የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) እና የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተ.መ.ድ.) የሰብአዊ መብቶች ከፍተኛ ኮሚሽነር ጽሕፈት ቤት ከሐምሌ ወር 2014 ዓ.ም. እስከ መጋቢት ወር 2015 ዓ.ም. ድረስ በኢትዮጵያ በተለያዩ አካባቢዎች በሽግግር ፍትሕ ጉዳይ ላይ ከተጎጂዎችና ጉዳት ከደረሰባቸው ማኅበረሰቦች ጋር ባደረጉት ምክክር የተገኙ ግኝቶችን በተመለከተ ባለ 90 ገጽ ሪፖርት ዛሬ ይፋ አድርገዋል። ሪፖርቱ  ተጠያቂነትን፣ እውነትን መፈለግ፣ ማካካሻ ማድረግ/ካሳ መስጠትን፣ ጥሰቶች እንዳይደገሙ ዋስትና መስጠትን እና ዕርቅን ማስፈን በመሳሰሉት ዋና ዋና የሽግግር ፍትሕ አላባዎች/ክፍሎች እና ግቦች ላይ አጽንዖት በመስጠት የተሳታፊዎችን ዕይታ እና ፍላጎቶችን ያብራራል። ይህ ሪፖርት የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶችን በመፍታት ረገድ ባህላዊ የግጭት አፈታት ሥርዐቶች ሊኖራቸው ስለሚችለው ሚና ተጎጂዎች ያላቸውን አመለካከት ያካትታል። ኢሰመኮ እና የተ.መ.ድ. የሰብአዊ መብቶች ከፍተኛ ኮሚሽነር ጽሕፈት ቤት በዛሬው ዕለት ይፋ ያደረጉት ይህ ሪፖርት፣ ሁለቱ ተቋማት በታኅሣሥ 6 ቀን 2015 ዓ.ም. ያወጡትን የጋራ ምክረ ሐሳቦችን እና ቁልፍ ግኝቶችን ያካተተ አጠር ያለ መሪ ሰነድ (Advisory Note) የሚያሟላ  ነው።

ኢሰመኮ እና የተ.መ.ድ. የሰብአዊ መብቶች ጽሕፈት ቤት ለ8 ወራት ያክል ሲካሄዱ የቆዩት የማኅበረሰብ ምክክሮች  ባጠቃላይ  805 ሰዎች የተሳተፉበት ሲሆን፣ እነዚህም  የተጎጂዎችንና ቤተሰቦቻቸውን፣ የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮችን፣ የአካል ጉዳተኞችን፣ ባህላዊና የሃይማኖት መሪዎችን እንዲሁም በሰብአዊ መብቶችና ሰላም ጥረት ላይ የሚሳተፉ ሀገር በቀል የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶችን ያካተቱ ናቸው፡፡ ምክክሮቹ በአፋር፣ በአማራ፣ በሐረሪ፣ በኦሮሚያ፣ በሶማሊ እና በትግራይ ክልሎች እንዲሁም በድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ተካሂደዋል። ከሃይማኖት መሪዎች ጋር በሀገር አቀፍ ደረጃ ተጨማሪ ምክክር ተካሂዷል።

ይህ ሪፖርት ቀደም ሲል ለተፈጸሙ የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶች በተሟላ መልኩ ተገቢውን ምላሽ መስጠት አስፈላጊነትን በግልጽ የሚያመላክትና የሚያጠናክር ነው። በተጨማሪም የሰብአዊ መብቶች ጥሰት ፈጻሚዎችን ተጠያቂ ማድረግ፣ እውነትን መፈለግ፣ ለተጎጂዎች ካሳ መስጠትን እና ተመሳሳይ የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶች ዳግመኛ እንዳይከሰቱ ዋስትና መስጠትን የሚያጠቃልል ሁሉን አቀፍ የሽግግር ፍትሕ ሂደት መተግበር አስፈላጊነት ላይ አብዛኛዎቹ ተጎጂዎች የሚስማሙበት/የሚጠይቁት እንደሆነ በሪፖርቱ ተመላክቷል። ከተለያዩ አካባቢዎች የተውጣጡ ተጎጂዎችና ማኅበረሰቦች የገለጹትን የፍትሕ ፍላጎት ለማሟላት፣ በኢትዮጵያ ለተፈጸሙ የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶች ምላሽ የሚሰጥ፣ ሁለንተናዊ አሠራርን የተከተለ፣ መጠነ ሰፊ የሽግግር ፍትሕ ሂደት ተግባራዊ ማድረግ ያስፈልጋል።

