የባለሙያ አስተያየት ከኢሰመኮ
ዘላለም ታደሰ
በጅማ ጽሕፈት ቤት የሰብአዊ መብቶች ኦፊሰር
የአካል ጉዳተኞች እና አረጋውያን መብቶች ሥራ ክፍል

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (የተ.መ.ድ) የአረጋውያን ሥራ ቡድን (UN Open-Ended Working Group on Ageing) 13ኛው ጉባኤ ትኩረቱን የአረጋውያንን ክብር እና ሰብአዊ መብቶች ለመጠበቅ እና ለማስፋፋት ሊወሰዱ በሚገቡ እርምጃዎች፣ ምርጥ ተሞክሮዎች፣ የተወሰዱ ትምህርቶች፣ በመርቀቅ ሂደት ላይ ላለው ለዓለም አቀፉ የአረጋውያን መብቶች ስምምነት ግብአት የሚሆኑ ይዘቶችን ለማሰባሰብ እና ተጨማሪ ትኩረት የሚሹ የአረጋውያን ጉዳዮች ላይ በማድረግ እ.ኤ.አ. ከሚያዚያ 3 – 6 ቀን 2023 በአሜሪካ፣ ኒው ዮርክ ከተማ በመካሄድ ላይ ይገኛል፡፡ ይህም ዓለም አቀፍ የአረጋውያን መብቶች ስምምነትን አስፈላጊነት የሚያመለክት ሲሆን ከስምምነቱም በርካታ ውጤቶች ይጠበቃሉ፡፡ 

የተ.መ.ድ ለስታቲስቲካዊ ዓላማ የሚጠቀምበት ትርጉም የዕድሜ ዘመንን (chronological age order) መሠረት በማድረግ ዕድሜያቸው 60 እና ከዚያ በላይ የሆኑ ሰዎች አረጋውያን መሆናቸውን ይገልጻል፡፡ በአፍሪካ የአረጋውያን መብቶች ፕሮቶኮልና በኢትዮጵያ የሕግና የፖሊሲ ሰነዶች (ለምሳሌ፡- የመንግሥት እና የግል ድርጅቶች ሠራተኞች ጡረታ አዋጆች እንዲሁም ብሔራዊ የአረጋውያን የድርጊት መርኃ-ግብር) ውስጥም ተመሳሳይ ትርጓሜ ተሰጥቶታል፡፡  የዓለም ጤና ድርጅት መረጃ እ.ኤ.አ. በ 2030 በዓለም ካሉ 6 ሰዎች መካከል ቢያንስ አንዱ ዕድሜው/ዋ 60 እና ከዚያ በላይ የሆኑ አረጋዊ/አረጋዊት ሊሆን/ልትሆን እንደሚችል ትንበያ ያስቀምጣል፡፡ በመሆኑም ከጊዜ ወደ ጊዜ ቁጥራቸው እየጨመረ ያለው አረጋውያን ፍላጎታቸውን እና ሁኔታቸውን ያገናዘበ የሕግ እና የፖሊሲ ማእቀፍ በመዘርጋት ሰብአዊ መብቶቻቸውን ሙሉ በሙሉ እንዲጠቀሙ ማስቻል አስፈላጊ ነው።

በዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብቶች ሥርዓት ውስጥ በልዩ ሁኔታ አረጋውያንን የተመለከተ የሰብአዊ መብቶች ስምምነት እስከ አሁን ባይኖርም፤ ሁሉም የሰብአዊ መብቶች ስምምነቶች የአረጋውያንን መሠረታዊ መብቶችና ነጻነቶችን ለማስከበር ከፍተኛ ጠቀሜታ አላቸዉ፡፡ በተለይም ሁሉን-አቀፉ የሰብአዊ መብቶች መግለጫ (UDHR)፣ ዓለም አቀፉ የሲቪልና ፖለቲካ መብቶች እንዲሁም የኢኮኖሚ፣ ማኅበራዊ እና የባህል መብቶች ቃልኪዳኖች፣ የአካል ጉዳተኞች መብቶች ስምምነት እና በሴቶች ላይ የሚደረግ ማንኛውንም አድሎአዊ ልዩነት ለማስወገድ የተደረገው ስምምነት የያዟቸው ድንጋጌዎችና እነዚህ ድንጋጌዎችን ተከትለው የተሰጡ ጠቅላላ አስተያየቶች ተጠቃሽ ናቸው፡፡

