የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ከግንቦት 16 ቀን 2013 ዓ.ም. ጀምሮ በትግራይ ክልል፣ ሽሬ ከተማ ከሚገኙ የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች የሚገኙባቸው የመጠለያ ካምፖች ውስጥ በጸጥታ ኃይሎች የተወሰዱ በርካታ ተፈናቃዮች ስላሉበት ሁኔታ ክትትል በማድረግ ላይ ነው። እነዚህ መጠለያዎች መደበኛ መኖሪያ ቦታቸው ያለውን የደኅንነት ስጋት ሸሽተው የመጡ ሰዎች ብቸኛ የደህንነት ቦታዎች ሲሆኑ፤ የሰብአዊ አቅርቦት ፍላጎቱ አሁንም ከፍተኛ መሆኑ ይታወቃል።

ስለሆነም፣ በእነዚህ መጠለያዎች የሚወሰዱ ማናቸውም የሕግ ማስከበር እርምጃዎችም ሆነ በመጠለያዎቹ ይገኛሉ ተብለው የሚታሰቡ ተጠርጣሪዎችን የመያዝ እርምጃ ተገቢውን የሕግ ሂደት የተከተለና በመጠለያዎቹ ያሉ ተፈናቃዮችን ሁኔታ ታሳቢ ያደረገ መሆን አለበት። ኢሰመኮ የሲቪል ሰዎችን ደኅንነት እና ሰላም አደጋ ላይ የሚጥሉ ማናቸውንም አይነት ተግባራት የሚያወግዝ መሆኑን እየገለጸ፣ አፋጣኝ የእርምት እርምጃ እንዲወሰድ በአጽንኦት ያሳስባል። ኮሚሽኑ የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች እና መጠለያ ቦታዎቻቸው በማንኛውም ጊዜ ቢሆን ጥበቃ ሊደረግላቸው እንደሚገባ በድጋሚ ያስታውሳል።