የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) እና የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ትብብር መድረክ ጠቅላላ ጉባኤ ጥቅምት 28 ቀን 2018 ዓ.ም. በቢሾፍቱ ከተማ ተካሂዷል። በጉባኤው ላይ የትብብር መድረኩ አባል የሆኑ 36 የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ተወካዮች እንዲሁም የኢሰመኮ ኃላፊዎችና ባለሙያዎች ተሳትፈዋል። ጉባኤው ባለፈው በጀት ዓመት በትብብር መድረኩ በተከናወኑ ተግባራትና በተስተዋሉ ተግዳሮቶች ዙሪያ ለመወያየት እና በቀጣይ በጋራ በሚከናወኑ ሥራዎች ላይ ለመመካከር ያለመ ነው።


የኢሰመኮ እና የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች የትብብር መድረክ የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ በቀደመው በጀት ዓመት የተከናወኑ ሥራዎች፣ ስኬቶች፣ ያጋጠሙ ተግዳሮቶች እና በቀጣይ ሊወሰዱ የሚገባቸው እርምጃዎች በዝርዝር ቀርበዋል። በተጨማሪም በጉባኤው ላይ የትብብር መድረኩን ለማስተዳደር ይረዳ ዘንድ የተሻሻለው ዝክረ ተግባር እና ረቂቅ የሀብት ማሰባሰቢያ ስትራቴጂ ቀርቦ ከተሳታፊዎች ጋር ውይይት ተደርጎበት ጸድቋል።


ከዚህ በፊት ከነበሩት 4 ንዑስ ዘርፎች ማለትም ከሰብአዊ መብቶች ክትትልና ምርመራ፣ ከሽግግር ፍትሕ፣ ከሴቶችና ሕፃናት መብቶች እንዲሁም ከአካል ጉዳተኞችና አረጋውያን መብቶች በተጨማሪ የሰብአዊ መብቶች ትምህርት እና የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች፣ ስደተኞችና ፍልሰተኞች ጉዳዮችን የሚያስተባብሩ 2 ተጨማሪ ንዑስ ዘርፎች እንዲቋቋሙ የቀረበውን አስተያየት ጉባኤው ያጸደቀ ሲሆን የትብብር መድረኩን የሚመሩ አዲስ የሥራ አስፈጻሚ አባላትም ተሰይመዋል።
የትብብር መድረኩ በርካታ ችግሮችን አልፎ አሁን ያለበት ደረጃ እንዲደርስ በጎ አስተዋጽዖ ላበረከቱ የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላት እና ተባባሪ ሊቀመንበሮች የምስጋና የምስክር ወረቀት ተሰጥቷቸዋል።

የኢሰመኮ የፕሮግራምና አጋርነት ሥራ ክፍል ከፍተኛ ዳይሬክተር ማንያውቃል መኮንን ኢሰመኮ ከሲቪል ማኅበራት ጋር የሚያደርገው ትብብር ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ መምጣቱን ጠቅሰው፤ ለሰብአዊ መብቶች መስፋፋት በትብብር የሚከናወኑ ተግባራት እንደሚቀጥሉ አረጋግጠዋል። የትብብር መድረኩን ተደራሽነት ለማስፋት በተለያዩ ክልሎች ተመሳሳይ መድረኮችን ማስፋፋት እንደሚገባም ገልጸዋል።