በአህጉር ደረጃ ኢትዮጵያ በአዋጅ ቁጥር 1082/2010 ያጸደቀችውና የሕጎቿ አካል የሆነው የአፍሪካ የሰዎች እና ሕዝቦች መብቶች ቻርተር የአረጋውያን መብቶች ፕሮቶኮል የአረጋውያን መብቶችን አህጉራዊ እውነታ ከግንዛቤ በማስገባት የጸደቀ ስምምነት ነው፡፡ ይህ ስምምነት ከዓለም አቀፍ ስምምነቶች በተለየ መልኩ በማኅበረሰባችን ውስጥ ያሉ አፍሪካዊ እሴቶችን ዋጋና እውቅና የሚሰጥ ሲሆን፤ የአረጋውያንን ፍላጎት ያገናዘቡ ሕጎችና ፖሊሲዎችን የማውጣት ግዴታን፣ እኩል ዕድል የማግኘትና በውሳኔ አሰጣጥ ሂደት ውስጥ ሙሉ እና ትርጉም ያለው ተሳትፎ የማድረግ መብትን እንዲሁም ዕድሜን መሠረት ያደረጉ መሰናክሎችን ለማስወገድ የሚያስችሉ ድንጋጌዎችን ይዟል፡፡ መሰል የአረጋውያን ሰብአዊ መብቶች ላይ ትኩረቱን ያደረገ ስምምነት በሌሎች አህጉራትም የሚገኝ ቢሆንም፤ ሁሉን አቀፍ የሆነና በዓለም አቀፍ ደረጃ ሊተገበር የሚችል ዓለም አቀፍ ስምምነት መኖር ለአረጋውያን ሰብአዊ መብቶቻቸው በተገቢው እንዲከበሩ እና ክብር ያለው ኑሮ እንዲኖሩ ለማስቻል አስፈላጊ ነው።

