የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) በፖሊስ ማቆያዎች እና በፌዴራል ማረሚያ ቤቶች ውስጥ በጥበቃ ስር ያሉ ተጠርጣሪዎችን የሰብአዊ መብቶች አያያዝ ላይ ከየካቲት 25 እስከ መጋቢት 4 ቀን 2014 ዓ.ም. በፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን የተጠርጣሪዎች ማቆያ፣ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ስር በሚገኙ 26 የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን የተጠርጣሪዎች ማቆያዎች (ጊዜያዊ ማቆያ ሥፍራዎችን ጨምሮ)፤ እንዲሁም መጋቢት 23 ቀን 2014 ዓ.ም. በፌዴራል ማረሚያ ቤት ኮሚሽን ስር በሚገኘው ቃሊቲ ከፍተኛ ጥበቃ ማረሚያ ቤት ውስጥ በተዘጋጀው ጊዜያዊ የተጠርጣሪዎች ማቆያ (በተለምዶ አባ ሳሙኤል ተብሎ የሚጠራው) ውስጥ የተያዙ ሰዎች አያያዝ ላይ የሰብአዊ መብቶች ክትትል አድርጓል። በተጨማሪም በፌዴራል ማረሚያ ቤቶች ኮሚሽን ስር በሚገኙ 5 ማረሚያ እና ማረፊያ ቤቶች፣ የፌዴራል ከፍተኛ ጥበቃ ማረሚያ ቤት (ቃሊቲ)፣ የቃሊቲ ሴቶች ማረሚያ ቤት፣ የዝዋይ ማረሚያ ቤት፣ የድሬዳዋ ማረሚያ ቤት እና የፌዴራል የቀጠሮ ማረፊያ ቤት ላይ የክትትል ሥራዎችን አከናውኗል፡፡

ኢሰመኮ ባደረገው ክትትል የለያቸውን ግኝቶች ለማሳወቅና የመፍትሔ ሃሳቦችን ለማቅረብ ጉዳዩ ከሚመለከታቸው ከፌዴራል እና ከከተማ አስተዳደሩ ከተውጣጡ የፍትሕ ተቋማትና ባለድርሻ  አካላት ጋር ከሰኔ 6 እስከ 7 ቀን 2014 ዓ.ም. እና ከሰኔ 17 እስከ 18 ቀን 2014 ዓ.ም. በቢሾፍቱ ከተማ ሁለት የውይይት መድረኮችን አዘጋጅቷል።

በዝግጅቶቹ ላይ የክትትል ሥራው ወሰን እና ሥራውን ለማከናወን ኢሰመኮ የተጠቀማቸው ዓለም አቀፋዊ፣ አህጉራዊ እና ሀገራዊ የሰብአዊ መብቶች መርሆች በክትትል እና ምርመራ ሥራ ክፍል ባለሙያዎች የቀረቡ ሲሆን፤ በክትትሉ የተለዩ ዋና ዋና አዎንታዊ እና አሉታዊ ግኝቶችም ቀርበዋል። ለምሳሌም ተጠርጣሪዎች በ48 ሰዓታት ውስጥ ፍርድ ቤት መቅረባቸው፣ ከጣቢያ ውጪ በሚንቀሳቀሱበት ጊዜ ካልሆነ በቀር በካቴና የማይታሰሩ መሆኑ፣ ተጠርጣሪዎች ወደ ፖሊስ ጣቢያዎች ሲገቡ ዝርዝር መረጃዎች የሚመዘገቡ መሆኑ፣ አብዛኛዎቹ ጣቢያዎች ለተጠርጣሪዎች የሕክምና አገልግሎት  በመንግሥት ወጪ መቅረቡ እና ተጠርጣሪዎች ሳምንቱን ሙሉ ከጠያቂዎች ጋር መገናኘት የሚችሉ መሆኑ በጠንካራ ጎን የታዩ ጉዳዮች ናቸው።

