የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) በተለያዩ አካላት የተዘጋጁ ዓለም አቀፉ የአካል ጉዳተኞች መብቶች ስምምነት የአማርኛ ትርጉም ሥራዎችን በመገምገም እና ማሻሻያ በማድረግ ባዘጋጀው ረቂቅ የአማርኛ ትርጉም ላይ የሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴርን ጨምሮ ከተለያዩ የአካል ጉዳተኞች ማኅበራት ተወካዮች እንዲሁም ከሕግ፣ ከቋንቋ እና ከልዩ ፍላጎት ዘርፍ ባለሙያዎች ጋር ሐምሌ 22 ቀን 2016 ዓ.ም. የግብአት ማሰባሰቢያ ውይይት አካሂዷል።
ኢሰመኮ በተለያዩ አካላት የተዘጋጁ የዓለም አቀፍ የአካል ጉዳተኞች መብቶች ስምምነት የአማርኛ ትርጉም ሥራዎችን ከገመገመ በኋላ ማሻሻያ ማድረግ አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ በድጋሚ የአማርኛ ትርጉሙን ሰርቷል። በውይይቱ ኢሰመኮ ያዘጋጀውን የስምምነቱ ረቂቅ የአማርኛ ትርጉም ለዘርፉ ባለሙያዎች በማሰራጨት ለትርጉም በተጋለጡ ቃላት/ሐረጎች ላይ ግብአት ያሰባሰበበት ሰነድ ቀርቧል፡፡ በዚህም ላይ ሰፊ ውይይት የተካሄደ ሲሆን የአካል ጉዳተኝነት ትርጉምን ጨምሮ ሌሎች መሰል ፅንሰ ሐሳቦችን በተመለከተ የረዥም ጊዜ ልምድ እና ዕውቀት ባላቸው ባለሙያዎች ለተሳታፊዎች ገለጻ በመስጠት ግንዛቤ ለማስጨበጥ ምቹ ሁኔታ መፍጠር ተችሏል፡፡
ኢሰመኮ በተሻሻለው ማቋቋሚያ አዋጁ ቁጥር 1224/2012 ከተሰጡት ሥልጣንና ኃላፊነቶች መካከል ኢትዮጵያ የተቀበለቻቸውን ዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብቶች ሰነዶችን በሀገር ውስጥ ቋንቋዎች መተርጎምና ማሰራጨት አንዱ ነው። የእነዚህ ስምምነቶች መተርጎም የስምምነቶቹን ተደራሽነት የሚጨምር ሲሆን በባለግዴታዎችም ሆነ በባለመብቶች ዘንድ ወጥነት ያለው አረዳድ እንዲኖር ያስችላል።
የኢሰመኮ የሴቶች፣ የሕፃናት፣ የአረጋውያን እና የአካል ጉዳተኞች መብቶች ኮሚሽነር ርግበ ገብረሐዋሪያ የስምምነቱ ረቂቅ የአማርኛ ትርጉም በኢሰመኮ፣ በሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር እንዲሁም በኢትዮጵያ አካል ጉዳተኞች ማኅበራት ፌዴሬሽን የተዘጋጀ ቢሆንም በአንዳንድ ቃላት ትርጉም ዙሪያ ስምምነት ላይ ባለመደረሱ ወጥነት የሌለው እና ለትርጉም የተጋለጠ እንዲሆን አድርጎታል ብለዋል፡፡ አክለውም የአካል ጉዳተኞች መብቶችን ለማስከበር በጋራ የሚደረገውን ውትወታ እንዲያግዝ የተተረጎመው ሰነድ የሚፈለገውን ሐሳብ በትክክል ለሁሉም አካላት እንዲያደርስ እንዲሁም ለተዛባ ትርጉም እንዳይጋለጥ ኢሰመኮን ጨምሮ ሁሉም ባለድርሻ አካላት በጋራ ሊሠሩ ይገባል ሲሉ ተናግረዋል፡፡