የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) በኦሮሚያ ክልል በምሥራቅ ወለጋ ዞን ጎቡ ሰዮ ወረዳ አኖ ከተማ በጥር 25 ቀን 2015 ዓ.ም. በዋናነት የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮችን ኢላማ በማድረግ በተፈጸመ ጥቃት በሰው ሕይወት፣ አካል እና ንብረት ላይ ጉዳት መድረሱን በተመለከተ ከጥር 25 – 27 ቀን 2015 ዓ.ም. ምስክሮችን፣ የመንግሥት አካላትን እና የተጎጂ ቤተሰቦችን በማነጋገር ምርመራ አድርጓል፡፡

በዚህም መሠረት ጥር 25 ቀን 2015 ዓ.ም. ከንጋቱ 12:00 ሰዓት ጀምሮ በርካታ ቁጥር ያላቸው የወታደር ልብስ የለበሱ የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት (በተለምዶ ኦነግ ሸኔ) መሆናቸው በነዋሪዎች የተገለጹ ታጣቂዎች በሦስት አቅጣጫ ወደ አኖ ከተማ መግባታቸውን፤ በመቀጠል በከተማዋ የተለያዩ አቅጣጫዎች ተከታታይ የሆነ የተኩስ ድምፅ መሰማት መጀመሩን እና የሲቪል ሰዎች ግድያና የአካል ጉዳት፣ የንብረት ዘረፋ እና ውድመት መድረሱ ታውቋል።

በጥቃቱ ዋና ኢላማ የተደረጉት ከጎቡ ሰዮ ወረዳ የተለያዩ ቀበሌዎች ተፈናቅለው በከተማዋ የተለያዩ ቦታዎች የተጠለሉ የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች መሆናቸውን ኢሰመኮ ያሰባሰባቸው መረጃዎችና ማስረጃዎች ያረጋግጣሉ፡፡ ከ2014 ዓ.ም. ጀምሮ በአካባቢው በተከሰቱ ግጭቶች ምክንያት ከጎቡ ሰዮ ወረዳ 11 ቀበሌዎች እና ከሁለት የአዋሳኝ ወረዳ ቀበሌዎች በድምሩ ከ13 ቀበሌዎች ተፈናቅለው በአኖ ከተማ በመጠለያ ውስጥ እንዲሁም ከመጠለያ ውጭ ከተቀባይ ማኅበረሰብ ጋር ተቀላቅለው የሚኖሩ ቁጥራቸው 10,800 (አስር ሺህ ስምንት መቶ) የሚሆኑ የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች የሚገኙ መሆኑን ኢሰመኮ ቀደም ሲል በአካባቢው ላይ ባደረገው ክትትል ያሰባሰበው መረጃ እና ማስረጃ ያሳያል፡፡

በታጣቂ ቡድኑ በተፈጸመ ጥቃት አንድ የክልል የሥራ ኃላፊ ከነሾፌሩ፣ የከተማ ፖሊስ እና የቀበሌ ሚሊሻ አባላትን ጨምሮ ቢያንስ 50 ሰዎች ተገድለዋል። ከእነዚም መካከል 42 ተጎጂዎች በተፈናቃዮች የመጠለያ ጣቢያ ውስጥ እና ከተቀባይ ማኅበረሰብ ጋር ተቀላቅለው ይኖሩ የነበሩ ተፈናቃዮች እንዲሁም መንግሥትን ይደግፋሉ የተባሉ ነዋሪዎች ነበሩ፡፡ ከሟቾች መካከል አራት ሴቶች እና ሦስት ሕፃናት ናቸው፡፡

ታጣቂዎቹ በከተማው ‘ሰኞ ገበያ’ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ከማኅበረሰቡ ጋር ተቀላቅለው የሚኖሩ ተፈናቃዮችን ቤት ለቤት እየዞሩ በተለይ የአማራ ብሔር ተወላጆችን ለይተው ገድለዋል፡፡ በተጨማሪም በከተማዋ ውስጥ የሚገኝ እና ቀደም ሲል የቀበሌ አስተዳደር ንብረት የነበረና ወደ አረጋውያን፣ ሴቶች እና ሕፃናት ተፈናቃዮች መጠለያነት ተቀይሮ በማገልገል ላይ ይገኝ የነበረ ግቢ ውስጥ በመግባት በፈጸሙት ጥቃት፤ በግቢው ውስጥ የነበሩ ማምለጥ ያልቻሉ ወንድ ተፈናቃዮችን መርጠው የገደሉ ሲሆን ከእነዚህም መካከል ከተገደሉ በኋላ ሬሳቸው በእሳት የተቃጠለ ሰዎች አሉ፡፡ በዚሁ ጥቃት ምክንያት ተፈናቃዮቹ ወደ ተለያዩ አካባቢዎች የተበተኑ ሲሆን መጠለያውም በጊዜያዊነት ተዘግቶ ነበር፡፡

