የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) በአፋር እና በሶማሊ ክልሎች መካከል በቅርቡ ሚያዝያ 2016 ዓ.ም. የተኩስ ማቆም ስምምነት የተደረገ ቢሆንም፤ ሁለቱን ክልሎች በሚያዋስኑ አካባቢዎች የትጥቅ ግጭቶች፣ የሲቪል ሰዎች ሕይወት መጥፋት እና መፈናቀልን የሚያመላክቱ ዘገባዎችን በአሳሳቢነት እየተከታተለ ይገኛል። በአካባቢዎቹ ያለው ውጥረት ተባብሶ መቀጠሉን ተከትሎ ከግንቦት 29 ቀን 2016 ዓ.ም. ጀምሮ የተኩስ ልውውጦች እና ግጭት በድጋሚ በመከሰታቸው የሲቪል ሰዎች ሞትን፣ በግል እና በሕዝብ ንብረት ላይ ጉዳት መድረሱን እና ሌሎች ጉዳቶችን የሚገልጹ አቤቱታዎችና ሪፖርቶች ለኢሰመኮ ደርሰውታል። ኢሰመኮ ያነጋገራቸው የአፋር እና የሶማሊ ክልሎች የአስተዳደርና የጸጥታ ኃላፊዎች እንዳረጋገጡት፤ በሁለቱ ክልሎች የጸጥታ ኃይሎች መካከል ከግንቦት 29 ቀን 2016 ዓ.ም. ጀምሮ በነበሩ ቀናቶች አልፎ አልፎ የተከሰቱ ግጭቶች በሲቪል ሰዎች ላይ ጉዳትና ሥቃይ እንዲሁም የአከባቢው ነዋሪዎች ከመኖሪያ ቀዬአቸው እንዲፈናቀሉ ምክንያት ሆነዋል።
ኢሰመኮ ሁለቱ ክልሎች በመካከላቸው ያሉትን የቆዩ እና የቀጠሉ አለመግባባቶች በንግግር ለመፍታት የሚያደርጉትን ጥረት እና የዚህም ውጤት የሆነውን በኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት መሪነት ሚያዝያ 2016 ዓ.ም. የተደረገውን የተኩስ አቁም ስምምነት ተገንዝቧል። በተመሳሳይ በፌዴራል እና በክልል ባለሥልጣናት የተወሰዱ እና ግጭቶቹ እንዳይስፋፉ ለመከላከል የተደረጉ ሌሎች ጥረቶችን በበጎ ይመለከተዋል።
የኢሰመኮ ምክትል ዋና ኮሚሽነር ራኬብ መሰለ፣ ለግጭቱ ሰላማዊ እና ዘለቄታዊ መፍትሔ ለማበጀት የሁለቱም ክልሎች ባለሥልጣናት ያሳዩት ፈቃደኝነት አበረታች መሆኑን ገልጸው፤ ግጭቱ በአፋጣኝ የሚቆምበት ሁኔታን ለማረጋገጥ የፌዴራል መንግሥቱ ተጨማሪ ጥረትና ድጋፍ እንዲያደርግ ጥሪ አቅርበዋል። ምክትል ዋና ኮሚሽነሯ አክለውም መጪውን የኢድ አላድሃ በዓል ታሳቢ በማድረግ ባለድርሻ አካላት በአካባቢው ያለው ግጭት ተባብሶ ተጨማሪ ጉዳት በሲቪል ሰዎች ላይ እንዳይደርስ ኢሰመኮ ጥሪውን ያቀርባል” ብለዋል።