የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል፣ መተከል ዞን፣ ግልገል በለስ ከተማ ሰኔ 30 ቀን 2015 ዓ.ም. የተፈጸመውን ጥቃት እና ከክስተቱ ጋር የተያያዙ ጉዳዮችን በተመለከተ የአካባቢውን ነዋሪዎች፣ የክልሉን የጸጥታ እና የአስተዳደር ኃላፊዎች በማነጋገር ክትትል አድርጓል። 

ጥቃቱ የተፈጸመው በግልገል በለስ ከተማ፣ በተለምዶ “ቻይና ካምፕ” ተብሎ በሚጠራ ሰፈር ከቀኑ 11፡30 ሰዓት ጀምሮ ሲሆን፣ 3 የአካባቢውን ሚሊሻ አባላት ጨምሮ 8 ነዋሪዎች መገደላቸውን፣ በ16 ሲቪል ሰዎች ላይ ደግሞ  ከባድ የአካል ጉዳት ደርሶ የሕክምና እርዳታ እያገኙ መሆኑን፣ በርካታ ሌሎች ነዋሪዎች ቻይና ካምፕን ለቀው ወደ ሌላ ሰፈር መሸሻቸው ታውቋል። የአካባቢው ነዋሪዎችና የአካባቢው አስተዳደር ኃላፊዎች የጥቃቱ ፈጻሚዎች በግልገል በለስ ከተማ አቅራቢያ ከመንግሥት ጋር በተደረገው ስምምነት መሠረት ትጥቅ ለማስፈታት በሚል አንድ ካምፕ ውስጥ እንዲሰፍሩ የተደረጉ የጉሙዝ ሕዝቦች ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ጉሕዴን) ተብሎ የሚጠራው ታጣቂ ቡድን አባላት መሆናቸውን  እና በጥቃቱም ጉዳት የደረሰባቸው ሰዎች በአካባቢው የሚኖሩ በተለምዶ “ቀዮች” ተብለው የሚታወቁ ነዋሪዎች/ከጉሙዝ ብሔር ውጪ ያሉ ሌሎች ብሔሮች መሆናቸውን ያስረዳሉ። ታጣቂዎቹም ለጥቃቱ ምክንያት ያሉት “ከመንግሥት ጋር የተደረሰው የሰላም ስምምነት አልተተገበረም” የሚል መሆኑን ኮሚሽኑ ካነጋገራቸው የአካባቢው ነዋሪዎች ማወቅ ተችሏል።

በየካቲት ወር 2015 ዓ.ም. በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሰባት አባላት ያሉትና በመተከልና ሌሎች አካባቢዎች የተፈጠሩ የጸጥታ ችግሮችን በመገምገም የመፍትሔ አቅጣጫ እንዲያቀርብ የተቋቋመ ኮሚቴ፣ በመተከል ዞን ያለውን ሁኔታ ጎብኝቶ፣ ከሦስት ሺህ በላይ ታጣቂዎች እና በእነርሱ አማካኝነት “ጫካ ገብተው” የነበሩ ከ68 ሺህ በላይ የጉሙዝ ብሔረሰብ አባላት ወደ ሰላማዊ ሕይወት መመለሳቸውን መግለጹ የሚታወስ ነው። ይህንንም ተከትሎ ታጣቂዎቹ ትጥቃቸውን ለመፍታት ከመንግሥት ጋር በተስማሙት መሠረት፣ በከተማዋ ምሥራቅ በኩል  በሚገኝ ካምፕ እንዲሰፍሩ የተደረገ መሆኑን እና በተለምዶ “የሰላም ተመላሾች” በመባል እንደሚጠሩ ለማወቅ ተችሏል። ሆኖም የአካባቢው ነዋሪዎች እንደሚያስረዱት፣ የታጣቂ ቡድኑ አባላት በከተማዋ ከነመሣሪያቸው ሲንቀሳቀሱ የሚታዩ፣ በከተማዋ የሚገኙ የምግብ ቤት እና ሌሎች አገልግሎቶችን ሳይከፍሉ ወይም አገልግሎት ሰጪዎችን በማስገደድ በነጻ የሚጠቀሙ እና ከነዋሪዎች በግዳጅ ገንዘብ የሚሰበስቡ የቡድኑ አባላት አሉ። የቡድኑ አባላት በነዋሪዎች ላይ ወከባ፣ ማስፈራራት፣ ብሎም ድብደባ እና ሰዎችን በካምፕ አስሮ የማቆየት ተግባራትን የፈጸሙበት ጊዜ እንዳለም ለማወቅ ተችሏል።

