የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ/ኮሚሽኑ) በሀገር ውስጥ በሴቶችና በሕፃናት የመነገድ ድርጊት የባለግዴታዎች ምላሽ አሰጣጥ ላይ ያተኮረ ባለ 33 ገጽ የክትትል ሪፖርት ዛሬ ይፋ አድርጓል። ይህ የክትትል ሪፖርት በሀገር ውስጥ በሴቶች እና በሕፃናት መነገድን የመከላከል፣ ለተጎጂዎች የሚደረጉ ጥበቃ እና መልሶ ማቋቋምን፣ የአጥፊዎችን ተጠያቂነት ለማረጋገጥ የተወሰዱ እርምጃዎችን እንዲሁም እነዚህን ተግባራት ለመከወን የተዘረጉ የትብብር ማዕቀፎች ከሰብአዊ መብቶች መርሖች እና መመዘኛዎች ጋር የተጣጣሙ መሆናቸውን በመመዘን አንኳር ግኝቶችን እና ምክረ ሐሳቦችን የያዘ ነው።

በሀገር ውስጥ በሰዎች የመነገድ ድርጊት መነሻ፣ መተላለፊያና መዳረሻ ተብለው የተለዩ ቦታዎችን መሠረት በማድረግ በመጀመሪያ ዙር በአማራ ክልል በባሕር ዳር ከተማ እና በአፋር ክልል በሰመራና ሎጊያ ከተሞች፤ በሁለተኛ ዙር በሲዳማ ክልል ሃዋሳ ከተማ እና በቀድሞ የደቡብ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል በአሁኑ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልላዊ መንግሥት ወላይታ ዞን፣ ከኦሮሚያ ክልል በምሥራቅ ሸዋ ዞን፤ በአዳማ ከተማ እና በአዲስ አበባ ከተማ በሚገኙ የኦሮሚያ ክልል ቢሮዎች እንዲሁም በአዲስ አበባ ከተማ በሚገኙ የፌዴራል ተቋማት ኮሚሽኑ ክትትል አድርጓል። በዚህም 23 የክልል ቢሮዎች፣ 6 የፌዴራል ተቋማት፣ 4 የከተማ አስተዳደር ጽሕፈት ቤቶች፣ 14 የዞን መምሪያዎች እና የፖሊስ ጣቢያዎች፣ 13 መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጀቶች፣ 4 የሥራ እና ሠራተኛ አገናኝ ኤጀንሲዎች እንዲሁም 21 የድርጊቱ ተጎጂዎችን ማነጋገር እና የተጎጂ ታሪኮችን መመልከት ተችሏል።

በክትትሉ ሴቶች እና ሕፃናት በሀገር ውስጥ በሰው መነገድ ድርጊት ሳቢያ ከጾታዊ እና አካላዊ ጥቃት እንዲሁም ከአድልዎና መገለል የመጠበቅ መብቶቻቸው፣ የአካልና የአእምሮ ደኅንነት መብት፣ የነጻነትና ከቦታ ቦታ የመንቀሳቀስ መብት እና ፍትሕ የማግኘት መብቶቻቸው እንደተጣሱ ተመላክቷል። በሰው መነገድን ለመከላከል እና ለመቆጣጠር የወጡ ሕጎች፣ ፖሊሲዎች፣ የድርጊት መርኃ ግብሮች፣ መነሻና ሳቢ ምክንያቶችን ለመቀነስ የሚያስችሉ እርምጃዎች እንዲሁም የግንዛቤ ማስጨበጫና የስልጠና መርኃ ግብሮች ከሁሉን አቀፍ ምላሽ ይልቅ፤ በዋናነት ሰውን በሕገ ወጥ መንገድ ድንበር ማሻገር እና ከሀገር ውጪ በሰው የመነገድ ድርጊት ላይ ብቻ ትኩረት ያደረጉ መሆናቸው በሪፖርቱ ተጠቅሷል።

