተለያዩ አካባቢዎች መውሰድ/እንዲሄዱ ማስገደድ የነጻነት መብት እና ከቦታ ቦታ በነጻነት የመንቀሳቀስን ጨምሮ ሌሎች የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶችን ስለሚያስከትል በአስቸኳይ ሊቆም ይገባል’’ ብለዋል። አክለውም ወደማቆያ በፈቃደኝነት ለሚገቡ ሰዎች የሚዘጋጁ የተሐድሶ ማእከላት መሠረተ ልማት የተሟላላቸው፣ ንጽሕናቸው የተጠበቀ፣ ለደኅንነት እና ለጤና ሥጋት የማይፈጥሩ ተደርገው የተዘጋጁ መሆናቸው ሊረጋገጥ እንደሚገባ አሳስበዋል።