የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተ.መ.ድ.) የሰብአዊ መብቶች ምክር ቤት (United Nations Human Rights Council – UNHRC) በጥር ወር 2017 ዓ.ም. በተካሄደው 4ኛው ዙር ሁሉ-አቀፍ ወቅታዊ የግምገማ መድረክ (Universal Periodic Review- UPR) ወቅት በኢትዮጵያ ያለውን የሰብአዊ መብቶች አያያዝ ለማሻሻል የተሰጡ ምክረ ሐሳቦችን ሀገር ውስጥ ካለው ነባራዊ ዐውድ ጋር በማዛመድ ሀገራዊ የሰብአዊ መብቶች አጀንዳ አድርጎ በጋራ ለመደገፍ ያለመ የምክክር መድረክ ጥር 20 እና 21 ቀን 2017 ዓ.ም. አካሄደ። በመድረኩ በሰብአዊ መብቶች ዙሪያ የሚሠሩ የመንግሥት አካላት፣ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች፣ የጥናትና የምርምር ተቋማት፣ ሚዲያዎች እና ዩኒሴፍን ጨምሮ መንግሥታዊ ያልሆኑ ዓለም አቀፍ ተቋማት ተወካዮች ተሳትፈዋል።



ከዚህ ቀደም ከኅዳር 3 እስከ 6 ቀን 2017 ዓ.ም. በተ.መ.ድ. የሰብአዊ መብቶች ምክር ቤት 47ኛው መደበኛ ስብሰባ ወቅት የኢትዮጵያ 4ኛው ዙር ሁሉ-አቀፍ የሰብአዊ መብቶች ግምገማ በጄኔቫ፣ ስዊዘርላንድ መካሄዱ ይታወሳል። በዚህ ስብሰባ ኢትዮጵያ በ3ኛው ዙር የግምገማ መድረክ የተሰጧትን ምክረ ሐሳቦች ከመተግበር አንጻር እና የሰብአዊ መብቶች ሁኔታን በማሻሻል ረገድ በሀገር አቀፍ ደረጃ ያከናወነቻቸውን ተግባራት አስመልክቶ ሪፖርት አቅርባ በተ.መ.ድ. አባል ሀገራት የአቻ ለአቻ ግምገማ ሂደት አልፋለች። በዚህ ሂደት በኢትዮጵያ ያለውን የሰብአዊ መብቶች ሁኔታ ለማሻሻል መንግሥት ሊወስዳቸው የሚገቡ እርምጃዎችን በተለመከተ 114 የተ.መ.ድ. አባል ሀገራት 316 ምክረ ሐሳቦችን ሰጥተዋል። በዚህም መሠረት ከቀጣዩ 58ኛው የተ.መ.ድ. የሰብአዊ መብቶች ምክር ቤት ስብሰባ አስቀድሞ ኢትዮጵያ ከእነዚህ 316 ምክረ ሐሳቦች ውስጥ የተቀበለቻቸውን ለይታ እንደምታሳውቅ ይጠበቃል፡፡


በምክክር መድረኩ የሁሉ-አቀፍ ወቅታዊ ግምገማ ሂደት ለሰብአዊ መብቶች መከበር እና መስፋፋት ያለውን ጉልህ ጠቀሜታ እንዲሁም በኢሰመኮ፣ በተለያዩ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች እና መንግሥታዊ ባልሆኑ ዓለም አቀፍ ተቋማት ቀርበው የነበሩ ሪፖርቶች ላይ ገለጻ ተሰጥቷል። ይህንንም ተከትሎ በሴቶች እና ሕፃናት፣ በሲቪል እና ፖለቲካዊ መብቶች፣ በማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ መብቶች፣ በሽግግር ፍትሕና ተጠያቂነት እና የቀሩ ዓለም አቀፍ ስምምነቶችን ማጽደቅ ላይ ውይይት ተደርጓል። እንዲሁም እንደ ኢሰመኮ ያሉ ነጻ ተቋማትን ማጠናከር፣ በመንግሥት ተቋማት፣ በሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች እና በዓለም አቀፍ ድርጅቶች መካከል ያለውን ትብብር ማጠናከርን በተመለከተ የተሰጡ ምክረ ሐሳቦች በውይይቱ ተዳስሰዋል።


የመድረኩ ተሳታፊዎች የምክረ ሐሳቦቹ ተቀባይነት ማግኘት በመንግሥት እየተወሰዱ ያሉ መልካም እርምጃዎችን አጠናክሮ ለማስቀጠል እንዲሁም አሳሳቢ በሆኑ እና ትኩረት በሚሹ የሰብአዊ መብቶች ጉዳዮች ላይ የሕግ፣ የፖሊሲ እና የአሠራር ማሻሻያዎችን በማድረግ ተጨባጭ እርምጃዎች እንዲወሰዱ በማገዝ ሰብአዊ መብቶችን በኢትዮጵያ ለማስፋፋት እና ለማስከበር ጉልህ አስተዋጽዖ እንዳለው ገልጸዋል። በተጨማሪም ምክረ ሐሳቦቹን ከመቀበል ባለፈ በሚመለከታቸው የመንግሥት ተቋማት እቅዶች ውስጥ እንዲካተቱ ማድረግ፣ ተጨባጭ የሆኑ እርምጃዎች እንዲወሰዱ እና አፈጻጸማቸውን በተሟላ ሁኔታ መከታተል እንደሚያስፈልግ ተገልጿል።

የኢሰመኮ ምክትል ዋና ኮሚሽነር ራኬብ መሰለ በ4ኛው ዙር የሁሉ-አቀፍ ወቅታዊ የግምገማ መድረክ የተሰጡ ምክረ ሐሳቦችን ተቀብሎ መተግበር በኢትዮጵያ ያለው የሰብአዊ መብቶች ዐውድ ላይ አወንታዊ አስተዋጽዖ እንደሚያበረክት ግምት ውስጥ በማስገባት መንግሥት በተቻለ መጠን አብዛኛዎቹን ምክረ ሐሳቦች እንዲቀበል በዕለቱ ጥሪ አቅርበዋል። ኢሰመኮ የኢትዮጵያ መንግሥት የሚቀበላቸውን ምክረ ሐሳቦች በመጪው ዓመታት ለመተግበር የሚከናወኑ ተግባራትን ለመደገፍ ከመንግሥት እና ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር እንደሚሠራም ገልጸዋል።