በዓለም አቀፍ ደረጃ የአረጋውያን መብቶች ስምምነት አስፈላጊ ከሚሆንባቸው በርካታ ምክንያቶች መካከል የሚከተሉት ይጠቀሳሉ፡- 

  1. ዋና ዋናዎቹ ዓለም አቀፍ ስምምነቶች ዕድሜን መሠረት ያደረገ አድሎን በግልጽ አለመከልከላቸው፡- ከዘጠኙ ዋና ዋና ዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብቶች ስምምነቶች መካከል ዕድሜን መሰረት ያደረገ መድልዎን በግልጽ የሚከለክለው ፍልሰተኛ ሠራተኞችን እና ቤተሰቦቻቸውን ለመጠበቅ የወጣው ዓለም አቀፍ ስምምነት ብቻ ነው፡፡ ከቀሪዎቹ ስምምነቶች መካከል የአካል ጉዳተኞች መብቶች እና በሴቶች ላይ የሚደረግ ማንኛውንም አድሎአዊ ልዩነት ለማስወገድ የተደረጉት ስምምነቶች በግልጽ ባይሆንም፤ ለአረጋውያን የሚቀርቡ አገልግሎቶች ዕድሜን ያገናዘቡ መሆን እንዳለባቸው እውቅና የሚሰጡ ጥቂት ድንጋጌዎችን ይዘዋል፡፡ ከእነዚህ ውጪ ዓለም አቀፉ የሲቪልና ፖለቲካ መብቶች እንዲሁም የኢኮኖሚ፣ ማኅበራዊ እና የባህል መብቶች ቃልኪዳኖች አድሎአዊ ልዩነት ለመፈጸም መነሻ ሊሆኑ የሚችሉ ምክንያቶችን ሲዘረዝሩ “ዕድሜን” በግልጽ አልጠቀሱም፡፡ በዚህም “ዕድሜን” መሠረት በማድረግ የሚፈጸሙ አድሎአዊ ልዩነቶች “በሌላ ሁኔታ/Other status” በሚለው ውስጥ ተካትተው የሚተረጎሙ ናቸው፡፡ ይኹንና “ዕድሜ” መሠረት ተደርጎ የሚፈጸም አድሎአዊ ልዩነት “በሌላ ሁኔታ/Other status” በሚለው ማእቀፍ ውስጥ ተካትቶ እንዲቀጥል ማድረግ ግልጽነት የጎደለውና ለትርጉም የሚጋለጥ ብሎም በዚህ መሠረት ጥሰት ለተፈጸመባቸው አረጋውያን ምላሽ የመስጠት ሂደቱን አዳጋች የሚያደርግ ነው፡፡ በመሆኑም የአረጋውያንን ልዩ ልዩ ፍላጎቶችና ተግዳሮቶች ያቀፈ፣ “ዕድሜን” መሠረት ያደረገ አድሎአዊ ልዩነት ማድረግን በግልጽ የሚከለክል የሕግ ማእቀፍ ማዘጋጀት አስፈላጊ ነው፤
  2. በባለግዴታዎች/በመንግሥታት ላይ ተጠያቂነትን  ለማረጋገጥ፡ ምንም እንኳን በሌሎች ዓለም አቀፍ ሕጎች የአረጋውያን ሰብአዊ መብቶች ይጠበቃሉ ተብሎ የሚታመን ቢሆንም፤ በባለግዴታዎች/በመንግሥታት ላይ ጥብቅ ክትትል እና ኃላፊነትን  ማረጋገጥ የሚቻለው ራሱን የቻለ ውጤታማ የመከታተያ ሥርዓት (effective monitoring mechanism) ያለው ዓለም አቀፍ የአረጋውያን ሰብአዊ መብቶች ጥበቃ ሥርዓት  ሲኖር ሲሆን እንዲሁም እንደሌሎች ለመድልዎ የተጋለጡ የሕብረተሰብ ክፍሎች ሁሉ በአረጋውያን ላይ የሚደርሱ ጥቃቶችን በተመለከተ ተገቢና ውጤታማ የሆኑ እርምጃዎችን ለመውሰድ የሚያስችል የሕግ ማእቀፍ አስፈላጊ በመሆኑ፤
  3. አረጋውያን ለጥቃት እና ለሰብአዊ መብቶች ጥሰቶች ተጋላጭ በመሆናቸው፡ አረጋውያን ልክ እንደ አካል ጉዳተኞች፣ ሴቶች እና ሕፃናት ከሌላው ማኅበረሰብ በተለየ ሁኔታ ለጥቃት እና ለአድሎአዊ ልዩነት የተጋለጡ ናቸው፡፡ ይህ የተጋላጭነት ሁኔታ ደግሞ በግጭት እና በተፈጥሮ አደጋ ሁኔታዎች፣ በኢኮኖሚያዊ ዐቅም፣ በጾታ፣ በአካል ጉዳትና በመሳሰሉት ምክንያቶች ተደራራቢ በመሆኑ እና ይህን የአረጋውያንን ልዩ ፍላጎት መሰረት ያደረገ ሕግ አስፈላጊ በመሆኑ፤
  4. በአረጋውያን ላይ የሚደርሱ ጥቃቶች ድብቅ እና በዓይነታቸው የተለዩ መሆናቸው፡ በአረጋውያን ላይ የሚደርሱ ጥቃቶች በአብዛኛው በቤት እና በእንክብካቤ መስጫ ተቋማት ውስጥ በቅርብ ሰዎች የሚፈጸሙ በመሆናቸው ታቅዶ የሚተገበር ጥብቅ ክትትል ከሌለ ሊታወቁ የሚችሉበት ዕድል ጠባብ ነው፡፡ በተጨማሪም የጥቃት ዓይነቶቹ የተለዩ በመሆናቸው እነዚህን የጥቃት ዓይነቶች እና ምልክቶቻቸውን በዝርዝር የሚይዝ ዓለም አቀፍ ሕግ መኖሩ የጥቃት ዓይነቶቹን ለመለየት የሚያስችል በመሆኑ፤
  5. በዓለም አቀፍ ደረጃ የአረጋውያን ቁጥር እየጨመረ መምጣቱ፡ ዕድሜያቸው ከ18 – 60 ዓመት የሆኑ ሰዎች ቁጥር ከጠቅላላው የሕዝብ ቁጥር አንጻር ከፍተኛ በመሆኑና የሰው ልጆች በሕይወት የመቆየት ምጣኔ (Life expectancy rate) እየጨመረ በመምጣቱ የዚህን ዓለም አቀፍ ሕግ ጥበቃ የሚሹ ሰዎች ቁጥርም ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ በመሆኑ አረጋውያን በአረጋዊነት ዘመናቸው የሚገጥሟቸውን ተግዳሮቶች ታሳቢ ያደረገ የሕግ ማእቀፍ አስፈላጊ በመሆኑ፤ 
  6. ለአረጋውያን የሚደረጉ ድጋፎችና እንክብካቤዎች ከሰብአዊ መብቶች ዕይታ (human rights model) ይልቅ በእርዳታ ዕይታ (charity model) የሚተገበሩ በመሆኑ፡ በአብዛኛው በመንግሥትም ሆነ መንግሥታዊ ባልሆኑ ተቋማት በኩል ለአረጋውያን የሚደረጉ ድጋፎችና የእንክብካቤ አገልግሎቶች እንደ ሰብአዊ መብት ከመታየት ይልቅ በችሮታና በጎ ፈቃድ ላይ ብቻ የተመሠረቱ እና የመልካምነት መገለጫ የሆኑ ሥራዎች ተደረግው ይቆጠራሉ፡፡ ይህን ዓይነቱን የተዛባ እሳቤ ለማስቀረት የሚያስችልና ለአረጋውያን የሚደረግ ድጋፍና እንክብካቤን እንደ መብት እውቅና የሚሰጥ አስገዳጅ የሕግ ማእቀፍ አስፈላጊ በመሆኑ፤
  7. አረጋውያን በሀገራቸው እንዲሁም በዓለም አቀፍ ደረጃ ያላቸውን ተጽእኖ ፈጣሪነት ለማሳደግአረጋውያን በልምድ ያካበቱትን እውቀታቸውን በሀገርና ዓለም አቀፍ ጉዳዮች ላይ ሰፊ፣ ንቁ፣ ውጤታማ እና ትርጉም ያለው ተሳትፎ እንዲያደርጉ በማስቻል እውቀትን ከማስተላለፍ፣ ድህነትን ከመቀነስ፣ ከሰላም ግንባታ እና ከመሳሰሉት ጉዳዮች አንጻር ለማኅበረሰባቸው ሊያበረክቱ የሚችሉት አስተዋጽዖ ከፍተኛ በመሆኑ እና ይህን የተሳትፎ መብታቸውን ጥበቃ የሚያደርግ የሕግ ማእቀፍ መቅረጽ ተገቢ ነው።

