የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ከአረጋውያንና ጡረተኞች ብሔራዊ ማኅበር እና ከሄልፕኤጅ ኢንተርናሽናል (HelpAge International) ጋር በመተባበር በየዓመቱ የሚከበረውን በአረጋውያን ላይ የሚደርስ ጥቃት ግንዛቤ የማስጨበጫ ቀንን በማስመልከት የተለያዩ መንግሥታዊ እና መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማት እና የአረጋውያን ማኅበራት ተወካዮች የተሳተፉበት የውይይት መድረክ ሰኔ 13 ቀን 2016 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ከተማ አካሂዷል።  

ውይይቱ የዚህ ዓመት መሪ ቃል በሆነው “ትኩረት በአደጋና አስቸኳይ ሁኔታዎች ውስጥ ለሚገኙ አረጋውያን” ፅንሰ ሐሳብ ላይ ያተኮረ ሲሆን በግጭት እና አሳሳቢ በሆኑ የሰብአዊ መብቶች ሁኔታ ውስጥ ያሉ አረጋውያን ላይ በሚደርሱ የጥቃት ዓይነቶች ዙሪያ የውይይት መነሻ ጽሑፎች ቀርበዋል። በተጨማሪም አረጋውያን ላይ በተጨባጭ እየደረሱ የሚገኙ የጥቃት ታሪኮች በዘርፉ ባለሙያዎች ለተሳታፊዎች ቀርበው ውይይት ተደርጎባቸዋል።

በውይይቱ የአረጋውያን ማኅበራት ተወካዮች ድምፃቸው ሊሰማ እንደሚገባ በመግለጽ “በዚህ ረገድ በሀገራዊ ምክክርና የሽግግር ፍትሕ ሂደቶች ላይ ትርጉም ያለው ተሳትፎ እንዲኖራቸው ሊደረግ ይገባል” ብለዋል። በአረጋውያን ላይ የሚደርሱ ጥቃቶች እና ምልክቶቻቸው ላይ የሚስተዋለውን የግንዛቤ ክፍተት ለመቀነስ ሁሉም ባለድርሻ አካላት የድርሻቸውን ሊወጡ ይገባል በማለት ሐሳባቸውን አጋርተዋል፡፡

የኢትዮጵያ አረጋውያንና ጡረተኞች ብሔራዊ ማኅበር ቦርድ ምክትል ፕሬዚደንት አቶ ጌታቸው ክፍሉ በበኩላቸው አረጋውያን መብታቸውን ለማስከበር ንቁ ተሳትፎ ማድረግ እንደሚጠበቅባቸው እና የሚያጋጥሙ የመብት ጥሰቶችን መንግሥታዊ እና መንግሥታዊ ካልሆኑ ባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን መከላከል እንደሚገባ ገልጸዋል፡፡ እንዲሁም “አረጋውያንን ለጥቃት ከሚያጋልጡ ሁኔታዎች ለመጠበቅ ሊወሰዱ ከሚገባቸው እርምጃዎች መካከል አንዱ እና ዋነኛው ከተረጂነት ማላቀቅ መሆኑ ታውቆ አረጋውያኑ ገቢ በሚያስገኙ ሥራዎች ላይ እንዲሳተፉ በመንግሥት በኩል ምቹ ሁኔታ ሊፈጠርላቸው ይገባል” ብለዋል።  

የኢሰመኮ የሴቶች፣ የሕፃናት፣ የአካል ጉዳተኞች እና የአረጋውያን መብቶች ኮሚሽነር ርግበ ገብረሐዋሪያ ኢትዮጵያ አረጋውያንን በተመለከተ ጠንካራ የሕግ ማዕቀፍ የሌላት መሆኑን ጠቁመው፤ በዚህም ምክንያት በሚፈጸሙ ጥቃቶች ላይ የተቀናጀ ምላሽ ለመስጠት አዳጋች መሆኑን ገልጸዋል። አክለውም በግጭት እና በተፈጥሯዊ አደጋዎች ምክንያት ለሚደርሱ አሳሳቢ የሰብአዊ መብቶች ሁኔታዎች አረጋውያን በተለየ መልኩ ለጉዳት ተጋላጭ በመሆናቸው አካታች የቅድመ ማስጠንቀቂያ ሥርዓቶችን የመዘርጋት እና ጥቃት የሚያደርሱ አካላትን ተጠያቂ በማድረግ ፍትሕ የማስፈን ተግባራት ትኩረት ሊሰጣቸው እንደሚገባ ተናገረዋል።