የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ድርጅቶች ህብረት (ኢሰመድህ) ከተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተ.መድ.) የሰብአዊ መብቶች ከፍተኛ ኮሚሽነር የምስራቅ አፍሪካ ጽ/ቤት (UNOHCHR – EARO) ጋር በመተባበር ታኅሣሥ 1 ቀን 2014 ዓ.ም. በሼራተን ሆቴል ባዘጋጀው መርኃ ግብር ለኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ምስጋና አቀረበ። የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ጉባዔ (ኢሰመጉ)፣ የመብቶች እና የዲሞክራሲ እድገት ማዕከል (CARD)፣ የኢትዮጵያ የሰብአዊ መብት ተሟጋቾች ማዕከል፣ ሴንተር ፎር ጀስቲስ እና የሌሎች በርካታ  የሰብአዊ መብቶች ድርጅቶች ጥምረት የሆነው ኢሰመድህ የምስጋና መርኃ ግብሩ ዓላማ ኢሰመኮ ባለፉት ሁለት ዓመታት የማቋቋምያ አዋጁን አሻሽሎ ተዓማኒ እና ውጤታማ ብሔራዊ የሰብአዊ መብቶች ተቋም ለመሆን ላደረገው ከፍተኛ ጥረት እውቅና ለመስጠትና በቀጣይም ለሚሰራቸው ስራዎች እንዲበረታታ ለማድረግ መሆኑን ገልጿል።

በእለቱ የኢሰመድህ ቦርድ አባል እና የሕግ ባለሞያዎች ለሰብአዊ መብቶች (Lawyers for Human Rights) ዳይሬክተር አቶ አምሃ መኮንን ባደረጉት ንግግር በተለይም በወቅታዊው የሀገራችን ሁኔታ ሰብአዊ መብቶች ከመቼውም ግዜ በላይ እንዲታወሱ ማድረግ ተገቢ ነው ብለዋል”። የኢሰመድህ ዳይሬክተር አቶ መሱድ ገበየሁ “ኢሰመኮ በተለይም በዘንድሮ ዓመት ከተ.መድ. የሰብአዊ መብቶች ጽ/ቤት ጋር በጣምራ የሰራውን ሪፖርት ጨምሮ በያዝነው ሳምንት በዓለም አቀፉ የብሔራዊ ሰብአዊ መብቶች ተቋማት ጥምረት (GANHRI)) የተሰጠው የደረጃ “A” (አንደኛ ደረጃ) እውቅና በሀገር ውስጥ ብቻ ሳይሆን በዓለም አቀፍ ደረጃ እያገኘ ላለው ተቀባይነት አንዱ ማስረጃ ነው” በማለት ገልጸዋል።  የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር ዶ/ር ዳንኤል በቀለ በበኩላቸው “ሀገር አቀፍ የሰብአዊ መብቶች ድርጅቶች ሀገራዊውን ሁኔታ እና በሰብአዊ መብቶች ስራ ሊያጋጥሙ የሚችሉ ተግዳሮቶችን ይበልጥ በቅርብ የሚያውቁና የሚረዱ በመሆናቸው፤ ለኮሚሽናችን በሀገር ውስጥ የሰብአዊ መብቶች ድርጅቶች የሚሰጠውን እውቅና ከፍተኛ ቦታ የምንሰጠው ነው” ብለዋል። በኢሰመድህ እና በኢሰመኮ መካከል ያለው አጋርነትም በአዳዲስ የትብብር መስኮች የሚቀጥል መሆኑንም አስረድተዋል።