በአጠቃላይ በዓለም አቀፍ ደረጃ የተሟላ የአረጋውያን መብቶች ስምምነትን ማጽደቅ፡-

  • ዕድሜን መሠረት አድርገው የሚፈጸሙ አድሎአዊ ድርጊቶችን ለመቀነስ ብሎም ለማስቀረት፤
  • መንግሥት በአረጋውያን ላይ ያሉትን ፖሊሲዎች፣ ሕጎች እና ፕሮግራሞች እንዲያሻሽል ለማበረታታት ብሎም ለማስገደድ፤
  • አረጋውያን የሚያጋጥማቸውን ዘርፈ-ብዙ አድሎአዊ አሠራሮችና የመብት ጥሰቶች ትኩረት እንዲያገኙና ተጠያቂነትን ለማስፈን የሚረዱ አረጋውያን ተኮር (age-friendly) የፍትሕና የተጠያቂነት ሥርዓትን ለማጎልበት ይረዳል፡፡

በተጨማሪም አረጋውያን በግልም ሆነ በሕብረት መብቶቻቸውን አውቀው እንዲጠይቁና ለመብቶቻቸው እንዲታገሉ ለማስቻል፣ በአረጋውያን ማኅበራት እና በሰብአዊ መብቶች ተሟጋቾች በኩል በቂ ግንዛቤና ትምህርት እንዲሰጥ እና የመሳሰሉት ጥቅሞች ያሉት በመሆኑ በዓለም አቀፍ ደረጃ የተጀመረው የአረጋውያን መብቶች ስምምነትን የማውጣት እንቅስቃሴ ሊደገፍ እና በፍጥነት ተግባራዊ ሊደረግ ይገባል፡፡