በአብዛኞቹ ጣቢያዎች የቢሮ ጥበት ያለ መሆኑ፣ ተጠርጣሪዎች እንዲያዙ ትዕዛዝ የተሰጠበትን የፖሊስ መጥሪያ ወይም የፍርድ ቤት መያዣ ትዕዛዝ ለተጠርጣሪዎች የማያሳዩ መሆኑ፣ ያለ ፍርድ ቤት ፈቃድ ብርበራና ፍተሻ የሚፈጸም መሆኑ፣ የተጠርጣሪዎች አያያዝ ከንጽሕና፣ ጤና እና ምግብ አቅርቦት ጋር የተያያዙ ክፍተቶች  በአሉታዊነት በክትትሉ የተለዩ ጉዳዮች ናቸው። 

በዚህ የውይይት መድረክ ላይ የፌዴራል ፍርድ ቤቶች ምክትል ፕሬዝዳንትና የፌዴራል ፍርድ ቤቶች ቃል አቀባይ፣ የፍትሕ ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ፣ የአዲስ አበባ ፍርድ ቤቶች ምክትል ፕሬዝዳንት፣ የአዲስ አበባ ፍትሕ ቢሮ ኃላፊ፣ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ቢሮ የበጀት ዘርፍ ኃላፊ፣ ፌዴራል ዳኞች እና የአዲስ አበባ አስራ አንዱ ክፍለ ከተሞች የወንጀል ምርመራ ምክትል ዳይሬክተሮች እና የኢሰመኮ ዋና እና ምክትል ዋና ኮሚሽነርን ጨምሮ የሲቪል፣ ፖለቲካ እና ማኅበራዊ-ኢኮኖሚያዊ መብቶች ኮሚሽነር በጥቅሉ 29 ሰዎች ተገኝተዋል። 

የፌዴራል ማረሚያ ቤቶችን ክትትል ግኝቶችን አስመልክቶ፤ በማረሚያ ቤቶች የጨለማ ቅጣት ቤቶች አለመኖራቸው፣ ታራሚዎች ወደ ማረሚያ ቤቶች ሲገቡ መብትና ግዴታቸው የሚነገራቸው መሆኑ በአዎንታዊ ጎኑ ቀርቧል። በተቃራኒው ደግሞ በማረሚያ ቤቶች በቂ ግብዓት አለመኖሩ፣ አብዛኛዎቹ ማደሪያ ክፍሎች የተጨናነቁ፣ ያረጁ፣ በቂ አየርና ብርሃን የማያስገቡ መሆናቸው፣ አልጋ የሌላቸውና መሬት ላይ የሚተኙ ታራሚዎች መኖራቸው፣ ለታራሚዎች የሕክምና አገልግሎት በተመለከተ ክፍተት ያለ መሆኑ፣ ከምግብ ጋር በተገናኘ የጥራት ችግር መኖሩን፣ አካላዊ ቅጣቶች መኖራቸው፣ ማግለያ ክፍል ውስጥ ታራሚ እንዲቆይ ሲላክ ከሕግ አግባብ ውጭ ከ15 ቀን  በላይ የሚቆዩ ታራሚዎች መኖር፣ በቂ የመዝናኛ አቅርቦቶች አለመኖራቸው፣ የማረምና ማነፅ ሥራዎች በበቂ ሁኔታ አለመከናወናቸው፣ የቤተሰብ ግንኙነት በሳምንት 2 ቀን ብቻ መሆኑ፣ ልዩ ድጋፍ ለሚያስፈልጋቸው ታራሚዎች በቂ ድጋፍ አለመኖሩ እና የመፀዳጃ እና መታጠቢያ ቤቶች እጥረት በዋናነት ቀርበዋል፡፡ 

