የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) በአካል ጉዳተኞች ሰብአዊ መብቶች ዙርያ ዕውቀትን፣ አመለካከትን እና ክህሎትን ለማጎልበት ከ2014 ዓ.ም. ጀምሮ እየተገበረ የቆየው የስልጠና መርኃ ግብር ያስገኘውን ውጤት በመመዘን ስልጠናውን ለማጠናከር ታኅሣሥ 3 ቀን 2017 ዓ.ም. ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ውይይት አድርጓል። በውይይቱ ኢሰመኮ በተለያየ ጊዜ የሰጠውን የአሰልጣኞች ስልጠና ወስደው በዋና አሰልጣኝነት ሌሎችን ሲያሰለጥኑ የነበሩ አካል ጉዳተኞች እና የአካል ጉዳተኞች ማኅበራት ተወካዮች ተሳትፈዋል።
የስልጠና መርኃ ግብሩ ተቀርጾ ላለፉት 2 ዓመታት ሲሰጥ የቆየ ቢሆንም አሁንም የስልጠና ፍላጎቶች ያሉ በመሆኑ የስልጠናውን ተደራሽነት ማስፋፋት በሚቻልባቸው ሁኔታዎች ላይ ውይይት ተደርጓል። በውይይቱ በኢሰመኮ የሰብአዊ መብቶች ትምህርት ሥራ ክፍል አማካኝነት ሲሰጥ የቆየው ስልጠና በአካል ጉዳተኞች ሰብአዊ መብቶች ዙሪያ ዕውቀትን፣ አመለካከትንና ክህሎትን ለማዳበር፤ የአካል ጉዳተኞችን ሰብአዊ መብቶች ለማስጠበቅና ለማስፋፋት እንዲሁም ተግባራዊ እርምጃ ለመውሰድ እገዛ ማድረጉ ተገልጿል።
ተሳታፊዎች በስልጠናው የአካል ጉዳተኞች ሰብአዊ መብቶችን በተመለከተ በማኅበረሰቡ ዘንድ ያለውን የተዛባ አመለካከት ለማስተካከል እንዲህ ዓይነት ስልጠናዎች በብዛትና በጥራት ተጠናክረው ሊቀጥሉ እንደሚገባ ሐሳብ ቀርቧል። ተሳታፊ ማኅበራት በበኩላቸው ስልጠናውን ተቋማዊ ይዘት ባለው መልኩ ለአባላቶቻቸው መስጠት የሚችሉባቸውን ሁኔታዎች ለማመቻቸት በልዩ ትኩረት እንደሚሠሩ ቃል ገብተዋል።
የኢሰመኮ የሴቶች፣ የሕፃናት፣ የአካል ጉዳተኞች እና የአረጋውያን መብቶች ኮሚሽነር ርግበ ገብረሐዋሪያ በአካል ጉዳተኞች ሰብአዊ መብቶች ላይ የሚሰጠው ስልጠና የአካል ጉዳተኞችን ሰብአዊ መብቶች ከማስጠበቅ እና ከማስከበር አኳያ የሚኖረውን ጉልህ ሚና ገልጸው፣ ይህ መድረክ መዘጋጀቱ የስልጠናውን ቀጣይነት ከማረጋገጥ ባሻገር በመድረኩ የተሰጡ ግበአቶች ስልጠናዎች በተሻለ የጥራት ደረጃ እንዲቀርቡ ለማድረግ ያስችላል ብለዋል።