የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) የፖለቲካ ፓርቲዎች መርኃ ግብሮች የአካል ጉዳተኞችን እና የአረጋውያንን ሰብአዊ መብቶች ያገናዘቡ እንዲሆኑ ለማስቻል ያለመ የውይይት መድረክ ኅዳር 9 ቀን 2018 ዓ.ም. በአዲስ አበባ አካሂዷል።

የውይይቱ ተሳታፊዎች

መድረኩ የተዘጋጀው ኢሰመኮ ሰብአዊ መብቶች ‘‘በማንኛውም ዜጋ፣ በመንግሥት አካላት፣ በፖለቲካ ድርጅቶች እንዲሁም በሌሎች ማኅበራት’’ መከበራቸውን የማረጋገጥ ኃላፊነቱን መሠረት በማድረግ፣ ለማሳያነት በተመረጡ የተወሰኑ ሀገር አቀፍ የፖለቲካ ፓርቲዎች የፖለቲካ መርኃ ግብሮች እና ሌሎች ሰነዶች ላይ በተለይም ከአካል ጉዳተኞች እና አረጋውያን መብቶች አንጻር ያደረገውን መነሻ ጥናት ተከትሎ ነው። በውይይቱ በሀገር አቀፍ ደረጃ የሚንቀሳቀሱ 20 የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ እና የሚመለከታቸው ሌሎች ባለድርሻ አካላት ተወካዮች ተሳትፈዋል።

አካል ጉዳተኞች እና አረጋውያን የሚያጋጥሟቸውን ተግዳሮቶች እንዲሁም በዓለም አቀፍ፣ አህጉራዊ እና ብሔራዊ የሰብአዊ መብቶች ማዕቀፎች ዕውቅና የተሰጣቸው የአካል ጉዳተኞች እና አረጋውያን መብቶችን አስመልክቶ ማብራሪያ የተሰጠ ሲሆን፣ በኢሰመኮ የተዘጋጀው መነሻ ጥናት ለተሳታፊዎች በዝርዝር ቀርቦ ውይይት ተደርጎበታል። በመነሻ ጥናቱ የተዳሰሱት የፖለቲካ ፓርቲዎች ሰነዶች ኢትዮጵያ ያጸደቀቻቸውን ዓለም አቀፍ ስምምነቶችን ለማክበር እና በስምምነቶቹ የተካተቱ ሰብአዊ መብቶችንም በሕገ መንግሥቱ ሳይሸራረፉ ለማካተት ቁርጠኛ አቋም እንዳላቸው በጥቅሉ የገለጹ ቢሆንም፤ የአካል ጉዳተኞች እና አረጋውያን መብቶችን ከማካተት አንጻር ክፍተቶች ያሉባቸው መሆኑ በመድረኩ ተገልጿል። የአካል ጉዳተኞች እና አረጋውያን ጉዳዮች በአንድ የፖለቲካ ፓርቲ ሰነድ ከሕገ መንግሥት ማሻሻያ ጋር ተያይዞ አረጋውያን ንቁ ተሳትፎ እንዲያደርጉ ጥረት እንደሚያደርግ ከመግለጹ እና በተወሰኑ ፓርቲዎች ሰነዶች ውስጥ ከማኅበራዊ መርኃ ግብሮች ጋር ብቻ በተገናኘ ከመቅረቡ በስተቀር በበቂ ሁኔታ አለመካተታቸው ተመላክቷል።

በመድረኩ የተሳተፉ የፖለቲካ ፓርቲዎች ተወካዮች ኢሰመኮ ያከናወነውን የመነሻ ጥናት መሠረት በማድረግ ያዘጋጀው የውይይት መድረክ የድርጅቶቻቸውን መርኃ ግብሮች አካታችነት ለመገምገም እና ማሻሻያዎችን ለማድረግ ግንዛቤ የፈጠረላቸው መሆኑን ገልጸው፤ ለአካል ጉዳተኞች እና አረጋውያን የፖለቲካ ተሳትፎ መሻሻል የጋራ ጥረት እንደሚያስፈልግ አስረድተዋል።

ጥበቡ ኃይሉ፣ የኢሰመኮ የአካል ጉዳተኞች እና የአረጋውያን መብቶች ሥራ ክፍል ዳይሬክተር

የኢሰመኮ የአካል ጉዳተኞች እና የአረጋውያን መብቶች ሥራ ክፍል ዳይሬክተር ጥበቡ ኃይሉ የፖለቲካ ፓርቲዎች በመርኃ ግብሮቻቸው አካል ጉዳተኞችን እና አረጋውያንን ጨምሮ ለሰብአዊ መብቶች ተጋላጭ የሆኑ የማኅበረሰብ ክፍሎች ጉዳዮችን በበቂ ሁኔታ ማካተታቸውን ማረጋገጥ እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል፡፡ አክለውም የፖለቲካ ፓርቲዎች በመርኃ ግብሮቻቸው እና አሠራሮቻቸው ላይ አካል ጉዳተኞችን እና አረጋውያንን ታሳቢ ያደረገ ፍተሻ እና እንደአስፈላጊነቱ ማሻሻያ ማድረጋቸው ያለውን ጠቀሜታ አስረድተዋል።