ተሳታፊዎች አጽንዖት ሰጥተው ካሰፈሯቸው ወሳኝ የሆኑ ፍላጎቶች አንዱ ለሰብአዊ መብቶች ጥሰቶች ፍትሕ እና ተጠያቂነት ማስፈን ነው። ተጠያቂነትን በተመለከተ ከወንጀል ኃላፊነት ባሻገር የተለያዩ እና እንደአስፈላጊነቱ ከሁኔታዎች ጋር ሊጣጣሙ የሚችሉ አሠራሮችን የሚከተል ሰፋ ያለ  የፍትሕ ፅንሰ ሐሳብ/ትርጓሜ/አረዳድ ያመላክታል። በዚህም መሠረት የፍትሕ ፅንሰ ሐሳብ የገንዘብ ካሳ ማግኘትን፣ ለሰብአዊ መብቶች ጥሰቶች መነሻ የሆኑትን የሥር ምክንያቶች ለይቶ ማወቅን፣ ከፍርሀት/ከሥጋት ነጻ ሆኖ መኖርን፣ ነጻ የሆነ እውነትን የማፈላለግ (truth seeking) እና የማውጣት ሂደትን፣ መሠረታዊ የሆኑ አገልግሎቶችን ማግኘትን፣ መብቶችን መልሶ መጠቀም ማስቻልን እና ለተፈናቃዮች ዘላቂ መፍትሔ መስጠትን ያጠቃልላል።

በሀገሪቱ ውስጥ አለመተማመንን እና ተደጋጋሚ ሁከትን የሚፈጥሩ የሐሰት እና አወዛጋቢ ትርክቶችን አዙሪት ለመስበር፣ ግጭቶችን በዘላቂነት ለመፍታት፣ ዘላቂ ሰላምን ለማስፈን፣ እንዲሁም ተጎጂዎች የሚካሱበትን ሥርዐትን ለማመቻቸት፤ የእውነትን ማውጣት/ማሳወቅን (truth seeking)  አስፈላጊነት ሪፖርቱ ያመላከተ ሲሆን፣ እውነት ለማውጣት/ለማሳወቅ  ሂደት መሠረት መሆን ያለባቸው ቁልፍ መርሖች ማለትም ግልጽነት፣ ተጎጂዎችን ማእከል ማድረግ፣አካታችነት፣ አሳታፊነት እና የተቋማት ነጻነት አጽንዖት ተሰጥቷቸዋል። ተሳታፊዎችም የደረሰባቸውን የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶች እና በደሎች በመመስከር እና ሐሳባቸውን በማቅረብ የእውነት ፍለጋ ሂደት አካል ለመሆን ፈቃደኛነታቸውን ገልጸዋል። ሆኖም ግለሰቦች የደረሰባቸውን የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶች በነጻነት ለመናገር እንዲችሉ አስተማማኝ ሁኔታዎች የመፍጠር፣ ደኅንነት እንዲሰማቸው እና ጥበቃ እንዲደረግላቸው የማድረግ እርምጃዎችን መውሰድ አስፈላጊ መሆኑም በሪፖርቱ ተሰምሮበታል።

