የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ሰኔ 28 ቀን 2016 ዓ.ም. ይፋ ካደረገው 3ኛው የኢትዮጵያ ዓመታዊ የሰብአዊ መብቶች ሁኔታ ሪፖርት በተጨማሪ የማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ መብቶች ሁኔታ ላይ የሚያተኩር ባለ 26 ገጽ ዓመታዊ የዘርፍ ሪፖርት ዛሬ ይፋ አድርጓል። ሪፖርቱ ከሰኔ ወር 2015 ዓ.ም. እስከ ሰኔ ወር 2016 ዓ.ም. ያለውን ጊዜ የሚሸፍን ሲሆን፣ ኢሰመኮ በሕግ በተሰጠው ሥልጣን፣ ተግባርና ኃላፊነት መሠረት በበጀት ዓመቱ የተቀበላቸውን አቤቱታዎች፣ ያከናወናቸውን የተለያዩ የሰብአዊ መብቶች ክትትሎች፣ ምርመራዎች፣ ጥናቶች፣ የውትወታ ሥራዎች፣ በምክክር መድረኮች የተገኙ ግብአቶች እና አግባብነት ያላቸው ሰነዶችና ሌሎች የመረጃ ምንጮችን መሠረት በማድረግ የተዘጋጀ ነው።
በ2016 በጀት ዓመት ከማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ መብቶች መከበር፣ መጠበቅና መስፋፋት አኳያ መልካም እመርታዎች መኖራቸው በሪፖርቱ ተገልጿል። መንግሥት የንግድ እና ሰብአዊ መብቶች የድርጊት መርኃ-ግብር ዝግጅት መጀመሩ፤ የዓለም አቀፍ ኢኮኖሚያዊ፣ ማኅበራዊ እና የባህል መብቶች ቃልኪዳን አፈጻጸምን በተመለከተ ለዓለም አቀፉ የኢኮኖሚያዊ፣ ማኅበራዊ እና የባህል መብቶች ኮሚቴ ሊቀርብ የሚገባውን ሪፖርት ለማቅረብ ዝግጀት መጀመሩ፤ የጤና ፖሊሲው ሰብአዊ መብቶች ተኮር በሆነ መልኩ መቀረጹ፤ የገጠር መሬት አስተዳደርና አጠቃቀም አዋጅ የባለይዞታዎችን መብቶች የሚያስፋፉ ድንጋጌዎችን ባካተተ መልኩ መጽደቁ፤ እንዲሁም የመኖሪያ ቤት ኪራይ ቁጥጥር እና አስተዳደር አዋጅ የተከራዮችን ዐቅም ባገናዘበና የመኖሪያ ቤት መብትን ለማረጋገጥ በሚያግዝ ሁኔታ ሥራ ላይ መዋሉ በሪፖርቱ ከተካተቱ ቁልፍ እመርታዎች መካከል ይገኙበታል። በተጨማሪም፣ ከግጭት እና ከመምህራን ደመወዝ አለመከፈል ጋር ተያይዞ ትምህርት በተቋረጠባቸው አካባቢዎች ትምህርት እንዲጀመር ለማድረግ በመንግሥት በኩል ጥረቶች መደረጋቸው በሪፖርቱ ተጠቁሟል።
በሌላ በኩል ሪፖርቱ ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ መብቶችን በማረጋገጥ ረገድ ያሉ አሳሳቢ ሁኔታዎችን ለይቷል። ከነሐሴ ወር 2015 ዓ.