የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ከተፎካካሪ/ተቃዋሚ ፓርቲዎች ውስጥ በእናት ፓርቲ እና በባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ ፓርቲ የመሰብሰብ መብት መከልከል እንዲሁም የጎጎት ለጉራጌ አንድነት እና ፍትሕ ፓርቲ ምሥረታን ተከትሎ በፓርቲው አስተባባሪዎች ላይ ስለደረሰው እንግልትና እስራት ሲከታተል ቆይቷል። ከተለያዩ የመረጃ ምንጮች በተጨማሪም ጉዳዩ የሚመለከታቸውን የመንግሥት አካላት አነጋግሯል፡፡ በዚህም መሠረት ለመረዳት እንደተቻለው፡-
- እናት ፓርቲ የካቲት 26 ቀን 2015 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ከተማ በቅድስት ሥላሴ ዩኒቨርሲቲ ግቢ ውስጥ በሚገኘው አዳራሽ ሊያካሂደው የነበረው የፓርቲው ጠቅላላ ስብሰባ እንዲሁም ባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ ፓርቲ መጋቢት 3 ቀን 2015 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ከተማ በጋምቤላ ሆቴል ውስጥ ሊያካሂድ የነበረው የፓርቲው ጠቅላላ ስብሰባ እንዳይካሄድ መስተጓጎሉን፣
- ለፓርቲዎቹ ስብሰባ ተዘጋጅተው የነበሩ ቦታዎች ጥበቃዎችና ሠራተኞች ማንነቱ ተለይቶ ካልታወቀ የበላይ አካል ተሰጥቷል ባሉት ትዕዛዝ መሠረት ስብሰባዎቹን መከልከላቸው እና ስብሰባዎቹ ሊካሄድባቸው በነበሩበት አካባቢዎች የደንብ ልብስ በለበሱ የፖሊስ አባላት እና ሲቪል ልብስ በለበሱ የጸጥታና ደኅንነት አባላት ስብሰባው እንዲካሄድ ከማገዝና ከማሳለጥ ይልቅ የማደናቀፍ ተግባር መከናወኑን፣
- የጎጎት ለጉራጌ አንድነት እና ፍትሕ ፓርቲ ምሥረታን ተከትሎ የፓርቲ አስተባባሪዎች ላይ እስራት እና እንግልት የተፈጸመ መሆኑን ኢሰመኮ ተገንዝቧል፡፡
ኢሰመኮ ከዚህ በፊት ባደረጋቸው ክትትሎች ሌሎች ተፎካካሪ/ተቃዋሚ ፓርቲዎችም ለምሳሌ የኦሮሞ ነጻነት ግንባር ፖለቲካ ፓርቲ እና የቁጫ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ በተለይም የአመራር አባሎች ላይ የተደረገውንም ገደብ፣ ማዋከብ እና እስራት ያስታውሳል፡፡
የፖለቲካ ፓርቲዎች ጠቅላላ ጉባዔዎቻቸውንም ሆነ ሌሎች የድርጅቶቻቸውን ስብሰባዎች እንዳያደርጉ በመንግሥትም ሆነ በሌሎች አካላት የሚደረጉ ወከባዎች፣ ክልከላዎችና እገዳዎች የሕግ እና የመሰብሰብ፣ የመደራጀት እና የመሳተፍ መብቶች ጥሰቶች ናቸው።