ለተጎጂዎች የሚሆን ማካካሻን/ካሳ በተመለከተ የተጎጂዎችን የሕይወት ተሞክሮ እና ልዩ ፍላጎቶቻቸውን መሠረት ያደረጉ ልዩ ልዩ ጥቆማዎችን/ሐሳቦችን ሪፖርቱ አካቷል። እነዚህም ጥቆማዎች ከደረሱ ጉዳቶች ጋር ተመጣጣኝ የሆነ የገንዘብ ወይም የዐይነት ካሳ መስጠትን፣ የወደሙ ንብረቶችን መገንባትን/ወደነበሩበት መመለስን፣ የሕክምና እና የሥነ-ልቦና አገልግሎቶች ማቅረብን፣ የተፈናቀሉ ዜጎችን መሠረታዊ ፍላጎቶች ለማሟላት አስቸኳይ የምግብ፣ የውሃ፣ የመጠለያ እና የጤና እንክብካቤ አገልግሎቶች ማቅረብን፣ እንዲሁም መፈናቀልን ለማስወገድ እና በሰብአዊ እርዳታ ላይ ጥገኝነትን ለመቀነስ ዘላቂ መፍትሔዎች የማፈላልግ አስፈላጊነት ላይ ያተኮሩ ናቸው።

የሰብአዊ መብቶች ጥሰትና በደል እንዳይደገም የሕግ እና የተቋማት ለውጦችን እና ማሻሻያዎችን ተግባራዊ ማድረግ አስፈላጊ መሆኑንም ተሳታፊዎች አጽንዖት ሰጥተዋል። ይህም በኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ ሰዎችን/ነዋሪዎች በሙሉ በእኩልነት ለመጠበቅ ሕገ-መንግሥቱን ጨምሮ ሌሎች የሕግ እና የፖሊሲ ማዕቀፎችን መመርመርና ማሻሻልን እንደሚጠይቅ ተገልጿል። ከዚህም በተጨማሪ የሕዝብ ተቋማት፣ በተለይም የፍትሕና የሕግ አስፈጻሚ አካላት ማሻሻልን የሚያካትቱ ጥያቄዎች በማኅበረሰብ ምክክሮቹ ቀርበዋል።

ዕርቅ አስፈላጊና ሊሳካ የሚችል ግብ እንደሆነ ቢታመንም፣ የተጎጂዎች ቁስል ከተፈወሰ በኋላ ብቻ እውን ሊሆን የሚችል ጉዳይ መሆኑን ተሳታፊዎች አጽንዖት ሰጥተው ተናግረዋል። ተሳታፊዎቹ አዎንታዊ አስተዋጽዖ ያላቸው ሃይማኖታዊ፣ ባህላዊና ልማዳዊ የጋራ እሴቶች እንዲሁም ባህላዊ የግጭት አፈታት ሥርዐቶች ዕርቅ ለመፍጠር የሚያስችል ዐቅም እንዳላቸውም አስገንዝበዋል።

ተቀባይነት ያለው፣ እውነተኛ፣ አሳታፊ፣ አካታች፣ ሥርዐተ ጾታን ከግምት ውስጥ ያስገባ/ያሰረጸ እና ተጎጂዎችን ያማከለ የሽግግር የፍትሕ ሂደት ለመተግበር ሁሉንም በግጭት የተሳተፉ አካላት እና የሕብረተሰብ ክፍሎችን ጨምሮ የሀገር አቀፍ ባለድርሻ አካላት ተሳትፎ አስፈላጊ ነው። ሴቶች ንቁ ተሳትፎ እንዲያደርጉና አመለካከቶቻቸውን ለማስረጽ እንዲችሉ ተጨባጭ እና ትርጉም ያለው ዕድል የመስጠት አስፈላጊነትም አጽንዖት ተሰጥቶታል።