ም. ጀምሮ በአማራ ክልል ከተከሰተው የትጥቅ ግጭት እና በሌሎች ክልሎችም ከቀጠለው የጸጥታ ችግር ጋር በተያያዘ መኖሪያ ቤትና የመተዳደሪያ ንብረቶችን ጨምሮ በመሠረተ ልማቶችና የአገልግሎት ተቋማት ላይ ውድመት የደረሰ ሲሆን በተለይም በምግብ፣ በጤና፣ በንብረት፣ በትምህርት፣ በሥራና ተያያዥ መብቶች ላይ ጉዳት አድርሷል። አፋር፣ አማራ እና ትግራይ ክልሎችን ጨምሮ በኢትዮጵያ የተለያዩ አካባቢዎች የተከሰተው ድርቅ ከግጭትና ከጸጥታ ችግር ጋር በተያያዘ ከሚከሰት የምርት መቀዛቀዝ እንዲሁም የመሠረታዊ ሸቀጦች ዋጋ ንረት ጋር ተዳምሮ በርካታ ሰዎችን ለምግብ እጥረት ዳርጓል። ከባድ ዝናብ ያስከተለው ጎርፍ ለምሳሌ በደቡብ እና ምሥራቅ የኢትዮጵያ አካባቢዎች በሚኖሩ ሰዎች ላይ በተለይም በሶማሊ ክልል የሰው ሕይወት ኅልፈት እና በመሠረታዊ አገልግሎቶች ላይ ጉዳት አስከትሏል። በሀገሪቱ የተወሰኑ ክፍሎች የተከሰተው የወባ፣ ኮሌራና ኩፍኝ ወረርሽኝ የጤና መብት ሁኔታን አሳሳቢ ማድረጉ፣ በ2016 በጀት ዓመት ለማኅበራዊ አገልግሎቶች የተመደበው በጀት ከ2015 በጀት ዓመት ጋር ሲነጻጸር በመቶኛ ያለው ድርሻ መቀነሱ፣ በተለያዩ አካባቢዎች በተከሰቱ ግጭቶች እና የተፈጥሮ አደጋዎች ምክንያት ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ትምህርት ቤቶች መዘጋታቸውና በርካታ ሕፃናት ከትምህርት ውጪ መሆናቸው፣ አዲስ አበባን ጨምሮ በተለያዩ ከተሞች በርካታ የንግድና መኖሪያ ቤቶች ሕጋዊ ሂደትን ባልተከተለ መልኩ እንዲፈርሱ መደረጋቸው እና የሠራተኞች ደመወዝ በወቅቱና በአግባቡ ባለመከፈሉ ምክንያት ሠራተኞች ለተለያዩ ችግሮች መዳረጋቸው በሪፖርቱ ከተመላከቱ ዋና ዋና ተግዳሮቶች እና አሳሳቢ ጉዳዮች መካከል ናቸው።
በሪፖርቱ መንግሥት በበጀት ዓመቱ የታዩ አሳሳቢ ሁኔታዎችን በመቅረፍ የማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ መብቶችን በተሟላ ሁኔታ እውን እንዲያደርግ እና ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ጉዳዮችን የሚመለከቱ ውሳኔዎችና እርምጃዎች ሕጋዊ ሁኔታን በተከተለ መልኩ ከባለመብቶች ጋር ተገቢው ውይይት ተደርጎ እንዲወሰዱ የሚሉ እና ሌሎች ምክረ ሐሳቦች ቀርበዋል። የሲቪል፣ የፖለቲካ፣ የማኅበራዊ-ኢኮኖሚያዊ መብቶች ኮሚሽነር ዶ/ር አብዲ ጅብሪል ኢሰመኮ በክትትልና በምርመራና ሥራዎቹ ላይ ተመሥርቶ የሚያቀርባቸውን ምክረ ሐሳቦች በከፍተኛ ትኩረት፣ ዕቅድና ቅንጅት መተግበር አስፈላጊ መሆኑን ጠቅሰው፣ በተለይም በሰው ሠራሽ እና በተፈጥሮ አደጋዎች ምክንያት ጉዳት የደረሰባቸው ተቋማት መልሰው እንዲቋቋሙና የተሟላ አገልግሎት እንዲሰጡ ለማድረግ መንግሥት አስፈላጊ እርምጃዎችን ሁሉ እንዲወስድ ጥሪ አቅርበዋል።