የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ከነሐሴ 26 እስከ ጷጉሜን 4 ቀን 2017 ዓ.ም. በቤኒንሻንጉል ጉሙዝ ክልል በሚገኙ 3 የስደተኞች መጠለያ ጣቢያዎች የስደተኞች ሰብአዊ መብቶች አያያዝ፤ እንዲሁም ጥቅምት 17 እና 18 ቀን 2018 ዓ.ም. በክልሉ ኩምሩክ የስደተኞች መቀበያ ማእክል እና ኡራ የስደተኞች ሳይት ባከናወናቸው የስደተኞች ምዝገባና ሰነድ ላይ ያተኮረ የምክረ ሐሳብ አፈጻጸም ክትትሎች በለያቸው ግኝቶች ላይ ጥቅምት 21 ቀን 2018 ዓ.ም. በአሶሳ ከተማ ከባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት አካሂዷል።
በውይይቱ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ፍትሕ ቢሮ፣ የአሶሳ ዩኒቨርሲቲ፣ የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት፣ የስደተኞችና ከስደት ተመላሾች አገልግሎት፣ የተ.መ.ድ. የስደተኞች ጉዳይ ከፍተኛ ኮሚሽነር (United Nations High Commissioner for Refugees (UNHCR)) እንዲሁም ሌሎች መንግሥታዊ እና መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ተወካዮችና የሥራ ኃላፊዎች ተሳትፈዋል።
በውይይቱ ኢሰመኮ በኡራ የስደተኞች ሳይት፣ ሸርቆሌ፣ ባምባሲ እና ጾሬ የስደተኞች መጠለያ ጣቢያዎች ባከናወነው ክትትል የለያቸው አሳሳቢ የሰብአዊ መብቶች ጉዳዮች እና ምክረ ሐሳቦች ለተሳታፊዎች ቀርበዋል። በጾሬ እና ኡራ ሳይቶች ለስደተኞችና ጥገኝነት ጠያቂዎች የዲጂታል መታወቂያ ካርድ መስጠት መጀመሩ እንዲሁም የክልሉ መንግሥት በኡራ ሳይት ለሚገኙ ስደተኞች እና ለስደተኞች ተቀባይ የማኅበረሰብ ክፍሎች ለግብርና ሥራ የሚሆን 300 ሄክታር መሬት መስጠቱ የሚበረታታ ተግባር መሆኑ ተገልጿል።

በሌላ በኩል የኩምሩክ የስደተኞች መቀበያ በጊዜያዊነት ጥገኝነት ጠያቂዎችን መቀበል ማቆሙ፣ ከለጋሽ ሀገራት የሚገኝ የገንዘብ ድጋፍ በመቀነሱ ስደተኞች ቤተሰቦቻቸውን ለማስተዳደር መቸገራቸውና ለጉልበት ብዝበዛ እና ለጥቃት መጋለጣቸው፣ ለሕክምና አገልግሎት የሚያስፈልጉ ቁሳቁሶችና መድኃኒቶች እጥረት፤ የስደተኞች እና ጥገኝነት ጠያቂዎችን የኑሮ ደረጃ ለማሻሻል የተጀመሩ ፕሮጀክቶች መቋረጥ፣ የመጠለያ ጣቢያዎች እድሳት አለመኖር እና ከትምህርት አገልግሎት ጋር የተገናኙ ችግሮች አሳሳቢ መሆናቸው ተመላክቷል። በተጨማሪም ስደተኞች በሚገኙባቸው መጠለያ ጣቢያዎች ከዚህ በፊት የነበረው ተዘዋዋሪ ችሎት እና ነጻ የሕግ ድጋፍ አገልግሎት መቋረጥ ስደተኞች እና ጥገኝነት ጠያቂዎች ፍትሕ የማግኘት መብታቸው ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ እንደፈጠረባቸው ተገልጿል።
የውይይቱ ተሳታፊዎች በኢሰመኮ የቀረቡ የክትትል ሥራ ግኝቶች ወቅታዊና ሁኔታውን የሚያሳዩ መሆናቸውን በመግለጽ፤ በክልሉ የሚገኙ ስደተኞች እና ጥገኝነት ጠያቂዎች መብቶች ጥበቃ ላይ ያላቸውን ልምድ፣ ያጋጠሟቸውን ተግዳሮቶች እና መልካም ተሞክሮዎችን አካፍለዋል። ለስደተኞች ጥበቃ እና ድጋፍ የሚደረገው የገንዘብ መጠን መቀነስ ስጋት እንደፈጠረባቸውና ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ የተጠናከረ ውትወታ ማድረግ እንደሚያስፈልግ እንዲሁም በሰብአዊ እርዳታ ላይ ጥገኝነትን ለመቀነስ ዘላቂ መፍትሔዎችን ማፈላለግ እንደሚገባ አመላክተዋል።