የሟቾችን አስከሬን ጥቃቱ በተፈጸመበት ዕለት እና በማግስቱ የአካባቢው ማኅበረሰብ መቅበሩን የተጎጂዎች ቤተሰቦች ለኮሚሽኑ አስረድተዋል። ከዚህም በተጨማሪ 8 ሰዎች ቀላል እና ከባድ የአካል ጉዳት ደርሶባቸዋል፡፡ በተፈጸመው ጥቃት በከተማዋ የሚገኙ የግለሰቦች የንግድ መደብሮች፣ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች፣ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አኖ ቅርንጫፍ እና ሌሎች ተቋማት መጠነ ሰፊ ዘረፋ እና ውድመት ተፈጽሞባቸዋል፡፡ 

የተፈጸመውን ጥቃት አስመልክቶ የታጣቂ ቡድኑ ቃል አቀባይ በየካቲት 1 ቀን 2015 ዓ.ም. ለአሜሪካ ድምጽ ሬዲዮ የአማርኛ ክፍል በሰጡት ምላሽ ጥቃቱን መፈጸማቸውን አምነው፤ ነገር ግን ማስረጃ ሳያቀርቡ ጥቃቱ የተፈጸመው በካምፕ ውስጥ በስልጠና ላይ በነበሩ የአማራ ኃይሎች ላይ እንጂ ሲቪል ሰዎች ላይ አይደለም በማለት ገልጸው እንደነበር ይታወሳል፡፡

ኢሰመኮ ከጥቃቱ አስቀድሞ ጥር 15 ቀን 2015 ዓ.ም. እንዲሁም ከጥቃቱ በኋላ የካቲት 3 ቀን 2015 ዓ.ም. ተፈናቃዮቹ ይኖሩበት የነበረውን የመጠለያ ጣቢያ በአካል የጎበኘ ሲሆን በዚህም ጥቃቱ በመጠለያ ጣቢያ እና በማኅበረሰቡ ውስጥ ተጠልለው በሚኖሩ የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች ላይ መፈጸሙን አረጋግጧል፡፡

በከተማው የነበረ ውስን የመንግሥት የጸጥታ ኃይል ጥቃቱን ለማስቆም ጥረት ሲያደርግ የነበረ ቢሆንም ታጣቂዎቹ በቦታው ከነበረው የመንግሥት የጸጥታ ኃይል አንፃር በቁጥር እጅግ በርካታ በመሆናቸው እና ጥቃቱ በዕቅድና ዝግጅት የተፈጸመ በመሆኑ ምክንያት ተጨማሪ የመከላከያ ሰራዊት ከነቀምቴ እስከመጣበት እስከ እኩለ ቀን 6፡00 ሰዓት ድረስ ታጣቂዎቹ በከተማዋ እየተዘዋወሩ ግድያ እና ዘረፋ ፈጽመዋል፡፡

በሌላ በኩል የመከላከያ ሰራዊት ከተማዋን መልሶ ከተቆጣጠረ በኋላ “ከሸኔ ጋር ተባብራችኋል” በሚል ጥርጣሬ ስምንት ወጣቶችን በቁጥጥር ስር ካዋሉ በኋላ በጸጥታ ኃይሎች መገደላቸውን ኢሰመኮ አረጋግጧል፡፡

የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር ዶ/ር ዳንኤል በቀለ “በኦሮሚያ ክልል እየተካሄደ ባለው ግጭት ዋነኛ ተጎጂ የሆኑት በተለያዩ መንገዶች ለጥቃት የተጋለጡ ሲቪል ሰዎች መሆናቸውን ኮሚሽኑ ለረጅም ጊዜ በግጭቱ ላይ እያደረገ ያለው የክትትል እና ምርመራ ግኝቶች ያሳያሉ” ብለዋል። አክለውም በተለይም በግጭት ምክንያት የተፈናቀሉ ሰዎች የተጠለሉባቸው ቦታዎችን የጥቃት ኢላማ ማድረግ በማንኛውም ሁኔታ ተቀባይነት የሌለው፣ የዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብቶች ድንጋጌዎችን የሚፃረር ተግባር መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ኮሚሽኑ ሁሉም ወገኖች ሲቪል ሰዎችን እና የሲቪል ሰዎችን ንብረት የጥቃት ኢላማ ከማድረግ እንዲቆጠቡ፣ ለተፈጸሙ ጥቃቶችም መንግሥት የወንጀል ምርመራ በማድረግ ተጠያቂነትን እንዲያረጋግጥ ጥሪ እያቀረበ፤ መንግሥት የሲቪል ሰዎችን ደኅንነት የማስጠበቅ ግዴታውን በአግባቡ ከመወጣት በተጨማሪ በክልሉ የሲቪል ሰዎችን ደኅንነት በዘላቂነት ለማረጋገጥ ለግጭቱ በአስቸኳይ ሰላማዊ መፍትሔ እንዲያፈላልግ በድጋሚ ያሳስባል፡፡