የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል አሶሳ ዞን ሥር በሚገኙ 12 የወረዳ እና የከተማ አስተዳደር ፖሊስ ጣቢያዎች ላይ የተጠርጣሪዎችን አያያዝ እና ሰብአዊ መብቶች አጠባበቅ በተመለከተ ባደረገው ክትትል የተለዩ ግኝቶች እንዲሁም በተሰጡ ምክረ ሐሳቦች አፈጻጸም ዙሪያ በአሶሳ ከተማ ታኅሣሥ 11 ቀን 2016 ዓ.ም. ከሚመለከታቸው የፍትሕ አካላት ጋር ውይይት አካሂዷል፡፡

በውይይት መድረኩ የክልሉ ሰላም ግንባታና ጸጥታ ቢሮ ምክትል ኃላፊ፣ የክልሉ ፍትሕ ቢሮ፣ ፖሊስ ኮሚሽን እና ጠቅላይ ፍርድ ቤት ተወካዮች፣ የአሶሳ ዞን ፖሊስ መምሪያ ኃላፊ፣ ከወረዳ ፖሊስ ጽሕፈት ቤት የአቤቱታ መቀበልና መመርመር የሥራ ሂደት አስተባባሪዎችን ጨምሮ ዐቃቢያነ ሕግ ተሳታፊ ሆነዋል፡፡

በውይይት መድረኩ በፖሊስ ጣቢያዎቹ ያለውን የተጠርጣሪዎች አያያዝ እና የሰብአዊ መብቶች አጠባበቅ ሁኔታን አስመልክቶ የተስተዋሉ መሻሻሎች እና አሳሳቢ ጉዳዮች ላይ ያተኮረ የክትትል ሪፖርት በኮሚሽኑ በኩል ቀርቦ ውይይት ተደርጎበታል። በክትትል ከተለዩ መልካም ጎኖች መካከል በአንዳንድ ፖሊስ ጣቢያዎች የተጠርጣሪዎች ማቆያ ክፍሎች ግንባታ መደረጉ፣ ለተጠርጣሪዎች መኝታ ክፍል ፍራሽ ለማስገባት የተከናወኑ ጅምር ሥራዎች መኖራቸው፣ በተወሰኑ ጣቢያዎች የመጠጥና የንጽሕና መጠበቂያ ውሃ እንዲገባ መደረጉ፣ ተጠርጣሪዎች በቤተሰቦቻቸውም ሆነ በማንኛውም አካል ያለ ገደብ እንዲጎበኙ መደረጉ እና በጣቢያ ውስጥ ለረጅም ጊዜ ታስረው የሚቆዩ ተጠርጣሪዎች ቁጥር እየቀነሰ መምጣቱ ተጠቅሷል፡፡

የውይይቱ ተሳታፊዎች በስብሰባ አዳራሽ ውስጥ

በሌላ በኩል ምግብና ውሃን ጨምሮ መሠረታዊ አገልግሎቶች አለመሟላት፣ በቂና ምቹ የሆነ የማቆያ ክፍሎች አለመኖር፣ በማቆያ ክፍሎችና መጸዳጃ ቤቶች የንጽሕና ጉድለት መኖር፣ የተጠርጣሪዎች መረጃ በተደራጀና ወጥ በሆነ አግባብ ያለመያዝ እና ለመብቶች ጥሰት ተጋላጭ የሆኑ የማኅበረስብ ክፍሎችን ታሳቢ ያደረጉ ድጋፍና እንክብካቤዎች አለመኖራቸው በትኩረት ሊሠራባቸው ከሚገቡ ጉዳዩች መካካል ተዘርዝረዋል።

የውይይቱ ተሳታፊዎች በበኩላቸው በኮሚሽኑ የቀረበውን የክትትል ግኝት እና የተሰጡ ምክረ ሐሳቦች በተመለከተ ሙሉ በሙሉ የሚቀበሉት መሆኑን ጠቅሰው በቀጣይ በተለዩት ክፍተቶች ላይ በትኩረት እንደሚሠሩ ተናግረዋል። አያይዘውም ከመሠረተ ልማት ጋር የተያያዙ የተጠርጣሪዎች መብቶችን ለማክበርና ለማሟላት በመንግሥት በኩል ለፖሊስ የሚመደበው በጀት አነስተኛ መሆኑ ተግዳሮት እንደሆነባቸው ገልጸዋል፡፡

በውይይት መድረኩ ተገኝተው ከተሳታፊዎች ለተነሱት ጥያቄዎችና አስተያየቶች ምላሽና የማጠቃለያ ሐሳብ ያቀረቡት የኢሰመኮ አሶሳ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ጉርሜሳ በፉጣ፤ በፖሊስ ጣቢያዎች ያለው የተጠርጣሪዎች አያያዝ ሁኔታ መሻሻሎች እያሳየ መምጣቱ ተስፋ ሰጪ ቢሆንም የፖሊስ አባላት መደበኛ ሥራቸውን በሚያከናውኑበት ጊዜ ሰብአዊ መብቶችን ማክበር ለአፍታም ቢሆን መዘንጋት እንደሌለባቸው አስረድተዋል፡፡ አክለውም የፍትሕ አካላት ሰብአዊ መብቶችን ለማክበር እና ለማስከበር ቁርጠኛ መሆን እንዳለባቸው እንዲሁም በኮሚሽኑ ክትትል የተለዩ ግኝቶችንና የተሰጡ ምክረ ሐሳቦችን በቅንነት ተቀብሎ መፈጸም እንደሚጠበቅባቸው ገልጸዋል፡፡