የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) በባሕርይ እና በማኅበራዊ ለውጥ ላይ በማተኮር የሚሠሩ ባለድርሻ አካላት በአካል ጉዳተኞች እና በአረጋውያን ሰብአዊ መብቶች ዙሪያ ያላቸውን ግንዛቤ ለማዳበር፤ እንዲሁም እነዚህን የኅብረተሰብ ክፍሎች የተመለከቱ ሥራዎች ሊሠሩ የሚችሉበትን ሁኔታ ለመፍጠር የሚያስችል ስልጠና በግንቦት 18 እና 19 ቀን 2015 ዓ.ም. በአዳማ ከተማ ሰጥቷል፡፡ ስልጠናው በዘርፉ ከሚሠሩ መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማት የተውጣጡ ባለሙያዎችን ያሳተፈ ሲሆን ከነዚህም መካከል አምስቱ አካል ጉዳተኞች ናቸው፡፡
የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠናው በአጠቃላይ በሰብአዊ መብቶች ፅንሰ ሐሳብ ዙሪያ እንዲሁም በልዩ ሁኔታ በአካል ጉዳተኞች እና በአረጋውያን ሰብአዊ መብቶች ላይ በማተኮር የተሰጠ ሲሆን ተሳታፊዎች በሥራዎቻቸው ውስጥ አረጋውያንን እና አካል ጉዳተኞችን አካተው ለመሥራት የሚችሉበትን ዐቅም የሚያዳብሩ ክንውኖች እና የቡድን ውይይቶች የተካተቱበት ነበር፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ሁለት አካል ጉዳተኞች ልምዳቸውንና ታሪካቸውን ያጋሩበት የሕያው ቤተ መጻሕፍት (Living Library) መርኃ ግብር የስልጠናው አካል ተደርጓል፡፡
ተሳታፊዎች አሳታፊና አስተማሪ ከሆነው የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና ያገኙትን ዕውቀት ወደ ተግባር የሚቀይሩበት ሁኔታ ላይ በማተኮር የሚሠሩ መሆኑን ገልጸዋል። የኢሰመኮ የአካል ጉዳተኞች እና የአረጋውያን መብቶች ኮሚሽነር ርግበ ገብረሐዋሪያም በባሕርይና በማኅበራዊ ለውጥ ዙሪያ የሚሠሩ አካላት በማንኛውም ሥራቸው ውስጥ ብዝኃነትን ማዕከል በማድረግ የአረጋውያንን እና የአካል ጉዳተኞችን ሰብአዊ መብቶች በማስፋፋት ረገድ የበኩላቸውን ሊወጡ ይገባል ሲሉ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