“የዘር ማጥፋት ወንጀል” እና “በሰብአዊነት ላይ የሚፈጸም ወንጀል” የሚያመሳስሏቸው አንኳር ነጥቦች አሉ። የዘር ማጥፋት ወንጀል፣በሰብአዊነት ላይ የሚፈጸም ወንጀል እና የጦር ወንጀል “የግፍ እና ጭካኔ ወንጀል” በሚል የወል ስም ይታወቃሉ። የግፍና ጭካኔ ወንጀሎች መላውን የሰው ዘር ህሊና
የሚያውኩ እጅግ ከባድና ዘግናኝ ተግባራት በመሆናቸው ዓለም አቀፍ ወንጀል ናቸው። ዓለም አቀፍ ወንጀል በመሆናቸውም እንደዚህ ዓይነት የግፍና ጭካኔ ወንጀሎች በብሔራዊ ሕግጋት በግልጽ ወንጀል ተብለው ባይደነገጉም እንኳን ድርጊቶቹን የሚፈጽሙ ሰዎች በወንጀል ከመጠየቅና ከመቀጣት ሊያመልጡ አይችሉም። የግፍና ጭካኔ ወንጀል የፈጸሙ ሰዎች ድርጊቱን በፈጸሙበት ሀገር ሕግ ወይም እንደሁኔታው በዓለም አቀፍ ደረጃ በሌላ ሀገር ወይም በዓለም አቀፍ የወንጀል ፍርድ ቤት ተዳኝተው ቅጣት ይጣልባቸዋል። የዘር ማጥፋት እና በሰብአዊነት ላይ የሚፈጸሙ ወንጀሎች በጦርነትም ሆነ በሰላም ጊዜ ቢፈጸሙ በወንጀል ተግባርነት የሚያስቀጡ ሲሆን፤ የጦር ወንጀል የሚፈጸመው፥ ስያሜው እንደሚያመለክተው፥ በጦርነት አውድ ብቻ ነው።