ማንኛውም ሰው የመሰብሰብ እና የመደራጀት ነጻነት አለው። ሰብአዊ መብቶች በሁሉም ጊዜ ለሁሉም ሰዎች እኩል መከበር፣ መጠበቅ እና መሟላት ያለባቸው ቢሆንም አንዳንድ መብቶች ከሌሎች በተለየ በዴሞክራሲ እና ሕዝባዊ ተሳትፎዎች ውስጥ ሂደቱን አሳታፊ፣ ነጻ እና ፍትሐዊ ከማድረግ እና ዴሞክራሲያዊ የሆነ ሥርዓት ከመገንባት አንጻር አስፈላጊነታቸው ጎልቶ ይወጣል። እንዲሁም የመሰብሰብ መብት ከመደራጀት መብት ጋር ከፍተኛ ቁርኝት አለው፡፡ የመደራጀት መብት የግለሰቦች ተግባብቶና ተደራጅቶ የጋራ ጥቅምን በጋራ የመግለጽ፣ የማራመድ፣ የማስከበር እና የመከላከል መብትን የሚያካትት ሲሆን ይህንን ለማሳካት ደግሞ የመሰብሰብ መብት ቁልፍ መሣሪያ ነው፡፡
የመሰብሰብ እና የመደራጀት መብቶች ሌሎች በርካታ መብቶችን ለመጠቀም፣ ሐሳብን በነጻነት የመግለጽ እና በሕዝብ ጉዳዮች ላይ የመሳተፍ መብቶችን ለማስከበር እንደ መሣሪያ ሆነው ያገለግላሉ። በዚህ መሠረት የመሰብሰብ እና የመደራጀት መብቶች ዜጎች በመረጡት የፖለቲካ አመለካከት ለመደራጀት፣ የፖለቲካ ፓርቲ ለመመሥረት እና በሕዝብ ጉዳዮች ውስጥ ለመሳተፍ አስፈላጊ ናቸው፡፡ በመሆኑም የመሰብሰብ መብት በተለይ ለፖለቲካ ፓርቲዎች ህልውና አስፈላጊ ነው፡፡
በዓለም አቀፍ ድንጋጌዎች መሠረት የመሰብሰብ መብት ላይ የሚደረጉ ገደቦች እና ክልከላዎች በሕግ በግልጽ የተደነገጉ እንዲሁም የሚገደቡበት ምክንያት ለብሔራዊ ደኅንነት፣ የሕዝብ ደኅንነት፣ የሕዝብ ጤና ወይም ሞራል እንዲሁም የሌሎችን መብት ለመጠበቅ ሲባል እና የገደቦቹ አስፈላጊነት በአንድ ዴሞክራሲያዊ ማኅበረሰብ ተቀባይነት ሲኖረውና ተመጣጣኝ ብቻ ሊሆን እንደሚገባ ያስቀምጣል። በዚህ መሠረት ዜጎች የመሰብሰብ መብታቸውን እውን ለማድረግ ሲንቀሳቀሱ መንግሥት እነዚህ የተጠቀሱትን የሕጋዊነት፣ ሕጋዊ ቅቡልነት ባላቸው ምክንያቶች፣ አስፈላጊነት እና ተመጣጣኝነት ቅድመ ሁኔታዎችን ያላሟሉ፣ ድንገተኛ እና ከታሰበላቸው ዓላማ በላይ የሆኑ እርምጃዎችን ከመውሰድ የመቆጠብ ግዴታ አለበት።
በሌላ በኩል መንግሥት ዜጎች የመሰብሰብ መብታቸውን ተግባራዊ እንዲያደርጉ የማመቻቸት እና ለተሳታፊዎች ጥበቃ እና ከለላ የማድረግ ግዴታ አለበት፡፡ ከመንግሥትም ሆነ ከሦስተኛ ወገን የሚመጡ ማስፈራራቶች እና ዛቻዎች እንዲሁም ማጉላላቶችን በመከላከል እና እነዚህ ጣልቃገብነቶች በአግባቡ በማጣራት እና ምርመራ በማድረግ ተጠያቂነትን የማስፈን ግዴታ አለበት፡፡ በተጨማሪም ሕጋዊ መሠረት የሌላቸው በተደጋጋሚ የሚፈጸሙ ክልከላዎችን በመጠቀም ዜጎች የመሰብሰብ መብታቸውን ከመጠቀም እንዲያፈገፍጉ ከማድረግ በመቆጠብ ምቹ ሁኔታዎችን መፍጠር ከመንግሥት የሚጠበቅ ግዴታ ነው።
የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር ዶ/ር ዳንኤል በቀለ “የፖለቲካ ፓርቲዎች የመሰብሰብ መብት እና የሰዎችን በሕዝባዊ ጉዳዮች ውስጥ የመሳተፍ መብታቸውን የሚገድቡ ተግባሮችን የመመርመርና ተጠያቂነትን የማረጋገጥ ኃላፊነት የመንግሥት ነው” ብለዋል፡፡