የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) በተለያዩ ጊዜያት በአማራ፣ በጋምቤላ እና በሶማሌ ክልሎች ውስጥ በሚገኙ አስር የስደተኛ መጠለያና መቀበያ ጣብያዎች ውስጥ የሚኖሩ ስደተኞችን በተመለከተ የሰብአዊ መብቶች አያያዝ እና የኢትዮጵያ ስደተኞች አዋጅ አተገባበር ዙሪያ ባከናወነው ክትትል መሰረት ከቁልፍ ባለድርሻ አካላት ጋር የአንድ ቀን አውደ ጥናት አካሄደ፡፡
መጋቢት 5 ቀን 2014 ዓ.ም በኢሰመኮ አዘጋጅነት በተደረገው ስብሰባ የስደተኞች መብቶች ጥበቃንና ሰብአዊ ድጋፍን በተመለከተ ባካሄደው ክትትል በተለዩ አንኳር ግኝቶች፣ ትኩረት በሚሹ የሰብአዊ መብቶች ጉዳዮች እና በመፍትሔ አቅጣጫዎች ዙሪያ ቁልፍ መንግሥታዊና መንግሥታዊ ያልሆኑ ባለድርሻ አካላትን፤ በተለይ የስደተኞችና ተመላሾች አገልግሎት (RRS)፣ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተ.መ.ድ.) የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽንን (UNHCR)፣ የስደተኞች ተወካዮች እና ዓለም አቀፍ ድርጅቶችን ያሳተፈ ውይይት ተደርጓል፡፡
የኢሰመኮ ምክትል ዋና ኮሚሽነር ራኬብ መሰለ ባደረጉት የመክፈቻ ንግግር እንደገለጹት ክትትሉ በሦስት ክልሎች የሚገኙ አስር የስደተኛ መጠለያና መቀበያ ጣቢያዎች የሸፈነ ሲሆን፣ በነዚህ ጣቢያዎች የሚገኙ የስደተኞችና ጥገኝነት ጠያቂዎች ቁጥር በአጠቃላይ በኢትዮጵያ ተመዝግበውና ከለላ ተሰቷቸው ከሚኖሩት 837,533 ስደተኞች ውስጥ 45 ከመቶ በላይ የሚሆነውን የሚወክል ነው፡፡
በመሆኑም ምክትል ዋና ኮሚሽነሯ እንዳብራሩት ይህ ዓይነቱ መድረክ የበርካታ ስደተኞችን መብቶች ለማስጠበቅና መብቶቻቸው መከበራቸውን ለማረጋገጥ ቁልፍ ሚና አለው። በተጨማሪም የሥራ ክፍሉ ዳይሬክተር እስከዳር በቀለ “በመድረኩ የተገኙ ባለድርሻ አካላት፣ ለክትትሉ አንኳር ግኝቶች ግባዓት ከማበርከት ባሻገር ምክረ-ሃሳቦችን ለማስፈጸም የሚኖራቸው ሚና ከፍተኛ እንደሆነ” ጠቁመዋል።