በማረሚያ ቤቶች ክትትል ግኝቶች ላይ ለመወያየት በተዘጋጀው መድረክ ላይ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሕግ እና ፍትሕ ቋሚ ኮሚቴ ምክትል ሰብሳቢ እና አባል፣ የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ፕሬዝደንትና መጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ምክትል ፕሬዘዳንትና የፌዴራል ፍርድ ቤቶች ቃል አቀባይ፣ የፌዴራል ማረሚያ ቤቶች ኮሚሽን ኮሚሽነር እና ምክትል ኮሚሽነሮች፣ የፍትሕ ሚኒስቴር ከፍተኛ አመራሮች፣ የኢሰመኮ ዋና እና ምክትል ዋና ኮሚሽነር፣ የ5 የፌዴራል ማረሚያ ቤት ኃላፊዎች፣ የአማኑኤል ሆስፒታልና ከፌዴራል ግዢ አገልግሎት አመራርን ጨምሮ በጥቅሉ 40 ሰዎች ተገኝተዋል።

በክትትሉ የተለዩ ግኝቶችን መነሻ በማድረግ ችግሮቹን ለመቅረፍ በአምስቱም የፍትሕ ተቋማት ማለትም ፍትሕ ሚኒስቴር እና አዲስ አበባ ፍትሕ ቢሮ፣ የፌዴራልና የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን፣ የፌዴራልና የአዲስ አበባ ከተማ ፍርድ ቤቶች አንዲሁም አዲስ አበባ ፋይናስ ቢሮ ከተሰጣቸው ኃላፊነት በመነሳት ሊተገብሩ የሚገባቸውን ምክረ ሃሳቦች በዝግጅቱ ወቅት ቀርበዋል፡፡

ተሳታፊዎቹ በበኩላቸው ለቀረቡት አሉታዊ እና አዎንታዊ ግኝቶች አስተያየቶቻቸውን ያቀረቡ ሲሆን በዋነኝነት ኮሚሽኑ ክትትል ሥራውን ማካሄዱን በበጎ ጎን እንደሚቀበሉት ገልጸው በአብዛኛው የተነሱት ግኝቶችን እንደሚቀበሏቸው፣ የተወሰኑ ግኝቶች ላይ ከክትትሉ በኋላ የተከናወኑ መሻሻሎች መኖራቸውን እንዲሁም ከበጀት ጋር የተያያዙ ችግሮችን ኮሚሽኑም ችግሩን በመፍታት ረገድ ለሚመለከታቸው አካላት የውትወታ ሥራ በመስራት እገዛ እንዲያደርግ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር ዶ/ር ዳንኤል በቀለ

በውይይቱ ላይ ንግግር ያሰሙት የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር ዶ/ር ዳንኤል በቀለ፣ “የአንድ ሀገር እድገት መለኪያ ተደርገው ከሚነሱ ነገሮች መካከል የተጠርጣሪዎችና ታራሚዎች አያያዝ አንዱ ሲሆን፣ ይህ የውይይት መድረክ የተዘጋጀው ኢሰመኮ በክትትል የለያቸውና ከሰብአዊ መብቶች አጠባበቅ አንፃር መሻሻል የሚገባቸውን ነገሮች ተቀራርቦ ለመሥራት እና ለቀጣይ ሥራቸው አጋዥ እንዲሆን እንጂ ለመወቃቀስ አይደለም ” ብለዋል፡፡

የኢሰመኮ ምክትል ዋና ኮሚሽነር ራኬብ መሰለ

በመጨረሻም የኢሰመኮ ምክትል ዋና ኮሚሽነር ራኬብ መሰለ በዝግጅቱ መዝጊያ ላይ ባሰሙት ንግግር፣ ማረሚያ ቤቶች ሰፊ ድጋፍና እገዛ እንደሚያስፈልጋቸውና ኮሚሽኑም በቀጣይ ስልጠናዎችን መስጠትን ጨምሮ ከተለያዩ ተቋማት ጋር በሚያደርጋቸው የውትወታ ሥራ ለማረሚያ ቤቶች ተገቢ ድጋፍ የሚያደርግ መሆኑን ገልጸዋል።