የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ከሚገኙ ማረሚያ ቤቶች መካከል በአሶሳ ዞን እና በመተከል ዞን ማረሚያ ቤቶች የ2015 ዓ.ም. የሰብአዊ መብቶች አጠባበቅ ሁኔታን በተመለከተ ባደረገው ክትትል በተለዩ ግኝቶች እና በተሰጡ ምክረ ሐሳቦች ዙሪያ በባምባሲ ከተማ ሰኔ 5 ቀን 2015 ዓ.ም. ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ተወያየ፡፡
በውይይቱ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ማረሚያ ቤቶች አስተዳደር ኮሚሽነር እና የፍትሕ ቢሮ ኀላፊን ጨምሮ ከምክር ቤት፣ ከሕዝብ ዕንባ ጠባቂ አሶሳ ጽ/ቤት፣ ከአሶሳ ዞን ማረሚያ ቤቶች አስተዳደር፣ ከመተከል ዞን ማረሚያ ቤቶች አስተዳደር መምሪያ የተውጣጡ ተወካዮች እና ከኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን የክትትልና ምርመራ ሥራ ክፍል ኀላፊዎች ተሳትፈዋል፡፡
በክትትል ሪፖርቱ በአሶሳ ዞን ማረሚያ ቤቶች አስተዳደር መምሪያ የታራሚዎች ማረፊያ ክፍል ጥበትን ለመቀነስ የሚያስችል የማስፋፊያ ግንባታ መጀመሩ፣ ታራሚዎች የተለያዩ የእጅ ሙያዎችን እንዲለምዱ እና ከማኀበረሰቡ ጋር ሲቀላቀሉ እራሳቸውን እንዲችሉ የሚያግዛቸው የብረትና የእንጨት ሥራ እንዲሠሩ መደረጉ፣ በማረፊያ ክፍሎች ተጨማሪ አልጋና ፍራሽ መግባቱ፣ አዲስ የዳቦ መጋገሪያ ማሽን መተከሉ እና የታራሚዎች ምግብ ዝግጅት ላይ ለሚቀርብ ቅሬታ ባለሙያዎች እንዲመደቡ መደረጉ በማረሚያ ቤቱ የተስተዋሉ አዎንታዊ መሻሻሎች መሆናቸው ተገልጿል፡፡
በሌላ በኩል በአሶሳ ዞን ማረሚያ ቤት ጭካኔ ከተሞላበት፣ ኢሰብአዊና አዋራጅ ከሆነ አያያዝና ቅጣት የመጠበቅ መብትን በተጻረረ መልኩ አንድን ታራሚ በካቴና አስሮ የማቆየት ቅጣት መወሰዱ እንዲሁም አልፎ አልፎ በታራሚዎች ላይ በማረሚያ ፖሊስ አባላት የሚፈጸም ድብደባ እና ማሸማቀቅ መኖሩ አሳሳቢ ተብለው ከተዘረዘሩት ግኝቶች መካከል ተጠቅሰዋል፡፡
ከመሠረታዊ ፍላጎቶች አገልግሎቶች ጋር በተያያዘ በመተከል እና አሶሳ ዞን ማረሚያ ቤት የታራሚ ክፍሎች ጥበትና ከፍተኛ የሆነ የንጽሕና ጉድለት መስተዋሉ፣ የመኝታ አልጋ እና ፍራሽ አቅርቦት እጥረት መኖሩ እንዲሁም ከሕክምና አገልግሎት፣ የመድኃኒት እና ላቦራቶሪ እጥረቶች መኖራቸው የማስተካከያ እርምጃ እንደሚያስፈልጋቸው በክትትሉ ተለይተው ለውይይት ቀርበዋል። በተጨማሪም በጊዜ ቀጠሮ ላይ በማረሚያ ቤት የሚገኙ ዜጎችን የተፋጠነ ፍትሕ እያገኙ አለመሆናቸው የተገለጸ ሲሆን የእምነት ነጻነት፣ የጾታ እኩልነት፣ በማረሚያ ቤቶቹ የተደራጀ እና ወጥ የሆነ የቅሬታ ማቅረቢያ ሥርዓት አለመዘርጋት ጋር የተያያዙ ችግሮች ቀርበው ውይይት ተደርጎባቸዋል፡፡
የውይይት መድረኩ ተሳታፊዎች በማረሚያ ቤቶቹ የሚስተዋሉት ችግሮች በመሠረታዊነት ከበጀት እጥረት ጋር የተያያዙ መሆናቸውን አስረድተዋል፡፡ የክልሉ ፍትሕ ቢሮ ኅላፊ በበኩላቸው ኮሚሽኑ ባካሄደው ክትትል ተለይተው የቀረቡት ግኝቶች የክልሉን ማረሚያ ቤቶች ነባራዊ ሁኔታ የሚያመላክቱ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡ አክለውም በጊዜ ቀጠሮ ማረሚያ ቤት ያለፍርድ ታስረው የሚገኙ እስረኞች ጉዳያቸው ከፌዴራል ፍትሕ አካላት ጋር የሚያያዝ መሆኑን ጠቁመው በቀጣይ መፍትሔ ለመስጠት እንሠራለን ብለዋል፡፡ ከመሠረታዊ ፍላጎቶች አቅርቦትና የማስፋፊያ ግንባታ ጋር በተያያዘ የክልሉ መንግሥት አስፈላጊውን በጀት በመመደብ ወደፊት የሚሠራ መሆኑንም ጨምረው ተናግረዋል፡፡
የኢሰመኮ የሰብአዊ መብቶች ክትትልና ምርመራ ሥራ ክፍል የሪጅን ዳይሬክተር ዶ/ር አለሙ ምህረቱ በውይይቱ ማጠቃለያ ላይ “ፖሊሲ አውጪዎችና የፍትሕ አካላት በፍርድ ቤት ጥፋተኛ የተባሉ ታራሚዎች ከእስር ይልቅ የማኅበረሰብ አገልግሎቶችን ጨምሮ አማራጭ የቅጣት ፖሊሲ በመተግበር እና አማራጭ የግጭት መፍቻ ዘዴዎችን በመጠቀም በአጠቃላይ በፍትሕ ሥርዓቱ በተለይም በማረሚያ ቤቶች የሚስተዋለውን ጫና መቀነስ ይቻላል” ብለዋል፡፡ አክለውም በክትትሉ የተለዩትን አንድን ታራሚ በካቴና ማሰርና ድብዳባ መፈጸምን በተመለከተ በዓለም አቀፍ ሰብአዊ መብቶች ስምምነቶችም ሆነ በኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት መሠረት ኢሰብአዊ አያያዝና ፈጽሞ የተከለከሉ ድርጊቶች መሆናቸውን አብራርተው ሊታረሙ እንደሚገባ ገልጸዋል፡፡