የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) “የሌሎች ሀገራትን መልካም ተሞክሮ በመቅሰም እና የባለድርሻ አካላት ትብብርን በማጠናከር በኢትዮጵያ የውጭ ሀገር የሥራ ስምሪት እና የሥራ ፍልሰት አስተዳደርን ማጎልበት” በሚል ርዕስ ሰኔ 12 እና 13 ቀን 2017 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ከተማ ዐውደ ጥናት አካሂዷል። በዐውደ ጥናቱ የመንግሥት አካላት፣ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅቶች፣ የሲቪል ማኅበረሰብ ተቋማት፣ በስደት ተመላሾች የተቋቋሙ ማኅበራት፣ የዓለም አቀፍ ድርጅቶች፣ የትምህርት ተቋማት፣ የግሉ ዘርፍ እና የተለያዩ ባለድርሻ አካላት ተወካዮች ተሳትፈዋል።

ዐውደ ጥናቱ የሀገራት መልካም ተመክሮዎችን በመውሰድ በኢትዮጵያ የውጭ ሀገር የሥራ ስምሪት እና የሥራ ፍልሰት አስተዳደርን ለማጠናከር ስትራቴጂያዊ ስልቶችን እና መፍትሔዎችን ለመለየት ያለመ ነው።

በዐውደ ጥናቱ የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር ተወካይ የኢትዮጵያ ሥራ ፍልሰት አስተዳደር ተግዳሮቶች እና ዕድሎች፣ የውጭ ሀገር የሥራ ስምሪት ረቂቅ አዋጅ ክፍተቶችን እና ድክመቶችን ስለመፍታት፣ በሥራ እና ክህሎት ሚኒስቴር ሥር ስላለው የኤሌክትሮኒክስ የሥራ ገበያ መረጃ ሥርዓት (E-LMIS)፣ የሥራ ዕድሎችን ለሥራ ፈላጊዎች በማቅረብ እና በውጭ ሀገር ሥራ ለመሰማራት ለሚፈልጉ ሰዎች መረጃን አደራጅቶ በማቅረብ ረገድ ያለውን ጠቀሜታ አብራርተዋል። በተጨማሪም በናይጄሪያ ለውጭ ሀገር ሥራ ስምሪት የሚሰጡ ስልጠናዎች የወደፊቱን የገበያ ፍላጎት ከግምት ያስገቡ እና የኢንፎርሜሽንና ኮሙኒኬሽን ቴክኖሎጂ ላይ ያተኮሩ ስልጠናዎችን ያካተቱ እንዲሁም የዳበሩ የፍልሰት መረጃ ማእከላት (MRC) ያላቸው መሆኑን አጋርተዋል።

የሲቪል ማኅበራት፣ የተመላሽ ማኅበራት እና የዓለም አቀፍ የሥራ ድርጅት ተወካዮች የተሳተፉበት በሥራ ፍልሰት አስተዳደር፣ በውጭ አገር የሥራ ስምሪት እና የባለድርሻ አካላት ሚና እና ኃላፊነት ላይ ያተኮረ የፓናል ውይይትም ተካሂዷል።

ከዚህ ጎን ለጎን መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማት ድርሻን አስመልክቶ የስደተኞች እና ተመላሾች አገልግሎት የአውሮፓ ተመላሾች ላይ የነበረ ተሞክሮ እና የመልሶ ማቋቋም ልምድ፣ እያደገ የመጣው የዓለም አቀፍ የፍልሰት ምላሽ አሰጣጥ ለውጦች፣ የዓለም አቀፍ የልማት አጋር ድርጅቶች የፍልሰት አስተዳደርን ከማጠናከር አንጻር ያላቸው ሚና፣ ፍልሰት እና ልማት ስላላቸው ትስስር እንዲሁም በኢትዮጵያ ስለሚገኙ የፍልሰት መረጃ ማእከላት እና ስለሚያከናውኗቸው ተግባራት በቀረቡ ገለጻዎች ላይ ውይይት ተደርጓል።

በዐውደ ጥናቱ ማጠቃለያ የግሉ ዘርፍ፣ የተመላሽ ማኅበራት እና የትምህርት ተቋማት ስላላቸው ሚና ገለጻ የተደረገ ሲሆን፣ እናት ባንክ እና መሰል ተቋማት በውጭ ሀገር ሥራ ለተሰማሩ ዜጎች ስለሚሰጡት የቁጠባ እና ከዋስትና ነጻ የብድር አገልግሎት፣ ይህንንም ተደራሽ ለማድረግ ስለሚሰጡት ስልጠና ልምዳቸውን አጋርተዋል። የመዳረሻ ሀገራትን ሕግ በመተርጎም ዜጎች ከመሄዳቸው በፊት ስለ መብቶቻቸው እና ግዴታዎቻቸው የማስገንዘብ እንዲሁም በመዳረሻ ሀገራት ያሉ አገልግሎት ሰጪ ተቋማትን ማስተዋወቅ ስላለው ጠቀሜታ እና በዚህ ረገድ ያከናወኑትን ተግባር ገልጸዋል።

የኢሰመኮ የስደተኞች፣ የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች እና የፍልሰተኞች መብቶች ሥራ ክፍል ዳይሬክተር እንጉዳይ መስቀሌ፣ ዐውደ ጥናቱ የተለያዩ ባለድርሻ አካላትን በማሰባሰብ በኢትዮጵያ የሥራ ፍልሰት አስተዳደር ዙሪያ ወሳኝ በሆኑ የሕግ እና ተቋማዊ አደረጃጀት እንዲሁም በፍልሰት ዑደት (Labour Migration Context) ውስጥ እየገጠሙ ያሉ አዳዲስ ተግዳሮቶች እና መልካም ጅማሮዎች ላይ ለመምከር እና መረጃ ለመለዋወጥ አስቻይ ሁኔታን መፍጠሩን ተናግረዋል። አክለውም በኢትዮጵያ የሥራ ፍልሰት አስተዳደር ላይ የተለያዩ ባለድርሻ አካላት የሚኖራቸውን ሚና፣ ትብብር እና ቅንጅት ማጎልበት ላይ ሊወሰዱ የሚገባቸውን እርምጃዎች በመለየት ረገድ እገዛ ማደረጉን ገልጸዋል።