የኢትዮጵያ መንግሥት እስካሁን ድረስ የወሰዳቸውን ተጨባጭ አዎንታዊ እርምጃዎች በበጎ በመቀበል፣ መንግሥት በፌዴራልም ሆነ በክልል ደረጃ ፖለቲካዊ ቁርጠኝነቱን በማያሻማ መልኩ እንዲያሳይ ኢሰመኮ ጥሪውን ያቀርባል። ይህም በየጊዜው የሚነሱ ግጭቶችን በውይይት በመፍታት፣ በመላ ሀገሪቱ ሰላምና ጸጥታን በማስፈን፣ የሕግ የበላይነትን በማስከበር፣ በዓለም  አቀፍ የሰብአዊ መብቶች እና የሰብአዊነት ሕጎችን በመጣስ የሚፈጸሙ ከፍተኛ ወንጀሎችን በመከላከል እና አጥፊዎችን ተጠያቂ ያለማድረግ ልማድን (culture of impunity) እንዲያበቃ በማድረግ፣ ለሽግግር ፍትሕ ሥርዐት ቀረጻ እና አፈጻጸም ምቹ ሁኔታ ለመፍጠር የሚያግዙ ወሳኝ እርምጃዎችን መውሰድን ይጠይቃል።  ከዚህም በተጨማሪ የመገናኛ ብዙኃን፣ የሲቪክ ማኅበራት፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ የሃይማኖት እና የባህል መሪዎችን ጨምሮ ሁሉም ባለድርሻ አካላት በሽግግር ፍትሕ ሂደቱ ውስጥ ገንቢ በሆነ መልኩ እና በንቃት እንዲሳተፉ ኢሰመኮ ጥሪውን ያስተላልፋል።

የሽግግር ፍትሕ ባለሞያዎች የሥራ ቡድን ያከናወናቸው ጠቃሚ ሕዝባዊ ምክክሮች እንደተጠበቁ ሆነው፣ የፖሊሲ አውጪዎች በብሔራዊ የሽግግር ፍትሕ ፖሊሲ ቀረጻ ሂደት ላይ የተጎጂዎች ድምፅ እንዲሰማ፣ መፍትሔ እንዲያገኙ እና የተጎዱ ማኅበረሰቦች ፍላጎት በበቂ ሁኔታ እንዲካተት በዚህ ሪፖርት የቀረቡትን ግኝቶች በጥብቅ እንዲያጤኗቸው ኢሰመኮ ያሳስባል። በተጎጂዎች ፍላጎት እና ቅድሚያ በሚሰጧቸው ጉዳዮች ላይ ከፍተኛ ትኩረት የሚያደርግ እና በሰብአዊ መብቶች ደንቦች ላይ የተመሠረተ እውነተኛ እና ሁሉን አቀፍ የሽግግር ፍትሕ ሂደት መተግበር በሀገር አቀፍ ደረጃ የደረሱ ጥፋቶችን በሚመጥን መልኩ ምላሽ ለመስጠት፣ ፍትሐዊ እና ሰላማዊ  ነገን ለመገንባት እና ብሔራዊ አንድነትን ለማምጣት ከሁሉም በላይ ተገቢው መንገድ ነው።

የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር ዶ/ር ዳንኤል በቀለ “የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶች ዋና መንስዔዎችን እልባት ለመስጠት፣ ቀደም ሲል የተፈጸሙ የመብት ጥሰቶች ያስከተሏቸው ቁስሎችን ለመፈወስ፣ እና ለፍትሕ፣ ለዘላቂ ሰላምና ለዕርቅ ምቹ መንገድን ለመፍጠር የሽግግር ፍትሕ አስፈላጊ ነው” ብለዋል።  አክለውም “አካታችነት፣ ትርጉም ያለው ተሳትፎን፣ የሥርዐተ-ጾታን ከግምት ውስጥ ማስገባትን ወይም ማስረጽን፣ ተጎጂዎችን ማእከል ማድረግን፣ ግልጽነትን እና ሀገራዊ ባለቤትነትን የመሳሰሉ መርሖችና መስፈርቶች በሽግግር ፍትሕ ፖሊሲ ቀረጻ እና ትግበራ ሂደት ላይ እንዲካተቱ ኢሰመኮ ከመንግሥት፣ ከሲቪል ማኅበራትና ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት መሥራቱን ይቀጥላል” ሲሉ ገልጸዋል።