ከሰኔ 30 ቀን 2015 ዓ.ም. ቀደም ብሎ የተፈጠሩ ክስተቶችን በተመለከተም፣ አንድ የጉሙዝ ብሔረሰብ ተወላጅ መሆኗ የተገለጸ ታዳጊ በከተማው በተከሰተ የመኪና አደጋ መሞቷን እና በአደጋ አድራሹ እና በሟች ቤተሰብ መካከል በተደረሰ የእርቅ ስምምነት መሠረት ካሳ የተከፈለ መሆኑ ተገልጿል። ሆኖም የጉሕዴን ታጣቂዎች ሰኔ 29 ቀን 2015 ዓ.ም. ከግልገል በለስ ከተማ ወጣ ብሎ በሚገኝ አካባቢ በመሄድ አንድ እረኛ የገደሉ መሆኑን ነዋሪዎች ያስረዳሉ። በከተማዋ ሰኔ 30 ቀን 2015 ዓ.ም. ከተፈጸመው ጥቃት በኋላ የሀገር መከላከያ ሠራዊት ወደ ከተማዋ በመሠማራቱ ለጊዜው አንጻራዊ ሰላም መኖሩን ማወቅ ተችሏል።

በደረሰው ጥቃት ሳቢያ አካባቢውን ለቀው ወደ ሌላ ሰፈር ለሸሹ  ነዋሪዎች አስፈላጊው ሰብአዊ ድጋፍ  ማድረስ፣ ለነዋሪዎች አስተማማኝ ሰላም በማስፈን ወደ አካባቢያቸው ለመመለስ እንዲችሉ ማድረግ፣ እንዲሁም አጥፊዎችን በሕግ ተጠያቂ በማድረግ ፍትሕን ማረጋገጥ ይገባል፡፡ ይህንን መሰል ጥቃቶችን እና ግጭቶችን በተመለከተ ኢሰመኮ ሐምሌ 5 ቀን 2015 ዓ.ም. ይፋ ባደረገው ዓመታዊ የሰብአዊ መብቶች ሁኔታ ሪፖርት፣ በሀገር አቀፍ ደረጃ ለሰብአዊ መብቶች ጥሰት ዋነኛ ምክንያት የሆኑ ግጭቶችን የማስቆም ጥረቶች ሊጠናከሩ እንደሚገባ፤ ዘላቂ እንዲሆኑ ሂደታቸው ተጎጂዎችን ጨምሮ ሁሉንም ባለድርሻ አካላትን ያካተቱ እና ግልጽ ሊሆኑ እንደሚገባ  ማሳሰቡ የሚታወስ ነው።  

ታጣቂ ኃይሎችን ትጥቅ የማስፈታት እና መልሶ የማቋቋም ሥራ ሰላም እና ደኅንነት የማረጋገጡ ዋነኛ አካል እንደሆነና ሂደቱም ሊከተላቸው የሚገቡ መስፈርቶች እና መርሖች እንዳሉት ያስታወሱት የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር ዶ/ር ዳንኤል በቀለ፣ “ይህንን የማድረጉን ሂደት የሚያስፈጽሙ የመንግሥት አካላት በተለይም የተጎዱ አካባቢ ነዋሪዎች እና ባለድርሻ አካላትን ማሳተፍ፣ እንዲሁም የዚህን መሰል ሂደቶች አፈጻጸም እና በተጎጂ አካባቢዎች ላይ ያለውን ተጽዕኖ በቅርበት መከታተልን እኩል ትኩረት መስጠት ውጤታማ በሆነ መንገድ የሰብአዊ መብቶች ጥሰትን ለመከላከል ያስችላል” ብለዋል።