የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) በአፋር እና በማእከላዊ ኢትዮጵያ ክልሎች በሴት ልጅ ግርዛት ላይ ስለሚያካሂደው ግልጽ የምርመራ መድረክ ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር ሚያዝያ 28 ቀን 2017 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ከተማ ውይይት አካሂዷል። የውይይቱ ዓላማ የግልጽ ምርመራ መድረኩ ቁልፍ ባለድርሻ አካላትን ማሳወቅ እና አስፈላጊ በሆኑ በትብብርና እገዛዎች ላይ መወያየት ነው።

የውይይቱ ተሳታፊዎች

በውይይቱ ጉዳዩ በቀጥታ የሚመለከታቸው ፍትሕ ሚኒስቴር፣ ሴቶችና ማኀበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ ጤና ሚኒስቴር እንዲሁም ከአፋር እና ከማእከላዊ ኢትዮጵያ ክልሎች የሴቶችና ሕፃናት ጉዳይ ቢሮ፣ ፍትሕ ቢሮ፣ ጠቅላይ ፍርድ ቤት፣ ፖሊስ ኮሚሽን፣ ጤና ቢሮ፣ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ፣ የሀዲያ ዞን ሴቶችና ሕፃናት ጉዳይ፣ የፍትሕ፣ የፖሊስ እና ጤና ጽሕፈት ቤት የሥራ ኃላፊዎች እና ባለሙያዎች ተሳትፈዋል። በተጨማሪም በሴት ልጅ ግርዛት ላይ የሚሠሩ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች፣ የሃይማኖት ተቋማት ተወካዮች እና የኢሰመኮ የከተማ ጽሕፈት ቤቶች የሴቶች እና የሕፃናት መብቶች ባለሙያዎች ተሳታፊ ሆነዋል።

በውይይት መድረኩ ስለ ኢሰመኮ ሥልጣንና ተግባር፣ የሥልታዊ ምርመራ እና ግልጽ የአቤቱታ መቀበያ መድረክ ምንነት እና ዓላማ፣ በሴቶች ላይ በሚፈጸም ግርዛት የሚጣሱ የሰብአዊ መብቶች፣ ግልጽ የምርመራ መድረክ የማካሄድ አስፈላጊነት፣ ኢሰመኮ በአፋርና ማእከላዊ ኢትዮጵያ ክልሎች ያከናወናቸው የሰብአዊ መብቶች ሁኔታ ክትትል ግኝቶች እንዲሁም የባለድርሻ አካላትን ሚና ያካተተ ጽሑፍ ቀርቦ ውይይት ተደርጓል።

የኢሰመኮ የሴቶች እና የሕፃናት መብቶች ሥራ ክፍል ዳይሬክተር ሰላማዊት ግርማይ (በግራ) 

የማእከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ተሳታፊዎች በሀዲያ ዞን በሻሾጎ ሶሮ እና ምዕራብ ሶሮ ወረዳዎች አካባቢ በሁሉም ዕድሜ ክልል በሚገኙ ሴቶች ላይ የሚፈጸም በማኀበረሰቡ ዘንድ ‘ጨበላ’ በመባል የሚታወቅ ግርዛት በሴቶች ላይ የሚያስከትለውን የጤና እክል እና እስከ ሞት የሚደርስ ጉዳት፣ ኢሰመኮ ከክልሉና ከዞኑ የሃይማኖት መሪዎች ጋር በመቀናጀት ማኅበረሰቡን በማስተማሩ እንዲሁም በድርጊቱ ተሳታፊ የሚሆኑ አካላትን ተጠያቂ ለማድረግ በተከናወኑ ሥራዎች ድርጊቱ በከፍተኛ ሁኔታ መቀነሱን ገልጸዋል። ይሁን እንጂ ተግባሩ ሙሉ በሙሉ ባለመቀረፉ ግልጽ የምርመራ መድረኩ አስፈላጊ እና ወቅታዊ መሆኑን አመልክተዋል።

የአፋር ክልል ተሳታፊዎች በበኩላቸው በክልሉ የገጠር አካባቢዎች ግርዛት እየተፈጸመ መሆኑን እና ግርዛትን የተመለከቱ ጎጂ ልማዶች መኖራቸውን በመጥቀስ ግልጽ የምርመራ መድረክ መዘጋጀቱ ከግርዛት ጋር የተያያዙ ችግሮችን ለመቅረፍ አስተዋጽዖ እንደሚኖረው አስረድተዋል። ፖሊስን ጨምሮ የፍትሕ፣ የሴቶችና የሕፃናት እና የጤና ቢሮዎች የሥራ ኃላፊዎች እና ሌሎች ተሳታፊዎች ኢሰመኮ የሚያካሂደው ግልጽ የምርመራ መድረክ በጸረ የሴቶች ግርዛት ላይ የሚከናወኑ ተግባራትን የሚያጠናክር እንዲሁም ተያያዥ የሆኑ ጉዳዮችንም ለመፈተሽ ዕድል የሚሰጥ በመሆኑ የሚጠበቅባቸውን ሚና ለመወጣት ያላቸውን ጸኑ ፍላጎት አሳውቀዋል።

የኢሰመኮ የሴቶች፣ የሕፃናት፣ የአካል ጉዳተኞች እና የአረጋውያን መብቶች ኮሚሽነር ርግበ ገብረሐዋሪያ በሴቶች ላይ የሚፈጸም ግርዛትና ተደጋጋሚ ግርዛትን ለማስቆም ተጠያቂነትን የማረጋገጥ እርምጃ መውሰድ ብቻውን ለችግሩ የተሟላ መፍትሔ የሚያስገኝ ባለመሆኑ ከዚህ ጎን ለጎን ማኀበረሰቡን የማንቃት እና ለተጎጂዎች ድጋፍ የማድረግ ሥራዎች እንደሚጠይቅ ገልጸዋል። አክለውም ባለድርሻ አካላት በሴቶች ግርዛት ላይ የሚካሂደው ግልጽ/ይፋዊ የምርመራ መድረክ ሥራው ተጀምሮ እስከ ምክረ ሐሳብ አፈጻጸም ድረስ ድጋፍ ለማድረግና ኃላፊነታቸውን ለመወጣት የገቡትን ቃል በመጠበቅ የበኩላቸውን ድርሻ እንዲወጡ አሳስበዋል።