የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን ከግንቦት ወር 2014 ዓ.ም. ጀምሮ በተለይም በአዲስ አበባ ከተማ እና በአማራ ክልል፣ እንዲሁም ለበርካታ ወራት በኦሮሚያ ክልል የታሰሩ ጋዜጠኞች እና የሚድያ ሠራተኞችን በተመለከተ እና በተለይም በአማራ ክልል የሕግ የበላይነትን ለማስከበር በሚል በተለያዩ የክልሉ አካባቢዎች የታሰሩ ሰዎችን አስመልክቶ የፌደራልም ሆነ የክልል የፀጥታ ኃይሎች ተጠርጣሪዎችን ለተራዘመ የቅድመ ክስ እስር ከመዳረግ፣ ጋዜጠኞችን በሥራቸው ምክንያት ከማሰር እና ከፍርድ ቤት ትዕዛዝ ውጭ ሰዎችን ከማሰር፣ ኢመደበኛ በሆኑ ማቆያዎች ከማሰር ሊታቀቡ እንደሚገባ በተደጋጋሚ ማሳሰቡ የሚታወስ ነው። በተመሳሳይ መልኩ በትግራይ ክልል ጋዜጠኞች ምስግና ስዩም፣ ተሾመ ጠማለው፣ ኃይለሚካኤል ገሰሰ እና ሃበን ሐለፎምን ጨምሮ 15 የሚዲያ ሠራተኞች ከተገባደደው የግንቦት ወር 2014 ዓ.ም. አጋማሽ ጀምሮ ተይዘው እንደሚገኙ ታውቋል።

በተለይም  በመገናኛ ብዙኃን አዋጅ ቁጥር 1238/2013 (ሚዲያ አዋጅ) መሰረት በመገናኛ ብዙኃን አማካይነት የወንጀል ድርጊት በመፈጸም የተጠረጠረ ማንኛውም ሰው ወይም አካል፣ በወንጀል ሥነ-ሥርዓት ሕግ ድንጋጌዎች መሰረት ለተጨማሪ ምርመራ በእስር እንዲቆይ ሳይደረግ ክሱ በቀጥታ በዐቃቤ ሕግ አማካኝነት ለፍርድ ቤት መቅረብ ያለበት መሆኑን በማስታወስ ኮሚሽኑ በሚድያ ሠራተኞች ላይ የተጀመሩ የሕግ ሂደቶች በዚሁ መሰረት እንዲተገበሩ ጥሪ ማቅረቡ የሚታወስ ነው፡፡ እንዲሁም በማናቸውም ጊዜ ቢሆን የተያዙና በእስር ላይ የሚገኙ ሰዎች አያያዝ የሰብአዊ መብቶችን ያከበረ ሊሆን እንደሚገባ እና በክልልም ሆነ በፌዴራል የፀጥታ አካላት የተያዙ ሰዎች የሚገኙበትን ቦታ የማሳወቅ፣ የሕግ አማካሪ እና የቤተሰብ ጥየቃን መብት የማክበር እንዲሁም በአፋጣኝ ፍርድ ቤት የማቅረብ መብቶችን ሊያከብሩ እንደሚገባ ኮሚሽኑ አሳስቧል። 

በአዲስ አበባ ከተማ ከግንቦት ወር 2014 ዓ.ም. ጀምሮ ተይዘው የቆዩ የሚድያ ሠራተኞች መካከል በተለያዩ ጊዜያት በፍርድ ቤት የዋስትና መብታቸው ተከብሮ የተለቀቁ መሆኑን ኮሚሽኑ ተመልክቷል። በአማራ ክልል ከግንቦት ወር 2014 ዓ.ም. ጀምሮ በተለይም የሚገኙበት ቦታ ሳይገለጽ፣ ፍርድ ቤት ሳይቀርቡ፣ በአብዛኛው ኢመደበኛ በሆኑ እና ከመኖሪያ አካባቢያቸው በራቀ ቦታ ለብዙ ሳምንታት ተይዘው የቆዩ በርካታ ሰዎች በባሕር ዳር ወደሚገኙ ማቆያ ቦታዎች መዛወራቸውን፣ እንዲሁም በእነዚሁ ቦታዎች ከቆዩ ሰዎች መካከል ይገኙ የነበሩ የሚድያ ሠራተኞች ፍርድ ቤት እንዲቀርቡ መደረጋቸውን ኮሚሽኑ ተመልክቷል። ሰኔ 30 ቀን 2014 ዓ.ም. የአሻራ ሚድያ እና የንስር ሚድያ ሠራተኞች በዋስ እንዲለቀቁ የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት መወሰኑን ተመልክቷል። ኢሰመኮ የሚድያ ሠራተኞችን የፍርድ ቤት ሂደት መከታተል ጨምሮ ሁሉንም በእስር ላይ የሚገኙ ሰዎችን ጉዳይ ክትትል እያደረገ ይገኛል። 

