የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ለመንግሥት እና ለግል አካቶ እና ልዩ ትምህርት ቤቶች መምህራንና ርዕሰ መምህራን በአካል ጉዳተኛ ተማሪዎች መብቶች ላይ ያተኮረ የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረክ ነሐሴ 23 እና 24 ቀን 2016 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ከተማ አዘጋጅቷል። መድረኩ አካል ጉዳተኛ ተማሪዎች ከጉዳት አልባ አቻዎቻቸው እኩል የትምህርት መብት ተጠቃሚ እንዲሆኑ በትምህርት ቤት ማኅበረሰብ ዘንድ የሚስተዋል የግንዛቤ እና የአመለካከት ክፍተትን ለማጥበብ ያለመ ነው፡፡
በዝግጅቱ ኢሰመኮ በተለያዩ ጊዜያት ባካሄዳቸው የሰብአዊ መብቶች ክትትልና ምርመራ በተለዩ ግኝቶች መሠረት የአካል ጉዳተኛ ተማሪዎች በትምህርት ወቅት የሚያጋጥሟቸው ተገዳሮቶች በዝርዝር ቀርበው ውይይት ተደርጎባቸዋል፡፡ ተሳታፊዎች በሰብአዊ መብቶች ፅንሰ ሐሳብ፣ በሕፃናት መብቶች እና በተለይም በአካል ጉዳተኛ ተማሪዎች የመማር መብት ላይ ያላቸውን ግንዛቤ ለማዳበር የሚያስችል ገለጻም ቀርባል። በተጨማሪም ተሳታፊ መምህራን የትምህርት ቤቶቻቸውን ተደራሽነት ሁኔታ ከቀረበው ገለጻ እና ከውይይቱ ባገኙት ዕውቀት እና የመመዘኛ መስፈርት ዝርዝር መሠረት እንዲመዝኑ የተደረገ ሲሆን፤ የተደራሽነት ክፍተቱ እና የተመጣጣኝ ማመቻቸት በአግባቡ አለመሟላት በአካል ጉዳተኛ ተማሪዎቻቸው ላይ የሚያሳድረውን ተጽዕኖ በተግባር በተደገፈ ክንውን እንዲረዱ ማድረግ ተችሏል።
በመጨረሻም መምህራን የተለያየ የአካል ጉዳት ካላቸው ሰዎች ጋር በሚያደርጉት ግንኙነት በጥቅም ላይ ሊያውሉ የሚችሏቸውን ክህሎቶች እንዲያዳብሩ በተንቀሳቃሽ ምስል (ቪዲዮ) የተደገፈ ገለጻ ተሰጥቷቸዋል። ሳምንታዊ የትምህርት ዕቅዳቸው አካታች እንዲሆን ለማድረግ አካታች የሆነ ዕቅድ አዘገጃጀትን በግል እንዲለማመዱ እንዲሁም ለየትምህርት ቤቶቻቸው የድርጊት መርኃ ግብር በቡድን እንዲያዘጋጁ ተደርጓል።
የኢሰመኮ የአካል ጉዳተኞች እና የአረጋውያን መብቶች ሥራ ክፍል ዳይሬክተር ሜቲ አቶምሳ፣ ኢሰመኮ ለተመረጡ ትምህርት ቤቶች ርዕሰ መምህራን እና መምህራን ያዘጋጀውን የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረክ ውጤት ለመገምገም ክትትል ማድረጉን እንደሚቀጥል ገልጸው፤ አካል ጉዳተኛ ተማሪዎች እንደ ጉዳት አልባ አቻዎቻቸው የትምህርት መብቶቻቸውን በምልአት መጠቀም ይችሉ ዘንድ ርዕሰ መምህራንን እና መምህራንን ጨምሮ ሌሎች ባልድርሻ አካላት የበኩላቸውን እንዲወጡ ጥሪ አድርገዋል።