የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ለ3ተኛ ጊዜ የሚያካሂደው የሰብአዊ መብቶች ፊልም ፌስቲቫል ላይ ለዕይታ የሚቀርቡ የአጫጭር ፊልሞች እና የፎቶግራፍ ውድድር የሚያካሂድ መሆኑን እንዲሁም ውድድሩ መስከረም 22 ቀን 2016 ዓ.ም. በይፋ ተጀምሮ ጥቅምት 23 ቀን 2016 ዓ.ም. ድረስ ለተወዳዳሪዎች ክፍት ሆኖ እንደሚቆይ ቀደም ሲል ባወጣው መግለጫ መግለጹ ይታወቃል። የኪነጥበብ ሥራዎቻቸውን በኮሚሽኑ ጽሕፈት ቤቶች በአካል በመገኘት እና በሌሎች መንገዶች ያቀረቡ ባለሙያዎች ቢኖሩም ለተጨማሪ ተወዳዳሪዎች ዕድል ለመስጠት እና በውድድሩ ለመሳተፍ ፍላጎት ያላቸው ባለሙያዎች የጀመሯቸውን ሥራዎች ለማጠናቀቅ ተጨማሪ ጊዜ በመጠየቃቸው የውድድር ጊዜው እስከ ጥቅምት 30 ቀን 2016 ዓ.ም. ድረስ ተራዝሟል።

ወጣቶች እና ታዳጊዎች እንዲሁም የኪነጥበብ ዘርፍ ባለሞያዎችን ጨምሮ በኪነጥበብ ሥራ ለመሰማራት ያቀዱ እና ሰብአዊ መብቶች ባህል የሆኑባት ኢትዮጵያን ለማየት የበኩላቸውን አስተዋጽዖ ለማበርከት የሚፈልጉ ሁሉ ይህንን መልካም አጋጣሚ በመጠቀም በውድድሩ እንዲሳተፉ ኮሚሽኑ በድጋሚ ጥሪውን ያቀርባል።

ቀለል ያሉ የቴክኒክ መስፈርቶች የተዘጋጀላቸው እነዚህ የውድድር ዘርፎች፤ ፍላጎት ያለው ማንኛውም ግለሰብ በውድድሩ እንዲሳተፍ ምቹ አጋጣሚን ፈጥረዋል። ውድድሩ መንግሥታዊ እና መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማት፣ የሚዲያ እና የኮሙኒኬሽን ድርጅቶች፣ የሲቪክ ማኅበረሰብ ድርጅቶች፣ የመገናኛ ብዙኃን ወይም የስልጠናና ትምህርት ሰጪ ተቋማት፣ እንዲሁም በእነዚህ ተቋማት የሚሠሩ፣ የሚሰለጥኑ፣ የሚማሩ እና የሚያስተምሩ ግለሰቦች እራሳቸውን ወክለው/በግል መሳተፍ ይችላሉ።

የ2016 ዓ.ም. የኢሰመኮ የሰብአዊ መብቶች ፊልም ፌስቲቫል በሕይወት የመኖር መብት እና በቂ የሆነ መኖሪያ ቤት የማግኘት መብት ላይ የሚያተኩር ሲሆን፣ የዘንድሮ ዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብቶች ቀን ዓለም አቀፉን የሰብአዊ መብቶች መግለጫ 75ኛ ዓመት የሚታሰብበት ዝግጅት በመሆኑ ልዩ ያደርገዋል። የፎቶግራፍ ውድድሩ በቂ የሆነ መኖርያ ቤት የማግኘት መብት ላይ የሚያተኩር ሲሆን ለባለሞያች እና ለጀማሪዎች (አማተር) ክፍት ነው። በሕይወት የመኖር መብት ላይ የሚያተኩረው የአጫጭር ፊልም ውድድሩ ደግሞ ሁለት የውድድር ዘፎች አሉት። በአንድ በኩል በተንቀሳቃሽ ስልክ (ሞባይል) የተቀረጸ እና ከ9 ደቂቃዎች ያልበለጠ አጭር ፊልም ዘርፍ ጀማሪዎችንም ባለሞያዎችንም የሚያሳትፍ፣ በሌላ በኩል በተለይ ለባለሞያዎች ብቻ የተዘጋጀ እና ከ25 ደቂቃዎች ያልበለጠ ዘጋቢም ሆነ ልብ ወለድ ትረካ ፊልሞችን የሚያወዳድር ነው።

በሁሉም ዘርፍ ለሚወዳደሩ ተሳታፊዎች ልዩ ልዩ የዕውቅና ሰርተፍኬቶች እና ለአሸናፊዎች በተለይም በየውድድር ዘርፉ ከአንደኛ እስከ ሦስተኛ ደረጃ ለሚወጡ የገንዘብ ሽልማቶች ተዘጋጅተዋል።

ደረጃየፎቶግራፍ ውድድር አሸናፊዎችየአጫጭር ፊልሞች ውድድር አሸናፊዎች
የጀማሪ/የአማተርየባለሞያ/የፕሮፌሽናል
አንደኛ40 ሺህ50 ሺህ150 ሺህ
ሁለተኛ30 ሺህ40 ሺህ120 ሺህ
ሦስተኛ20 ሺህ30 ሺህ100 ሺህ
ልዩ ትኩረት የማኅበርሰብ ክፍሎች ቦነስ/ማበረታቻ የገንዘብ ሽልማት፡ በሁሉም ዘርፍ እና በሁሉም ደረጃ፡ 5000 ሺህ ብር

——–

የፎቶግራፍ እና የአጫጭር ፊልም ውድድሮች የተሳትፎ ቅጽበሁለቱም ዘርፍች የተቀመጡ ውድድር የቴክኒክ መስፈርቶች እና የውድድሩ አጠቃላይ መመሪያዎች እና ደንቦች ይመልከቱ።