ኮሚሽኑ ክትትል ባደረገባቸው የተወሰኑ ጉዳዮች በፍርድ ቤት የዋስትና መብት የተጠበቀላቸውን ተጠርጣሪዎች በዋስትና ውሳኔው ላይ ይግባኝ ተጠይቋል ወይም ለሌላ የወንጀል ምርመራ ተጨማሪ ጊዜ አስፈልጓል በሚል ምክንያት  የፍርድ ቤት ትዕዛዞችን በመጣስና ታሳሪዎቹን በቁጥጥር ስር በማቆየት ሕገወጥ እስር እየተፈጸመ መሆኑን ተመልክቷል፡፡ በተጨማሪም በአዲስ አበባ ከተማ ጋዜጠኛ ያየሰው ሽመልስ ሰኔ 21 ቀን 2014 ዓ.ም. ከጠዋቱ 12፡00 ሰዓት፣ እንዲሁም ጋዜጠኛ አበበ ባዩ ከሰኔ 22 ቀን 2014 ዓ.ም. ከምሽቱ 4፡00 ሰዓት የሲቪል ልብስ በለበሱ የፀጥታ ኃይሎች ከተወሰዱ በኋላ ያሉበት ቦታ ያለመገለጹን ኮሚሽኑ በከፍተኛ ሁኔታ የሚያሳስበው ነው። በማኅበራዊ ሚድያ ጽሑፎቹ የሚታወቀው በላይ በቀለ ከሰኔ 21 ቀን 2014 ዓ.ም. ጀምሮ በተመሳሳይ መልኩ የሲቪል ልብስ በለበሱ የፀጥታ አካላት ከተወሰደ በኋላ ያለበት ቦታ ሳይገለጽ ተይዞ ከቆየ በኋላ ሰኔ 27 ቀን 2014 ዓ.ም. መለቀቁ ታውቋል። እንዲሁም የሚድያ ሠራተኛ  ወግደረስ ጤናው በባሕር ዳር ከሰኔ 25 ቀን 2014 ዓ.ም. ጀምሮ ተይዞ የሚገኝ መሆኑን እና ፍርድ ቤት መቅረቡ ታውቋል። 

እነዚህን እስሮች በተመለከተ የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር ዶ/ር ዳንኤል በቀለ “የዘፈቀደ፣ ሕገ ወጥ እና በተለይም ተጠርጣሪዎች የሚገኙበትን ቦታ ሳያሳውቁ የሚደረጉ እስሮች ሰዎችን ለከፍተኛ ስጋት፣ ቤተሰቦችን ለጭንቀት ዳርጓል። በመንግሥት የፀጥታ አካላት እውቅናና ሆነ ተብሎ ሰዎችን ከሕግ እይታ ውጪ እንዲሆኑ ማድረግ የአስገድዶ መሰወር ድርጊት ሊሆን የሚችል የሰብአዊ መብቶች ጥሰት ነው፡፡ በፍርድ ቤት ትዕዛዝ በዋስ እንዲፈቱ መብታቸው የተጠበቀላቸውን ተጠርጣሪዎች ከሕግ አግባብ ውጭ በቁጥጥር ስር ማቆየት የሕግ የበላይነትን በከፍተኛ ሁኔታ የሚሸረሽር ነው” ብለዋል። ስለሆነም ኮሚሽኑ የፌዴራል እና የክልል የፀጥታ አካላት በአፋጣኝ የተያዙ ሰዎች የሚገኙበትን ቦታ እንዲገልጹና ተዓማኒ ክስ የማይቀርብ ከሆነ በአፋጣኝ እንዲለቀቁ እንዲያደርጉ፤ እንዲሁም በመገናኛ ብዙኃን አማካይነት ተፈጽሟል ተብሎ ለሚጠረጠር የወንጀል ድርጊት ተጠርጣሪው ለምርመራ በእስር እንዲቆይ ሳይደረግ ክሱ በቀጥታ በዐቃቤ ሕግ አማካኝነት ለፍርድ ቤት መቅረብ ያለበት መሆኑን ኮሚሽኑ በአጽንዖት ያሳስባል።