ስለ እኛ


የኢኮኖሚ፣ ማኅበራዊ እና ባሕላዊ መብቶች

የኢኮኖሚ፣ ማኅበራዊ እና ባሕላዊ መብቶች አለመከበር ተጋላጭ የሆኑት የሕብረተሰብ ክፍሎች ዝቅተኛ ገቢ ያላቸውና በልዩ ልዩ ምክንያት የተገለሉት በመሆናቸው፥ ለእነዚህ የሕብረተሰብ ክፍሎች ትኩረት በመስጠት የኢኮኖሚ፣ ማኅበራዊ እና ባሕላዊ መብቶችን የማስፋፋት፣ የማክበርና የማስከበር ስራዎችን እንሰራለን። ይህ ፕሮግራም የሚሰራባቸው ሰብአዊ መብቶች ደረጃውን የጠበቀ ኑሮ የመኖር፣ የትምህርት፣ የጤና እና ደረጃውን የጠበቀ መጠለያ የማግኘት መብቶችን ይጨምራል። በተጨማሪም፣ የባሕል መብት አካል የሆኑትን በራስ ባሕል የመሳተፍ እንዲሁም በእኩልነት፣ ሰብአዊ ክብርን በጠበቀና ከመድሎ በፀዳ መልኩ በራስ ቋንቋ የመማር መብትን ጨምሮ ለባሕል መብቶች ሙሉ ተግባራዊነት እንሰራለን። 

ምርምር በማካሄድና የውትወታ ተግባራትን በመፈጸም የኢኮኖሚ፣ ማኅበራዊ እና ባሕላዊ መብቶች እንደሌሎች ሰብአዊ መብቶች ሁሉ መከበር ያለባቸው ስለመሆኑ ግንዛቤ እንዲኖር፣በፍርድቤት የዳኝነት ሂደት እንዲረጋገጡ ፣ እነዲተገበሩና በአጠቃላይ ሰዎች የኢኮኖሚ፣ ማኅበራዊ እና ባሕላዊ መብቶቻቸው ተጠቃሚ እንዲሆኑ እንሰራለን። በተጨማሪም መብቶቹ እየተተገበሩ መሆናቸውን እንከታተላለን እንዲሁም በተለያዩ የሰብአዊ መብቶች አፈጻጸም ተመጋጋቢና ተደጋጋፊ እንዲሆን እናደርጋለን።