በተጨማሪም የወንጀል ምርመራዎች በአብዛኛው ሰውን በሕገ ወጥ መንገድ ድንበር ማሻገር ላይ ትኩረት ማድረጋቸው፣ ከዋናው ድርጊት ጀምሮ ያሉትን የመብት ጥሰቶች በተናጠል እየመረመሩ ለእያንዳንዱ ሕገ ወጥ ድርጊት ተጠያቂነትን ከማረጋገጥ ይልቅ በአንዱ የጥቃት ዐይነት ላይ ብቻ ምርመራ በማካሄድ ክስ እንደሚቀርብ እና በዚህም አጠቃላይ የክስ ምጣኔ ዝቅተኛ መሆኑ በሪፖርቱ ተብራርቷል።

መንግሥት በሀገር ውስጥ በሰው መነገድን ለመከላከል እና ለመቆጣጠር እንዲችል፤ ብሔራዊ ትብብር ጥምረቱ የጥናት ውጤትን መሠረት በማድረግ መነሻ እና ሳቢ ምክንያቶችን ለመቀነስ የሚያስችሉ ተገቢ እርምጃዎችን እንዲወስድ እና እንዲያስተባብር፣ ሕፃናት ወደ ከተሞች በመፍለስና በልዩ ልዩ የሥራ ዘርፎች በመሰማራት ለብዝበዛ የሚዳረጉበትን ሁኔታ ለመቀነስ የሚያስችል የማኅበራዊ መከላከያ ፕሮግራሞችን በመንደፍ ተግባራዊ እንዲደረግ፣ እንዲሁም የወንጀል ፍትሕ አስተዳደር መረጃዎች ለትንታኔ፣ ለሕግ እና ለፖሊሲ ማሻሻያዎች ግብአት ሊሰጡ በሚችሉ መልኩ የመረጃ ሥርዓት እንዲዘረጉ ሪፖርቱ ዝርዝር ምክረ ሐሳብ አቅርቧል። የሲቪል ማኅበራትም በሰው የመነገድ ድርጊት ተጎጂ ለሆኑ ሴቶችና ሕፃናት የመጠለያ፣ የማኅበራዊ ሥነ ልቦና ድጋፍና የሕግ ምክር አገልግሎት እና የሥራ ክህሎት ስልጠና የመሳሰሉትን ጠቅላላ ድጋፍና አገልግሎት እንዲሰጡ ምክረ ሐሳብ ቀርቧል።

የኢሰመኮ የሴቶች፣ የሕፃናት፣ የአረጋውያን እና የአካል ጉዳተኞች መብቶች ኮሚሸነር ርግበ ገብረሐዋርያ፣ “በሀገር ውስጥ በሴቶች እና በሕፃናት መነገድ ሰፊና ውስብስብ ችግር በመሆኑ ድርጊቱን ለመከላከል እና ለመቆጣጠር ሁሉን አቀፍ ሕጋዊ፣ ፖለቲካዊ፣ አስተዳደራዊ እና ማኅበራዊ ስልቶች መነደፍ ይኖርባቸዋል’’ ብለዋል። አክለውም በሴቶች እና በሕፃናት የመነገድ ወንጀልን የመከላከል፣ ለተጎጂዎች ድጋፍ እና ጥበቃ የማድረግ እንዲሁም ወንጀሉን የመመርመርና የአጥፊዎችን ተጠያቂነት የማረጋገጥ እርምጃዎች ከሀገር ውጪ ለሆኑ ድርጊቶች ብቻ ሳይሆን፤ በሀገር ውስጥ በሰው መነገድ ድርጊትም ላይ ትኩረት እንዲያደርጉ፤ እነዚህንም ለመተግበር የሚዘረጉ የትብብር ማዕቀፎች በሁሉም ባለድርሻ አካላት ትብብር መሆን እንዳለባቸው ገልጸዋል።